አፋብን "ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ተቋማት" ለሚመራ ድርድር "ምላሽ ለመስጠት" ዝግጁ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናገሩ

በሳር የተሸፈነ መሬት ላይ መሣሪያዎቻቸውን ይዘው የተቀመጡ የፋኖ ታጣቂዎች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) "ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እና ልምድ ባላቸው ተቋማት" የሚመራ እንዲሁም "አፈጻጸሙንም የሚከታተሉት" ድርድር ከመንግሥት ጋር እንዲደረግ ጥያቄ የሚቀርብ ከሆነ "ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ" መሆኑን የቡድኑ ቃል አቀባይ አስረስ ማረ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የአፋብን እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለኅልውና መሪ ዘመነ ካሴ በቅርቡ ከተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ጋር ባደረጉት ውይይት ግጭቶችን "ሁሉን አቀፍ በሆነ ንግግር እና የድርድር ስምምነት" ለመፍታት መንግሥት ላይ "ተገቢው ጫና" እንዲደረግ መጠየቃቸውንም ገልጸዋል።

ከሦስት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በአማራ ክልል ከመንግሥት ጋር እየተዋጉ ያሉት የፋኖ ኃይሎች ቃል አቀባይ የሆኑ አስረስ ይህንን ያሉት ትናንት አርብ ኅዳር 18/2019 ዓ.ም. ከቢቢሲ አማርኛ የሬዲዮ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው።

በዚህ ቃለ መጠይቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሙስ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ከታጣቂ ኃይሎች እና ድርድር ጋር በተያያዘ ለሰጡት አስተያየት የታጣቂ ቡድኑ ምላሽ ምን እንደሆነ አስረስ ተጠይቀዋል።

ዐቢይ በፓርላማ ንግግራቸው፣ ታጣቂ ኃይሎች "ልክ ወንድሞቻችሁ ከኦሮሚያም፣ ከአማራም፣ ከትግራይም ገብተው ተነጋግረው አቋማቸውን ቀይረው እየሰሩ እንዳሉት በሠላም መንገድ ብትሰሩ ይሻላል" ብለዋል።

አክለውም "መቼም ቢሆን አይሳካላችሁም" ሲሉ በአገሪቱ የሚገኙት ታጣቂ ኃይሎች መንግሥታቸውን መጣል እንደማይችሉ ተናግረዋል።

"ይሄ መንግሥት በጣም ይቆያል። ብዙ ባትቸገሩ ጥሩ ነው" ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "እናንተ አንድ እርምጃ ስታስቡ 20 እጥፍ የሚያስብ መንግሥት ነው ያለው" በማለት አስጠንቅቀዋል።

ስለዚህ የፓርላማ ንግግር ጥያቄ የቀረበላቸው የአፋብን ቃል አቀባይ አስረስ፣ "ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌሎችም የሚናገሯቸው የሰላም ጥሪዎች የእጅ ስጡ ጥሪዎች እንጂ የድርድር ጥሪዎች አይደሉም" በማለት አጣጥለዋል።

እስካሁን ድረስ "ይፋዊ በሆነ መንገድ አጠቃላይ የአገሪቱ ቀውስ" የሚፈታ እንዲሁም "በሦስተኛ ወገኖች ቁጥጥር" የሚደረግበት የሰላም ንግግር ለማድረግ ከመንግሥት በኩል ፈቃደኝነት አለ ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።

"በተለይ ከአማራ ኃይል ጋር በዚህ ረገድ እስካሁን ድረስ ተጨባጭ የሚባል የተሰራ ሥራ የለም" ያሉት አስረስ፣ እየተካሄደ ያለው በተለያዩ ሥፍራዎች የሚገኙ የታጣቂ አመራሮችን እና አባላትን "በተለያየ ስልት በማባበል ወደ አገዛዙ እጅ እንዲሰጡ" የማድረግ ሙከራ መሆኑን አንስተዋል።

"[ከዚህ] በስተቀር የአማራ ሕዝብ የህልውና ጥያቄ የተሸከመው ኃይል በተጨባጭ የፖለቲካ ጥያቄ ያለው መሆኑን አምኖ፣ ይህን የፖለቲካ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እና በድርድር ለመፍታት የተደረገ አንዳችም ተጨባጭ እንቅስቃሴ የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ያ ፍላጎት ቢኖር ኖሮ፣ እውነት ለመናገር በብዙ ርቀት የኢትዮጵያን ሰላም መመለስ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ" በማለትም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "እናንተ አንድ እርምጃ ስታስቡ 20 እጥፍ የሚያስብ መንግሥት ነው ያለው" በማለት ታጣቂዎችን አስጠንቅቀዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፣ አፋብን "አገዛዙ በሰላማዊ ድርድር ጥያቄዎችን ለመመለስ ዝግጁ" በሚሆንበት ጊዜ ይዞ የሚቀርባቸውን "ስልቶች በሰነድ" አዘጋጅቷል።

ታጣቂ ቡድኑ ለሰላም ንግግር የራሱ መስፈርቶች እና ተቀባይነት የሚኖራቸው ሂደቶች እንዳሉት የሚናገሩት አስረስ፣ ከእነዚህ አንዱ ድርድሩ "ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እና ልምድ ባላቸው ተቋማት" የሚመራ መሆን አለበት የሚል እንደሆነ አብራርተዋል።

"ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው" ተቋማት ሊደረግ የሚችለውን የሰላም ንግግር "ሊቆጣጠሩ፣ ሊመሩ እና አፈጻጸሙንም ሊከታተሉ" እንደሚገባ አስረድተዋል።

"በዛ ደረጃ የሚመጣ የሰላም እና የድርድር ጥያቄ ካለ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ የሚባል ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነው። አብዛኞቹ እስካሁን የቀረቡት ግን ከዛ በታች የሆኑ ነገሮች ናቸው" ብለዋል።

የፋኖ ኃይሎች ቃል አቀባዩ ከቢቢሲ የቀረበላቸው ተያያዥ ጥያቄ የትብብር ለህልውና እና አፋብን መሪ የሆኑት ዘመነ ካሴ በቅርቡ ከተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር አድርገውታል ስለተባለው ውይይት ነው።

የተመድ ዋና ጸሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ጓንግ ኮንግ በኅዳር መጀመሪያ ከዘመነ ጋር ንግግር ማድረጋቸውን በትግራይ ክልል ከመንግሥት ጋር እየተዋጉ ላሉት የትግራይ ኃይሎች ቅርበት ያለው 'ትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን' ዘግቦ ነበር።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ኮንግ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እና የውይይት ጥረቶችን ለመደገፍ "ከአገር አቀፍ እና ቀጣናዊ ባለድርሻ አካላት" ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት መስከረም ላይ አስታውቆ ነበር።

ኮንግ ከታጣቂዎች ትብብር መሪ ጋር ከመወያየታቸው አስቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ከሆኑት ጌታቸው ረዳ ጋር ተነጋግረው ነበር።

ጌታቸው ውይይቱን አስመልክተው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ንግግራቸው ትኩረት ያደረገው "በሱዳን እና ሶማሊያ ስላለው ግጭት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአስመራ የሚገኘው አገዛዝ በቀጣናው እየተጫወተ ስላለው አጥፊ ሚና" እንደሆነ ገልጸዋል።

አፋብን፣ ህወሓት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን (ኦነሠ) ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ኃይሎችን የያዘውን ትብብር ለኅልውና የሚመሩት ዘመነ፣ ከልዩ መልዕክተኛው ጋር ስላደረጉት ንግግር ቃል አቀባዩ አስረስ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ዘመነ ካሴ ከልዩ መልዕክተኛው ጋር ንግግር ያደረጉት በትብብር ለኅልውና እና በአፋብን ያሏቸውን "ሁለቱንም ኃላፊነቶች በመወከል" ነው።

በውይይቱ የሚደረገው ግጭት ስላደረሰው ተጽዕኖ፣ "ቀጣናው ላይ ያለው አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የትብብር ለኅልውና አመሰራረት እና ቀጣይ ሁኔታዎችን" የተመለከቱ ጉዳዮች መነሳታቸውን ገልጸዋል።

የሰላም ድርድርም የውይይቱ አካል እንደነበረ አክለዋል።

የትብብር ለኅልውና መግለጫ

"በአጠቃላይ ተመድን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ሁኔታ አካታች ፣ ሁሉን አቀፍ በሆነ ንግግር እና የድርድር ስምምነት መፈታት እንዲችል ተገቢውን የዲፕሎማሲ ጫና እንዲያደርጉም ጥቆማ ለማቅረብ ተሞክሯል" ብለዋል።

የትብብር ለኅልውና አሁናዊ እንቅስቃሴን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አስረስ፣ "ትብብሩ በታሰበለት እና በተቀመጠለት አሰራር እና ሂደት መሰረት ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ብለዋል። "የጋራ የፖለቲካ ፕሮግራም ጭምር አለው። እነኚህን ነገሮች ለማስተግበር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ያሉት" በማለት ተናግረዋል።

ትብብሩ ይፋ ካደረጉ ከቀናት በኋላ የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ አየር ማረፊያዎችን ተቆጣጥረው በድጋሚ ግጭት ተጀምሯል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ፌደራል መንግሥት የክልሉ ዋና ዋና ከተሞችን በእጁ ያስገባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ውጊያ ለኤርትራ ድንበር ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች እየተካሄደ እንደሆነ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ጉዳይ የተነሳላቸው አስረስ፣ በክልሉ የታዩትን የግጭት አካሄዶች "ያልተጠበቁ ወታደራዊ ውጤቶች" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

"በወታደራዊ እንቅስቃሴ ረገድ እንዳነሳኸው በተለይ የብልፅግና ኃይል ትግራይ ውስጥ ዘልቆ በመግባቱ ምክንያት ያልተጠበቁ ወታደራዊ ውጤቶች ተከስተዋል። እነኚህን አጠቃላይ ወታደራዊ ሁኔታዎች ለመቀልበስ የትብብሩ ኃይላት በጋራ በመስራት ላይ ነው የሚገኙት" በማለት ተናግረዋል።

አክለውም፣ "ዛሬም ድረስ በአካል የትብብሩ መሥራች ድርጅቶች አመራር አባላት በጋራ በትብብሩ ጉዳይ ላይ እየመከሩ ነው የሚገኙት። በአንድ ላይ በየጊዜው የሚከሰቱ ነገሮችን እየገመገሙ አቅጣጫ እያስቀመጡ ነው ያሉት" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።