ቀጥታ , የሁቲዎች እና ሳዑዲ ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል

የየመን ሁቲዎች ረቡዕ ዕለት ራስ ታኑራ በተባለው የሳዑዲ አረቢያ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ እና በሪያድ የፋይናንስ ቀጣና ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ። ሳዑዲ አረቢያ፣ ሁቲዎች ራስ ታኑራ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ የሰነዘሩትን የድሮን ጥቃት ማክሸፏን ተናግራለች። የሳተላይት ምስሎች ግን ከዚህ ነዳጅ ማጣሪያ ስፍራ ላይ ትልቅ ጭስ ወደላይ እየወጣ መሆኑን አሳይተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የየመን ሁቲዎች የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ ነዳጅ ማጣሪያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገለጹ

    ከራስ ታኑራ ነዳጅ ማጣሪያ ላይ ጭስ ወደላይ ሲወጣ የሚያሳይ የሳተላይት ምስል
    የምስሉ መግለጫ, ጥቃት ተፈጽሞበታል ከተባለው ራስ ታኑራ ነዳጅ ማጣሪያ ስፍራ ላይ ጭስ እየወጣ መሆኑን የሳይተላይት ምስሎች አሳይተዋል

    የየመን ሁቲዎች ረቡዕ ዕለት ራስ ታኑራ በተባለው የሳዑዲ አረቢያ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ እና በሪያድ የፋይናንስ ቀጣና ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ።

    ሳዑዲ አረቢያ፣ ሁቲዎች ራስ ታኑራ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ የሰነዘሩትን የድሮን ጥቃት ማክሸፏን ተናግራለች። የሳተላይት ምስሎች ግን ከዚህ ነዳጅ ማጣሪያ ስፍራ ላይ ትልቅ ጭስ ወደላይ እየወጣ መሆኑን አሳይተዋል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ጥቃት እንደፈጸሙበት የገለጹት ራስ ታኑራ፣ ከዓለም ትላልቅ የድፍድፍ ነዳጅ ኤክስፖርት ወደቦች አንዱ አጠገብ የሚገኝ የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ ነው።

    600 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ገደማ ስፋት እንዳለው የሚገመተው የነዳጅ ማጣሪያ ስፋቱ ከአሜሪካዋ ቺካጎ ከተማ ጋር እንደሚቀራረብ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭን ጠቅሶ ዘገቧል።

    በሌላ በኩል፣ በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር ረቡዕ ዕለት በአገሪቱ የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ጂዳ ወደብ አቅራቢያ አንድ የሁቲ ድሮንን ጠልፎ ማውደሙን አስታውቋል።

    የየመን ሁቲዎችም ይህ ከተገለጸ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ሳዑዲአረቢያ በየመን ወደብ ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ መውሰዳቸውን ተናግረዋል። በዚህ የአጸፋ ጥቃት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙትን ሁለቱን የጂዳ እና የጃዛን ወደቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    የሁቲዎች እና የሳዑዲ መራሹ ጥምር ጦር ግጭት ባለፉት ቀናት ይበልጥ ተባብሶ ታይቷል።

    የትናንቶቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከሁቲዎች ጋር የሚዋጋው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት፣ በየመን የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘውን የሆዴይዳ ወደብን ዒላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን ካስታወቀ በኋላ ነው።

    የሁቲዎች ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ “ሁለቱም ዘመቻዎች ዒላማዎቻቸው ላይ ጉዳት አድርሰዋል” ብለዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ፣ በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በሁቲዎች የተወነጨፈ ተተኳሽ ጃዛን ወደብ ላይ ማረፉን አስታውቆ ነበር።

    የሳዑዲ መራሹ ጥምረት ቃል አቀባይ ቱርኪ አል ማሊኪ “ቀላል ጉዳት የደረሰ ሲሆን የተገደለ ወይም የቆሰለ ሲቪል የለም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

    አክለውም «የተተኳሹን ዓይነት ለመለየት ጥረቶች ቀጥለዋል” ብለዋል።

    ዋና ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛውን የምዕራብ የመን ክፍል የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች፣ ረግቦ የነበረው የመን ግጭት በኢራን ጦርነትን ምክንያት ባለፈው ሐምሌ ላይ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሳዑዲ አየር ማረፊያዎች፣ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች እና የመስሪያ ቤት ሕንፃዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

    ከዚህ ቀደም በግዙፉ የሳዑዲ የነዳጅ አምራች አራምኮ ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ተቋሙ በጊዜያዊነት ሥራ እንዲያቆም አስገድደው ነበር። አየር ማረፊያዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶችም ወደ ሪያድ የሚደረጉ አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆነዋል።

  2. የኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባ ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የሐሙስ ኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።