ራሳቸውን ለሚያጠፉ ሰዎች መርዝ ሲሸጥ የነበረው ካናዳዊ ተከሳሽ የተጎጂ ቤተሰቦችን ይቅርታ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Peel Regional Police / PA Wire
በ40 አገራት በሚገኙ የኦንላይን ራስን የማጥፋት መድረኮች አማካኝነት መርዛማ ኬሚካሎችን ሲሸጥ የነበረው ካናዳዊ ግለሰብ፣ በድርጊቱ እጅግ መጸጸቱን እና ይህንን ድርጊት በጭራሽ እንደማይደግመው በመግለጽ በፍርድ ቤት የተጎጂዎችን ቤተሰቦች ይቅርታ ጠየቀ።
ኬኔዝ ሎው የተባለው ተከሳሽ ይህንን የተናገረው የካናዳ አቃብያነ ሕግ ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኛ የ25 ዓመት እስራት እንዲፈርዱበት በጠየቁበት ትናንት አርብ በተካሄደ ችሎት ላይ ነው።
የ61 ዓመቱ ሎው ባለፈው ግንቦት ላይ ካናዳ ኦንታሪዮ ከተማ የሚገኙ 14 ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ረድቷል በሚል በቀረቡበት 14 ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል። ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥም ለ79 ሰዎች ሞት ተጠያቂ እንደሆነ ተገልጿል።
ግለሰቡ በእንግሊዝ እና በዌልስ ለሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ ተጎጂዎች ሞት ምክንያት መሆኑንም አምኗል።
የካናዳ ባለሥልጣናት ይበልጥ ከባድ የሆኑ የነፍስ ማጥፋት ክሶችን እንዲያቀርቡበት የጥፋተኝነት ስምምነት የተደረገ በመሆኑ፣ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ወይም ከብሪታናውያኑ ሞት ጋር በተያያዘ ክስ አይመሠረትበትም።
መርዙን አቅርቦላቸው የሞቱት አብዛኞቹ ተጎጂዎቹ ወጣቶች እና አእምሮ ጭንቀት ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን ዓቃብያነ ሕግ አርብ ዕለት በኦንታሪዮ ፍርድ ቤት በተካሄደው የቅጣት ውሳኔ ስሚ ችሎት ላይ በአጽንዖት አንስተዋል።
ተከሳሹ ሎው፣ በአቃቤ ሕግ የቀረበበት የቅጣት ውሳኔ ሀሳብ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ በቁጥጥር ሥር ከዋለበት ከአውሮፓውያኑ ግንቦት 2023 ጀምሮ የሚቆጠር የ20 ዓመት ገደማ እስር ይጠብቀዋል።
በትናንቱ ችሎት መከራከሪያቸውን ያቀረቡት አቃቤ ሕግ ካትሊን ዶኸርቲ፣ ተከሳሹ ሎው "ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን" የሚበዘብዝ አጥቂ ሲሉ ገልጸውታል።
ዐአቃቤ ሕጓ፣ "የሚያስፈልጋቸው እርዳታ ነበር። ያገኙት ግን የሎውን እና የሞት ምርቶቹን ነበር" ብለዋል። የሎው ዋነኛ ግብ ገንዘብ ማግኘት እንደነበርም አክለዋል።
"ሰዎች መክፈል የሚችሉ ከሆነ ይሸጥላቸው ነበር። ሎው የሚሸጥለት ግለሰብ ምን አይነት ነገር እያጋጠመው እንዳለ ለመረዳት የሚያስችል ምንም ንግግር ወይም ማጣራት አያደርግም ነበር" ሲሉም ከስሰዋል።
እነዚህን ውንጀላዎች የተቃወሙት የሎው ጠበቃ ማቲው ጉርሌይ በበኩላቸው፣ ደንበኛቸው ተጎጂዎቹ ለነበሩበት የአእምሮ ሕመም ትግል ተጠያቂ አለመሆኑን በማንሳት ተከራክረዋል።
"እያንዳንዱ ክስተቶች በራሳቸው አሳዛኝ ናቸው" ያሉት ጉርሌይ፣ "ሎው በመካከላቸው የሚገኝ የጋራ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ሁሉ ተጎጂዎች ምርቶቹን እንዲፈልጉ ላደረጋቸው ትግል እና መከራ መንስኤው ሎው አልነበረም" ብለዋል።
ሎው ተጎጂዎቹን እየረዳሁ ነው የሚል "የተሳሳተ እምነት" እንደነበረው ጠበቃው ገልጸዋል። ጠበቃው ፍርድ ቤቱ የ12 ዓመት እስራት እንዲፈርድበት ጠይቀዋል።
በችሎቱ መጨረሻ ላይ ንግግር ያደረገው ሎው በአንጻሩ፣ ተጎጂዎቹ ራሳቸውን እንዲያጠፉ በመርዳቱ ጥልቅ ጸጸት እንደሚሰማው ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
"ለተጎጂዎች ቤተሰቦች፤ የምትወዷቸውን ሰዎች ማጣት በቃላት የሚገለጽ አይደለም። ጥልቅ ሀዘኔን እገልጻለሁ። አሁንም ጸጸት ይሰማኛል፤ ይቅርታ" ብሏል።
በቀጣይ በሚኖረው የችሎት ውሎ የቅጣት ውሳኔው እንደሚተላለፍበት ይጠበቃል።































