ሕክምናው 3.5 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቀው፣ ልጆች እንዳይናገሩ እና እንዳይራመዱ የሚያደርገው ሕመም

የፎቶው ባለመብት, Oleksii Bykov
ኒካ ሦስተ ዓመቷ ነው። እንደ ዕድሜ እኩዮቿ ዓለምን የማወቅ ጉጉት አላት።
መጽሐፍ ማገላበጥ ትወዳለች። አንዳንዴም ረባሽ ልጅ እንደምትሆን እናቷ አና ትናገራለች።
ኒካን ከዕድሜ እኩዮቿ የሚለያት ያለባት ሕመም ነው። በዘረ መል የሚተላለፈው ሕመም በርካቶች ላይ አይከሰትም።
ኤስፒጂ47 ወይንም Hereditary Spastic Paraplegia Type 47 በሚል መጠሪያ ይታወ ቃል።
ዓለም ላይ ይህ ሕመም እንዳለባቸው የሚታወቀው 130 ሰዎች ብቻ ናቸው። በእርግጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሽታው ሊኖርባቸው ይችላል። ነገር ግን ሕመሙ እንዳለባቸው አያውቁም።
በሽታው የልጆችን ነርቭ ያዛባል። ስለዚህም መነጋገር እና መንቀሳቀስ ይቸገራሉ።
በአሜሪካ፣ በቦስተን የልጆች ሆስፒታል የእንቅስቃሴ ችግር ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዳሪስ ኢብራሂሚ ፋራኪሪ እንደሚሉት መራመድ የሚችሉ ልጆች በጊዜ ሒደት ለመንቀሳቀስ ይቸገራሉ።
ለዓመታት ይህ በሽታ ሕክምና አልነበረውም። ብዙ ሰዎች ላይ የሚከሰት ስላልሆነ የመድኃኒት አምራች ተቋማት እምብዛም ትኩረት አልሰጡትም።
ሕመሙ ያለባቸው ልጆች ወላጆች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አሰባስበው ልጆቻቸው የዘረ መል ሕክምና (gene therapy) እንዲያገኙ ያደርጋሉ።
ሕክምናው ለሙከራ ዝግጁ ቢሆንም ሙከራውን ለማከናወን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ወላጆች ይናገራሉ።
ሕክምናው ሙከራ ቢደረግበት የልጆችን ሕይወት ማሻሻል የሚችል ነው።
የኒካ እናት አና ፖፖቪች ልጇ ላይ ችግር ማስተዋል የጀመረችው እድገቷ ሲዘገይ ነበር። ኒካ መንከባለል እና መዳህ የጀመረችው ዘግይታ ነው።
አንድ ዓመት ሲሆናት ያለ ድጋፍ መቀመጥ አልቻለችም።
ዩክሬናውያኑ ጥንዶች ልጃቸው ኒካ ሕመሙ እንዳለባት ያወቁት በቼክ ሪፐብሊክ በተደረገ ምርመራ ነው።
የዩክሬን ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2022 ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ሄደዋል።
ኒካ በተደጋጋሚ ራሷን ስታ ትወድቅ ነበር። በተደጋጋሚ ምርመራ ቢደረግላትም ሐኪሞች ሕመሟን ማወቅ አልቻሉም።
ሕመማቸው ላልታወቀ ልጆች የዘረ መል ምርመራ ለማድረግ የአውሮፓ ኅብረት ገንዘብ መድቧል። ኒካ ምርመራ የተደረገላትም በዚህ መርሃ ግብር አማካኝነት ነው።
"ኤስፒጂ47 የሚለውን ስናይ ጉግል ማድረግ ጀመርን። ዶክተሯ የሕመሙን ስም የሰማችው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ነገረችን" ስትል አና ታስታውሳለች።

የፎቶው ባለመብት, Oleksii Bykov
ሕመሙ ምንድን ነው?
ዶ/ር ዳሪስ እንደሚሉት ሕመሙ የሚከሰተው ልጆች ኤፒ4ቢ1 (AP4B1) የተባለው ዘረ መላቸው ሲራባ ነው። ይህም የነርቭ እድገትን ያዛባል። የሚያስከትለው ጉዳት ከነርቭም የሚሻገር ነው።
"አብዛኞቹ ልጆች ምልክት የሚያሳዩት በተወለዱ የመጀመሪያው ዓመት ነው። የእድገት መዘግየት ይታይባቸዋል። መቀመጥ፣ መቆም እና መራመድ ከሚጠበቅባቸው ጊዜ ይዘገያሉ። መነጋገርም በቶሎ አይጀምሩም" ሲሉ ያስረዳሉ።
ሕመሙ ያለባቸው ልጆች ከአራት እስከ ስድስት ዓመታቸው ድረስ እንቅስቃሴ ለማድረግ የበለጠ ይቸገራሉ። የእግራቸው ጡንቻቸውም ይተሳሰራል።
ቀስ በቀስ ሕመም እየተባባሰ ይመጣል። መናገር እና መራመድ የሚችሉ ልጆች መናገርም ሆነ መራመድ ይሳናቸዋል።
ዕድሜያቸው 10 ወይም 11 ሲደርስ ዊልቼር እንደሚያስፈልጋቸው ሐኪሙ ይናገራሉ።
ሕመሙ እንዳለባቸው የሚታወቁ ሰዎች ውስን መሆኑን ይገልጻሉ። ነገር ግን ሕመሙ እንዳለባቸው ገና ያልታወቀላቸው ሰዎች በርካታ እንደሆኑ ይገምታሉ።
ሕመሙ ያለባቸው ልጆች ወላጆች ተሰባስበው ብላክፊን ባዮ የተባለ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ መሥርተዋል።
ከኩባንያው የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በመላው ዓለም ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች ከ3,600 ሊበልጡ ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Chris Edwards
በርካታ አገራት ይሄንን ሕመም ማከም የሚችሉ ባለሙያዎች ስለሌላቸው በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ትክክለኛ አሐዝ ለማወቅ ከባድ እንደሆነ ዶ/ር ዳሪስ ይናገራሉ።
አንዳንድ ልጆች ሰረብራል ፓልሲ (cerebral palsy) እንዳለባቸው ይነገራቸዋል። ይህ ሕመም እንቅስቃሴን በመደበኛ ሁኔታ ለመወጣት አስቸጋሪ የሚያደርግ ነው።
የክሪስ ኤድዋርድ የ12 ዓመት ልጅ ሮቢ በዊልቼር ትንቀሳቀሳለች።
በአውሮፓውያኑ 2016 ልጁ ኤስፒጂ47 እንዳለባት ተነገረው። በወቅቱ በዓለም ላይ ሕመሙ እንዳለባቸው ከሚታወቁ ልጆች 10ኛዋ ነበረች።
በአሜሪካ የሚኖረው አባት ሕመሙ ላይ ምርምር የሚሠሩ የተለያዩ የሳይንስ መጽሔቶች ላይ የሚጽፉ አጥኚዎችን ለማነጋገር ሞክሯል።
ለአጥኚዎቹ የልጁን ፎቶዎች ኢሜል እያደረገ ምክራቸውን እና እርዳታቸውን ይጠይቅ ጀመር።
በ2017 በቦስተን የሚገኘው የሕጻናት ሆስፒታል ለሕጻናቱ የዘረ መል ሕክምና መሰጠት እንዳለበት መግለጹን ተከትሎ በገንዘብ የሚደግፉ ባለ ሃብቶች እና ባለሙያዎች መፈለግ ተጀመረ።
ክሪስ በርካታ ሰዎች ላይ የማይከሰቱ ሕመሞች (rare diseases) ላይ ምርምር ለሚያደርጉ ተቋማት ባጠቃላይ መልዕክት ልኳል።
ለኤስፒጂ47 ሕክምና ለማግኘት በሚደረገው ምርምር ላይ እንዲሳተፉ ጠይቋል።
"የባዮቴክኖሎጂ ተቋማት ከሚያገኙት ትርፍ አንጻር ስለሚያዩት ምርምር ለማድረግ ቢያንስ 500 ታካሚዎች ይፈልጋሉ። ብዙ ቀና ሰዎች አግኝቻለሁ። ነገር ግን ሁሉም የሰጡኝ ተመሳሳይ መልስ 'ያሉት ታካሚዎች ጥቂት ናቸው' የሚል ነው" ሲል ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Boston Children's Hospital
ፈታኙ የሕክምና ሒደት
ክሪስ ለጥያቄው አወንታዊ ምላሽ ሳያገኝ ብዙ ደክሟል። በስተመጨረሻም ልጆቻቸው ከታመሙባቸው ወላጆች ጋር ተጣመረ።
ኪውር ኤፒ-4 የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሠረቱ። ከዚያም ለሕመሙ ሕክምና ለማግኘት ብላክፊን ባዮን አቋቁመዋል።
በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ወላጆች ሕክምናውን ለማስጀመር ገንዘብ ሰብስበዋል። ወላጆቹ ክሮሺያ፣ ሕንድ፣ ዩክሬን፣ ሊቢያ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድስ፣ አሜሪካ፣ ዮናይትድ ኪንግደም እና በሌሎችም አገራት የሚኖሩ ናቸው።
የኒካ አባት ኦሌክሲ ቢኮቭ ስለ ልጁ ሕመም በአደባባይ መናገር ምን ያህል ከባድ እንደነበር ያስታውሳል። ለሕክምናዋ የሚሆን ገንዘብ መጠየቅም ነበረበት።
"ለልጃችን ማድረግ የሚገባን ነገር ነው" ይላል ኦሌክሲ።
ወላጆች ካሰባሰቡት ገንዘብ የተወሰነው በዩኬ ለሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሼፊልድ ተሰጥቷል። በዩኒቨርስቲው ዶ/ር ሚሞን አዙዝ የዘረ መል ሕክምና ምርምር አድርገዋል።
ይህ ሕክምና የሚሰጠው የተጎዳውን ኤፒ4ቢ1 ዘረ መል አውጥቶ በተሻሻለ የቫይረሱ ዝርያ ውስጥ በማስገባት ነው።
ልጆች የተሻሻለው ቫይረስ ሲሰጣቸው ወደ አንጎል ሕዋሳቸው ጤናማ ዘረ መል ይሸጋገራል።
የተጎዱ የአንጎል ሕዋሳት አዲሱን ዘረ መል መጠቀም ይጀምራሉ።
አጥኚዎቹ እንደገለጹት፤ ሕክምናው ውጤታማ የሚሆነው ከአንድ እስከ አምስት ዓመት ባሉ ልጆች ላይ ነው።
"ከጊዜ ጋር የሚደረግ እሽቅድምድም ነው። ታማሚዎች እንቅስቃሴ ማድረግ ከተሳናቸው በኋላ በሕክምናው የመዳን ዕድላቸው ይቀንሳል። ስለዚህም ቀድሞ ሕክምናውን መስጠት ያስፈልጋል" ሲሉ ዶ/ር ዳሪስ ያስረዳሉ።
በ2025 የአሜሪካ ምግብ እና መድኃኒት ተቆጣጣሪ ተቋም የመጀመሪያውን ሙከራ ፈቅዷል። የዘረ መል ሕክምና ሙከራው የሚከናወነው በልጆች ላይ ነው።
ልጆቻቸው የታመሙባቸው ወላጆች እስከ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ቢሰበስቡም ሕክምናው 3.5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያስፈልገዋል።
ሙከራው በአምስት ዓመት ውስጥ ሕክምናው ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ እና የሕክምናውን ውጤታማነት ለመገንዘብ ይረዳል።
ተመራማሪዎች አሁን ላይ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ቢያገኙ በስድስት ወራት ውስጥ የመጀመሪያውን ሕጻን ማከም እንደሚጀምሩ ሐኪሙ ይናገራሉ።
ሕክምናው ያለው የአደጋ ተጋላጭነት እንዳለ ሆኖ ልጆቻቸው የታመሙባቸው ወላጆች ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ይናገራሉ።
"ኒካ ሦስት ዓመት ሊሞላት ነው። ሕክምናው ገበያ ላይ እስከሚውል መጠበቅ አንችልም። መድኃኒቱ ማቀዝቀዣ ውስጥ ተቀምጦ የመጀመሪያውን ታካሚ ልጅ እየጠበቀ ነው" ስትል እናቷ ትናገራለች።
ክሪስ እንደሚለው፤ በአሜሪካ መድኃኒት ሠርቶ ለማጠናቀቅ እና ፈቃድ ለማግኘት ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።
ይሄንን ገንዘብ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ እና ፈቃድ ለማግኘትም ጊዜ እንደሚወስድ ይገነዘባል።
የኒካ እናት እንደምትለው ቤተሰባቸው ገንዘብ ለማግኘት "ሁሉንም አማራጭ" ይጠቀማል።
"ኒካ መናገርም መራመድም አትችልም። ሆኖም ግን ደስተኛ ልጅ ናት" ትላለች።
ክሪስ ልጁ በሕክምና ሙከራው ለማሳተፍ ዕድሜዋ እንዳለፈ ይናገራል። ሆኖም ግን ከሌሎች ወላጆች ጋር ጥረቱን ቀጥሏል።
"ሕክምናውን የሚያገኘውን የመጀመሪያውን ቤተሰብ ማየት ስለምፈልግ ነው የማላቆመው። የልጃቸው ሕይወት እስከወዲያኛው ሲለወጥ ማየት እሻለሁ" ይላል።


































