የመንግሥት ሠራተኞች የሃይማኖት መለያዎችን እንዳያደርጉ የሚከለክለው የካናዳዋ ግዛት ሕግ በፍርድ ቤት ጸና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመንግሥት ሠራተኞች መስቀል እና ሂጃብን ጨምሮ ሃይማኖታዊ መለያዎችን እንዳይጠቀሙ የሚከለክለውን የካናዳዋን ኩቤክ ግዛት ሕግ በአብዛኛው አጸደቀ።
'ቢል 21' በሚል የሚታወቀው አወዛጋቢው ሕግ ከሙስሊም ሴቶች፣ ከሲክ እና ከካቶሊክ እምነት መምህራን እንዲሁም መሠረታዊ መብቶችን ይጥሳል የሚል ተቃውሞ ካነሱ በርካታ ቡድኖች የሕግ ተግዳሮት ገጥሞታል።
ኩቤክ ግዛት፣ የካናዳ መንግሥት ልክ እንደ የሃይማኖት ነፃነት ያሉ የተወሰኑ መብቶችን ለማስወገድ የሚመዘውን የሕግ ክፍተት በመጠቀም ሕጉን ያፀደቀችው በ2011 ዓ.ም. ነው።
የአርብ ዕለቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔም በካናዳ ታሪክ ከፍተኛ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ ሲሆን ውሳኔው በኩቤክ ግዛት እና በመላ አገሪቱ በርካቶችን አነጋግሯል።
ውሳኔውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ለአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት መንግሥት ሕጉ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ እንደሚያጠና ገልጸው፣ ሕግ አውጪዎች በቁጥር አነስተኛ የሆኑትን ጨምሮ የሁሉንም ካናዳውያን ነፃነት እና መብቶች ማክበር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 'ቢል 21' ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን እንዲሁም ግዛቷ የተጠቀመችው የሕግ ክፍተት ተገቢ ስለመሆኑ እንዲሁም ገደቦች መኖር አለመኖራቸውን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውለታል።
ፍርድ ቤቱ 'ቢል 21'ን በአብዛኛው ሕጋዊ መሆኑን ያረጋገጠ ቢሆንም የኩቤክ ተመራጭ ባለሥልጣናት በሃይማኖት ምክንያት ፊታቸውን እንዳይሸፍኑ (ኒቃብ እንዳይለብሱ) በመከልከል ዴሞክራሲያዊ መብትን ይጥሳል ብሏል።
ጨምሮም አንድ ሕግ ከካናዳ መብቶች እና የነፃነት ሕጎች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን ወይም አለመሆናቸውን የማወጅ ሥልጣን እንዳለው ገልጿል።
End of podcast promotion
ከሰባቱ የፍርድ ቤቶቹ ዳኞች አብዛኞቹ የግዛቷ ሕግ ተቀባይነት እንዳለው የወሰኑ ሲሆን የተወሰኑት ከፊሎቹን ሕጎች ተቃውመዋል።
ዳኛ አንድሮማች ካራካትሳሰስ ፣ ሚሸል ኦቦንሳዊን እና ኒኮላስ ካሲረር የሕግ ክፍተቱ " ከመሠረታዊ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ከሆነችው ካናዳ ባሕርይ ጋር አብሮ የማይሄድ ሕግ ለመፍቀድ ሊውል አይገባም" ብለዋል።
ሕጉ በተለይም የሃይማኖት ነፃነትን፣ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን እና የእኩልነት መብትን የሚጥስ እንደሆነ እንደሚያምኑም ዳኞቹ ገልጸዋል።
በኩቤክ የሚገኙ የሲቪል ነፃነት ቡድኖችም ሂጃብ የሚለብሱ ሙስሊም ሴቶችን በግዛቷ ውስጥ ካሉ ቁልፍ የአደባባይ ሕይወት በመነጠል እጅግ እንደሚጎዳ በመግለጽ ሕጉን ተቃውመውታል።
የካናዳ ሙስሊሞች ብሔራዊ ምክር ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ስቴፈን ብራውን በበኩላቸው ሕጉን "አድሏዊ" ሲሉ በመጥራት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተችተዋል።
ሕጉን ከተቃወሙት ዋና ዋና ቡድኖች አንዱ የሆነው የእንግሊዝ ሞንትሪያል የትምህርት ቤት ቦርድ ሊቀመንበርም ቦርዱ በውሳኔው "በጣም ማዘኑን" ገልጸዋል።
ኩቤክ ግን ሕጉ በግዛቷ ውስጥ የመንግሥት እና የሕዝብ ተቋማትን ከሃይማኖት ጋር ለመለየት አስፈላጊ መሆኑን እና የማንነቷ ወሳኝ አካል መሆኑን በማስረዳት ሞግታለች።
የኩቤክ ሉዓላዊነትን የሚደግፈው የፌዴራል ፓርቲ የሆነው 'ብሎክ ኩቤኮይስ' መሪ አርብ ዕለት የተላለፈው ውሳኔ ግዛቷ እሴቶቿን የመጠበቅ መብትን የሚያከብር ነው ብሏል።
ኩቤክ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሕዝብ ትምህርት ቤት መምህራን፣ ዳኞች እና የፖሊስ መኮንኖች የሚታዩ የሃይማኖት መለያዎችን እንዳያደርጉ የከለከለች ሲሆን በኮሌጆች እና በዩኒቨርሲቲዎች የጸሎት ቤቶች እንዳይኖሩ እና በግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንዳይከናወኑ ከልክላለች።
ከዚህም በተጨማሪ ያለ ፈቃድ መናፈሻዎች እና ጎዳናዎች ላይ ጭምር በአደባባይ በቡድን የሚደረጉ ጸሎቶችን እና ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች አግዳለች፤ ሕጉን በማያከብሩት ላይ የገንዘብ ቅጣት አስተዋውቃለች።
በስተሰሜን ምሥራቅ ካናዳ የምትገኘው ኩቤክ ግዛት በአገሪቷ ካሉ 10 ግዛቶች ትልቋ ስትሆን በዓመት ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ ስደተኞችን እንደምትቀበል የአገሪቱ መንግሥት መረጃ ያሳያል።
































