ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'የወረቀት አውሮፕላኖችን ማባረር እንጂ ከጦር ጄቶች መደበቅ አልፈልግም'
በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን መካከል ጦርነት በተጀመረበት በመጀመሪያው ቀን፣ ማይክል የትምህርት ቤት ዩኒፎርሙን ለብሶ፣ ቦርሳውን በትከሻው አነግቶ ከቤቱ ለመውጣት ዝግጅቱን አጠናቆ ነበር። ነገር ግን ከመውጣቱ በፊት እናቱን ሲሰናበታት የሚያሳይ ፎቶግራፍ እንድታነሳው ጠየቃት።
"ተመልሶ መጥቶ የማስታወሻ ፎቶ እንዳነሳው ሲጠይቀኝ ገረመኝ" ትላለች እናቱ ለቢቢሲ ስትናገር። "በፎቶው ላይ እጁን እያወዛወዘ ተሰናበተኝ ፤ ነገር ግን ለመጨረሻ ጊዜ የማየው እንደሚሆን ፈጽሞ አልገመትኩም ነበር። በእርግጥም የዘላለም ስንብት ነበር።"
በዚያው ዕለት በሚናብ ከተማ በሚገኘው የሻጃሬህ ታይቤህ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ በተሰነዘረው የሚሳዔል ጥቃት በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት በጦርነቱ የመጀመሪያ ወር ውስጥ ከተገደሉት ከ340 በላይ ሕፃናት አንዱ ማይክል ሆነ፤ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል።
እናቱ ለቢቢሲ ስትናገር "ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት እራት አቀረብኩለት እና በከፍተኛ ፍላጎት ተመገበ" ብላለች።
"እማዬ የምግብሽ ጣዕም እንደ ገነት ነው አለኝ። በጣም ተገረምኩኝ እና የጭንቀት ስሜት ተሰማኝ፤ 'ለምንድነው እንዲህ የምትለኝ? ከዚህ በፊት እንዲህ ብለኸኝ አታውቅም' ብዬ ጠየቅኩት።"
"ሁልጊዜም የስሙ ትርጉሙ 'የአምላክ መልአክ' እንደሆነ ይናገር ነበር። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ምኞቱን ቢነግረኝ ለእግዚአብሔር እንዲያሳካለት እነግርለታለሁ ይል ነበር፤ ልክ እግዚአብሔር ይህን ልጅ በእውነት ወዶት ወደ ራሱ እንደወሰደው ሁሉ።"
ዩኒሴፍ በተለያዩ አገራት በግጭቱ ተሳታፊ በሆኑ ወገኖች የሚሰነዘሩ የማያቋርጡ ጥቃቶች ሕፃናት የሚተማመኑባቸውን ተቋማት እና መሠረተ ልማቶች እያወደሙ መሆኑን ገልጿል።
ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የውኃ መስመሮች እና ቆሻሻ ማስወገጃዎች መወደማቸውን ሮይተርስ ጨምሮ አስታውቋል።
ዩኒሴፍ አክሎም "በቀጣናው በቦምብ ጥቃቶች እና በመልቀቂያ ትዕዛዞች ምክንያት ነዋሪዎች በመውጣታቸው ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።"
ከእነዚህ መካከል የ12 ዓመቱ ሊባኖሳዊ ቃሲም "ጉዞው በማይታመን ሁኔታ አድካሚ ነበር፤ ቤታችን በቦምብ ከፈረሰ በኋላ ቤተሰቦቼ ለእኛ መጠለያ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው፤ ነገር ግን መከራችን በዚህ አላበቃም።
"ተዋጊ አውሮፕላኖች በላያችን ላይ በሚበሩበት ጊዜ ሁሉ እናቴ አሁንም ትጮኻለች። የቦምብ ጥቃቱ ሲጀምር በአጋጣሚ ወደ መስኮት ተጠግቼ ካገኘችኝ ልትጎትተኝ ትሮጣለች፣ ስለዚህ እኔም እሸሻለሁ። ይህ ሁሉ ህልም ቢሆን እያልኩ እሮጣለሁ። በፊት በፍጥነት አድጌ ወንድ መሆን እመኝ ነበር ፤ ግን እንደዚህ ባለ ሁኔታ አይደለም።"
"በሌሊት፣ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ስሰማ ለብቻዬ ለመተኛት ስለምፈራ ወደ እናቴ ሄጄ አጠገቧ እተኛለሁ። እሷም ታቅፋኝ እንዳልፈራ ትነግረኛለች። ነገር ግን እጇ ሲንቀጠቀጥ ይሰማኛል፤ እናም እሷም እንደፈራች አውቃለሁ።"
ቃሲም የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምፅን "አስፈሪ ድምፅ ያለው አስጨናቂ ጭራቅ" ሲል ይጠራዋል።
"ምን ዓይነት ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል ለመገመት በላያችን ላይ የሚበሩትን የአውሮፕላን ዓይነቶች መለየት ለምጃለሁ" ብሏል።
"ይህንን የተማርኩት ልቤ በከፍተኛ ፍጥነት እየመታ ነው። ይህን የተማርኩት ቤታችን በእስራኤል የአየር ድብደባ ከፈረሰበት ጊዜ ጀምሮ ነው።"
በጦርነቱ ወቅት በሊባኖስ ስላለው የትምህርት ቤት ሕይወት የተጠየቀው ቃሲም "ትምህርት ቤቴ? አንዳንዴ ይዘጋል፣ አንዳንዴ ደግሞ እሄዳለሁ፤ ነገር ግን ተመልሼ ላልመጣ እችላለሁ ወይም ተመልሼ ስመጣ ቤተሰቦቼን አላገኛቸውም ብዬ እፈራለሁ። በትምህርቴ ላይ ማተኮር ፈጽሞ አልቻልኩም።"
እግር ኳስ መጫወት እንደሚወድ የሚናገረው ቃሲም፣ "ነገር ግን ለመጫወት ከቤት ለመውጣት መፍራት ጀምሬያለሁ፤ ምናልባት ስመለስ ቤተሰቦቼን ባላገኛቸውስ ብዬ እሰጋለሁ። እኔ ውጪ እየተጫወትኩ ሳለ እነሱ በቦምብ ሊመቱ ይችላሉ፣ ስለዚህ ከቤት መውጣቴን አቁሜያለሁ" ይላል።
አክሎም "እኛ በሰላም መኖር እንፈልጋለን፤ ልክ እንደማንኛውም የዓለም ሕፃን መደሰት እንፈልጋለን። ስለ ፖለቲካ ብዙ አላውቅም፤ ነገር ግን ፍርሃት ምን ማለት እንደሆነ፣ የለቅሶ ድምፅ እና የአምቡላንስ ድምጽ ምን እንደሚመስል በሚገባ እረዳለሁ" ብሏል።
"ጦርነት አልፈልግም። ደስተኛ የልጅነት ጊዜን የሚመራ፣ ለበዓላት በአዳዲስ ልብሶች እያማረ ትምህርቱንም የሚማር ሕፃን መሆን ነው የምፈልገው። መፍራት የምፈልገው ፈተና ስላለብኝ እንጂ በቦምብ ጥቃት ምክንያት አይደለም። በቅርቡ ምን ዓይነት ጥቃት እንደሚመጣ ለማወቅ የአውሮፕላን ዓይነቶችን ሳይሆን የፍራፍሬ ዓይነቶችን መለየት እፈልጋለሁ። በፀሐይ ብርሃን የወረቀት አውሮፕላኖችን ማባረር እንጂ ከእውነተኛዎቹ መደበቅ አልፈልግም።"
የዩኒሴፍ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ጦርነት በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ የግጭት ቀጠናዎች ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን መከራ አባብሶታል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት ቋሚ መጠለያ፣ ንጹህ ውሃ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን አጥተዋል፤ በተለይም ባለፈው ጥቅምት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢታወጅም፣ ብዙዎች አይጥ በወረራቸው ድንኳኖች ውስጥ መኖራቸውን እንደቀጠሉ ነው።
የአዳም ዩሱፍ እናት ወጣቷ ያስሚን "ልጄ ገና አንድ ወር እንኳን አልሞላውም ነበር፤ አውሎ ነፋስ የበረታበት ዝናባማ ምሽትም ነበር። የንፋሱ ድምጽ በጣም ከፍተኛ ስለነበር ምንም የአይጥ ድምጽ አልሰማንም።
"በድንጋጤ ከልጄ ጩኸት እስክነቃ ድረስ ወደ ድንኳናችን ሰብረው ገቡ። በድንኳኑ ውስጥ ምንም መብራት ስለሌለን የእጅ ባትሪ ፈልጌ ልጄ ላይ አበራሁት፤ በዚህ ጊዜ ፊቱ በደም ተሸፍኖ እና በከፍተኛ ሁኔታ እየደማ ሳገኘው ደነገጥኩ። ባለቤቴ ነቅቶ ሸለምጥማጥ የሚመስሉት አይጦች ሲሸሹ እስኪያይ ድረስ መጮኼን ቀጠልኩ፣ ከዚያም እንደነከሱት ተረዳን።"
"ከዚያም በቀጥታ ወደ አል ራንቲሲ ሆስፒታል በፍጥነት ሄድን፤ በዚያም የሕክምና ግብዓቶች እጥረት በመኖሩ ዶክተሮቹ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተው ቆሙ። በመጨረሻም አዲስ የተወለዱ ሕጻናት ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ወሰኑ እና ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተሉ ቆይተው ፈጣሪ ሕይወቱን በተዓምር አተረፈለት።"
"ልጄ እንዲህ ላለ አደጋ ይጋለጣል ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅኩም ነበር፤ ይህ ሁሉ የሆነው ሊጠገን በማይችል ሁኔታ በነተበ እና በተቀደደ ድንኳን ውስጥ ስለምንኖር ነው። በቆሻሻ በተከበበ እና ለነፍሳት እና ለአይጦች ምቹ በሆነ ሙሉ በሙሉ ኢሰብአዊ በሆነ አካባቢ፣ በፈራረሱ ቤቶች ፍርስራሽ መካከል ለመኖር ተገድደናል።"
የዩኒሴፍ ሪፖርት በጦርነቱ የመጀመሪያ ወር ውስጥ የተጎዱ ሕፃናትን ዝርዝር እንዲህ ያቀርባል፡-
- በኢራን 216 ተገደሉ፣ 1,767 ቆሰሉ
- በሊባኖስ 124 ተገደሉ፣ 413 ቆሰሉ
- በእስራኤል አራት ተገደሉ፣ 862 ቆሰሉ
- በኩዌት አንድ ተገደለ
- በባህሬን አራት ቆሰሉ
- በዮርዳኖስ አንድ ቆሰለ
ነገር ግን የአካል ጉዳት ያልደረሰባቸው እንኳ "ለረጅም ጊዜ ለጥቃት እና ለአለመረጋጋት በመጋለጣቸው" ምክንያት "በአንጎል እድገት፣ በስሜት ቁጥጥር እና በረጅም ጊዜ የአእምሮ ጤና ላይ ዘላቂ ተጽእኖ" ሊደርስባቸው ይችላል።
ጦርነቱ በጀመረ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ በኳታር የሚኖሩ ጥንዶች የ4 እና የ6 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሁለት ልጆቻቸውን ከጥቃት ለመከላከል በዶሃ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ቁምሳጥን ውስጥ ደብቀዋቸዋል።
የ40 ዓመቷ ክርስቲና ፓስቺን ለቢቢሲ "የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት በጣም ከባድ ነበሩ። የማያቋርጥ የሚሳዔል ማዕበል ይመጣ ነበር፣ እናም የፍንዳታዎቹ ድምፅ በላያችን ላይ ይሰማ ነበር። ለልጆቹ ትልቅ የነጎድጓድ ድምፅ ነው አልናቸው። ለሰሚው አስቂኝ ሊመስል እንደሚችል አውቃለሁ።"
"እስራኤል ኢራንን ማጥቃቷን እና መጠለል እንዳለብን ከአሜሪካ ኤምባሲ በስልኬ ማሳወቂያ ሲደርሰኝ ከልጄ ጋር በዳንስ መማሪያ ክፍል ውስጥ ነበርኩ። ስለዚህ እሷን ይዤ 'ምን እየሆነ ነው?' እያለች ስትጠይቀኝ ትልቅ ነጎድጓድ እየጠሰማ ነው፤ ዝናብ ስለሆነ ወደ ቤት መግባት አለብን በማለት ነገርኳት።"
"በመጨረሻም እውነቱን ለሕፃናት በሚገባ መንገድ ነገርናቸው፤ 'ታዲያ ዝናቡ የት አለ?' አሉን። እኛም አገራት ጠብ ላይ ናቸው፤ መጥፎ ጠብ ውስጥ ናቸው፤ እኛ ግን ምንም እንዳንሆን ቤታችን ውስጥ በሰላም እንቆያለን' ብለን አስረዳናቸው።"
ጥንዶቹ የኳታር ሚሳዔል መቃወሚያዎች የሚተዉትን ጭስ ከቤታቸው ሆነው ማየታቸውን ይናገራሉ።
የክርስቲና ባለቤት የ46 ዓመቱ አሌክስ ዴሚያንቹክ ለቢቢሲ ሲናገር "በአሁኑ ወቅት ነገሮች ከቁጥጥራችን ውጪ ናቸው። ልጆቻችን ከልክ በላይ እንዳይጨነቁ እና እንዳይጠበቡ እኛ በተቻለ መጠን በተረጋጋ መንፈስ ለመቆየት መሞከር አለብን... ነገር ግን በእነሱ ዕድሜ የሁኔታውን አሳሳቢነት ሙሉ በሙሉ ይረዳሉ ብዬ አላስብም። ትምህርት ቤት በመዘጋቱ እና ተጨማሪ የቲቪ/ስልክ መመልከቻ ጊዜ በማግኘታቸው ብቻ ደስተኞች ይመስሉኛል። የዕለት ተዕለት ኑሯችን በቤት ውስጥ ተወስኗል። አብዛኛው ጊዜያችንንም በቤት ውስጥ ወዲያ ወዲህ በማለት እናሳልፋለን።"
ባለቤቱ ደግሞ በጣም አስፈሪው ጊዜ የሚሳዔል ጥቃቶች ሊሰነዘሩ የሚችሉበት የሌሊት ሰዓት እንደሆነ ተናግራለች።
"ፍንዳታዎቹ በሚከሰቱበት ጊዜ በጣም ያስፈራል፤ ከዚያም ምንም መስኮት ወደሌለበት የእቃ ማከማቻ ክፍል እንሮጣለን" ስትል ገልጻለች።
"እንደ አንድ ጥንቃቄ የምንወስደው ነገር፣ ልጆቹ እንቅልፍ እንደወሰዳቸው ሁላችንም አብረን እንድንሆን ወደ እኛ ክፍል እናመጣቸዋለን...ይህም የሆነው በፍጥነት አንስተን ቢያንስ ወደ ታችኛው ፎቅ ለማውረድ እንዲመቸን ነው።"
የዩኒሴፍ ሪፖርት በጦርነቱ የመጀመሪያ ወር በእስራኤል ውስጥ ተገድለዋል ያላቸው አራት ሕፃናት፣ በሼሜሽ ከተማ ላይ በደረሰ የኢራን የሚሳዔል ጥቃት ከሞቱት ዘጠኝ ሰዎች መካከል ነበሩ።
ከእነዚህም ውስጥ ሦስቱ ታዳጊዎች ሳራ (13 ዓመት)፣ አቪጌኤል (15 ዓመት) እና ያዕቆብ (17 ዓመት) የመምህር ይስሐቅ ቢቶን ልጆች ነበሩ።
ማይክል የሞተበት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚሳዔል በተመታ በማግሥቱ ጥቃቱ በደረሰበት ዕለት ተማሪዎቻቸውን እያስተማሩ ነበር።
ሳራ፣ አቪጌይል እና ያዕቆብ በአካባቢው ወደሚገኝ የቦምብ መጠለያ ለመደበቅ ሲሄዱ፤ ባለቤታቸው ታማር እና የአራት ዓመቷ ልጃቸው ራቼል ከምኩራቡ አቅራቢያ በሚገኘው ቤታቸው ቀርተው ነበር።
ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል "የምኩራቡ ጣሪያ እና ኮርኒስ ተደርምሶ ነበር፤ በመስኮት በኩል ተመለከትኩኝ፣ ምኩራቡ የነበረበትን አካባቢ አየሁት። በእሳት እየተቃጠለ ነበር፣ በሰማዩ ላይም በጣም ጥቁር ጭስ ይታይ ነበር። ወደዚያ ለመሄድ ፈርቼ ነበር።"
"ለመሄድ ድፍረቱን ካገኘሁ በኋላ፣ ምኩራቡ ሙሉ በሙሉ ወድሞና መጠለያው ተከፍቶ አየሁት። መጠለያው አስተማማኝ አልነበረም። ከለላ አልሰጠም። አንድ ሳይሆን፣ ሁለት ሳይሆን፣ ሦስት ልጆቼን ነው ያጣሁት።"
"በአንዲት ጀምበር፣ በድንገት ግማሽ ቤተሰቤን አጣሁ።"