የተኩስ አቁም ስምምነት ምንድን ነው? ጦርነትን የሚያስቆም ግዴታስ ነው?

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ኢራን እና አሜሪካ በቅድመ ሁኔታ የተያዘ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል። በዚህ የተኩስ አቁም ወቅት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የመርከብ እንቅስቃሴ ይፈቀዳል።

ይህ የሆነው አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ከአንድ ወር በኋላ ሲሆን፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ለነዳጅ እና ለሌሎች ከባሕር ሰላጤው ለሚደረጉ ወሳኝ የመርከብ እንቅስቃሴዎች ወሽመጡን እንደገና ካልከፈተች "አጠቃላይ ሥልጣኔዋ ያከትምለታል" ብለው ከዛቱ ከሰዓታት በኋላ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉን ገልጸው ምክንያቱም "ከኢራን ጋር ዘላቂ ሰላም እና የመካከለኛው ምሥራቅን በሚመለከት ስምምነት ለመድረስ" ጊዜ ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል ።

"የተለያዩ የድርድር ነጥቦች ከሞላ ጎደል በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስምምነት የተደረሰባቸው ቢሆንም፣ የሁለት ሳምንት ጊዜ ግን ስምምነቱ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ተግባራዊ እንዲሆን ያስችላል" ብለዋል።

"ይህን የረዥም ጊዜ ችግር ለመፍታት መቃረብ ክብር ነው።"

ትራምፕ በኋላ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ አሜሪካ "ጠቅላላ እና የተሟላ ድል" ማግኘቷ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።

ነገር ግን የኢራን ከፍተኛ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት አሜሪካ ታሪካዊ ውድቀት ገጥሟታል ብሏል።

በቀጣዮቹ አስራ አምስት ቀናት ፓኪስታን ውስጥ ድርድር እንደሚደረግ በመጥቀስ ዝርዝር ነጥቦቹ ተጠናቅቀው "ኢራን በግንባር ያስመዘገበችው ድል በፖለቲካዊ ድርድርም ይጠናከራል" ሲል አክሏል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ "ሁለቱም ወገኖች አስደናቂ ጥበብ እና ማስተዋል አሳይተዋል፤ እናም ሰላም እና መረጋጋትን ለማስቀጠል ገንቢ በሆነ መልኩ ሲሳተፉ ቆይተዋል።

"የኢስላማባድ ንግግር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንዲሳካ ከልብ ተስፋ እናደርጋለን እናም በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ መልካም ዜናዎችን ለመጋራት እንፈልጋለን።"

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም አካላት በዓለም አቀፍ ሕግ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡ እና የተኩስ አቁም ውሎችን በማክበር በአካባቢው ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት መንገዱን እንዲጠርጉ" ጠይቀዋል።

ነገር ግን እንደሌሎች ግጭቶች የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሸጋገር አሁንም ብዙ ጥበብ የሞላበት ዲፕሎማሲ ይፈልጋል።

የተኩስ አቁም ምን ማለት ነው?

እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ “ተኩስ አቁም” ለሚለው ቃል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ፍቺ የለም።

ቃሉ የመጣው “ተኩስ ማቆም” ከሚለው ወታደራዊ ትዕዛዝ የመጣ ሲሆን፣ “ተኩስ መጀመር” ለሚለው ትዕዛዝ ተቃራኒ ነው።

ይህም ሁለት ተፋላሚ ወገኖች በድርድሩ ወቅት እንደሚወስዱት ትርጉም ሊሆን ይችላል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ተኩስ አቁም” እና “ግጭት ማቆም” በሚሉት ቃላት መካከል ብዙ ጊዜ ልዩነት እንዳለ ገልጿል።

“የግጭትን ማቆም” ጦርነትን ለማቆም የሚደረግ መደበኛ ያልሆነ ስምምነት ነው ይላል።

“የተኩስ አቁም” የበለጠ መደበኛ ነው። በተጨማሪም ይህ የተኩስ አቁም ዓላማን፣ በቀጣይ የሚኖርን የፖለቲካ ሂደት፣ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን እና የሚሸፍነውን አካባቢም የሚያካትት ነው።

ምን ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚፈቀዱ እና እንደማይፈቀዱ እንዲሁም የተኩስ አቁሙ እንዴት ክትትል እንደሚደረግበት ሊገልጽ ይችላል።

ለምሳሌ የላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 1993 እንዲጠናቀቅ ያደረገው የብሔራዊ ጊዜያዊ መንግሥቱ ከላይቤሪያ አርበኞች ግንባር እና ከተባበሩት የነጻነት ዘመቻ ጋር ስምምነት መድረሱ ነው።

ሁለቱም ወገኖች የጦር መሳሪያ መታጠቅን እንዲያቆሙ፤ ወታደራዊ ቦታዎችን ላለመቀየር ወይም ላለማጥቃት፣ ተጨማሪ ጦርነት ላለመቀስቀስ እና ፈንጂዎችን እና ተቀጣጣይ መሳሪያዎችን ላለመጠቀም ተስማምተዋል።

የተኩስ አቁም ቋሚ ነው ወይስ ጊዜያዊ?

ሁለቱም ሊሆን ይችላል ይላል የመንግሥታቱ ድርጅት።

አንዳንድ ጊዜ በጦርነት ውስጥ ያሉት ሁለቱ ወገኖች ጊዜያዊ ወይም የመጀመሪያ ደረጃ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ይስማማሉ።

ይህ የሚደረገው ጥቃትን ለመቀነስ ወይም ሰብአዊ ቀውስን ለማቃለል ሊሆን ይችላል።

ከአንድ ዓመት በፊት በእስራኤል እና በሐማስ በሚመሩ ታጣቂ ቡድኖች መካከል ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ከስምምነት ሲደረስ፤ ሐማስ 105 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል በበኩሏ 240 የሚሆኑ እስረኞችን ፈትታለች።

የመጀመሪያ ደረጃ የተኩስ አቁም ቀጣይ ድርድርን የሚያግዝ እና ለዘላቂ የተኩስ አቁም መንገድ ለመክፍት የሚረዳ ከባቢን ሊፈጥር ይችላል።

በአውሮፓውያኑ 2000 ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በመካከላቸው ያለውን ግጭት ለማቆም ስምምነት ተፈራርመው ነበር።

ይህም ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዲቻል ነበር። በዚህም የሁለቱን አገራት ጦርነት ያቆመው የአልጀርስ ስምምነት ተፈርሟል።

ሆኖም ግን በተስማሚዎቹ መካከል የሚጠበቀው እርምጃ ካልተወሰደ የተኩስ አቁም ስምምነት መጣስ፣ አለመሳካት እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ጦርነቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም ተከታታይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በአውሮፓውያኑ 1978፣ 1981 እና 1990 ሞክሯል።

ነገር ግን ከእያንዳንዱ ስምምነት በኋላ ጦርነት አገርሽቷል። በኋላም በ1975 የተጀመረው ጦርነት እስከ 1990 ዘልቋል።

በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አንደኛው ወይም ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በመሬት ላይ ያላቸውን አቋም ለማጠናከር የተኩስ አቁሙን ሊጠቀሙበት ሊፈልጉ ይችላሉ።

በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተሳካ የሰላም ንግግሮችን ተከትሎ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ የተኩስ አቁም ሊደረግ ይችላል።

ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 1998 በሰሜን አየርላንድ የተደረገው የጉድ ፍራይዴይ ስምምነት የአይአርኤ እና ታማኝ ቡድኖቹ መሳሪያቸውን “ከጥቅም ውጪ” ለማድረግ መስማማታቸውን ያካትታል።

ስምምነቱ ቀጣይነት ያለው ሰላም እና ስምምነትን ለማበረታታት የታቀዱ አንቀጾችንም ይዟል።

ምን ዓይነት የተኩስ አቁም ዓይነቶች አሉ?

እስራኤል እና ሐማስ በኅዳር 2023 የደረሱትን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም “የሰብዓዊ ተኩስ አቁም” ብለው ጠርተውታል።

ሰብዓዊ ተኩስ አቁም ግጭቱን ለመቀነስ ወይም ሰብዓዊ ቀውስን ለማቃለል አንዳንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

ለምሳሌ የሱዳን መንግሥት በዳርፉር የተካሄደውን ጦርነት ለ45 ቀናት በማስቆም የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርስ ከሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ እና ከፍትህ እና የእኩልነት ንቅናቄ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሷል።

በአውሮፓውያኑ 2004 ኢንዶኔዥያ በሱናሚ ከተመታች በኋላ በአካባቢው እርዳታ እንዲደርስ የኢንዶኔዥያ መንግሥት እና ፍሪ አቼ የተባለው ንቅናቄ የተኩስ አቁም አውጀዋል።

መልክዓ ምድራዊ የተኩስ አቁም ተብሎ የሚጠራው ደግሞ በተወሰነ አካባቢ ላይ የሚደረግ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

በአውሮፓውያኑ 2018 ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት አደራዳሪነት የየመን መንግሥት እና ሁቲዎች በቀይ ባሕር ሆዴይዳ ወደብ ዙሪያ የሚደረገውን ጦርነት በማስቆም የአካባቢውን ሕዝብ ለመጠበቅ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።