ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሦስት ዓመታት ከቀሪው ዓለም የተነጠለው እና የስልኩን መልዕክት ያልሰማው ሱዳናዊ ጋዜጠኛ ሕይወት
መሐመድ ሱሌይማን ባለፈው ጥር በባሕር ጠረፏ የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳን በሚገኘው የቴሌኮም ቢሮ እንደገባ ማልቀስ ጀመረ።
ከሦስት ዓመታት በፊት በሱዳን ጦርና በቀድሞ አጋሩ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል በነበረ የሥልጣን ሽኩቻ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዺህ ለረዥም ጊዜ ስልኩ ሲጮህ አልሰማም ነበር።
ይህ ጋዜጠኛ እና ምሁር በምዕራባዊቷ ኤል-ፋሸር ከተማ መውጫ አጥቶ ከቆየ በኋላ ፖርት ሱዳን መድረስ የቻለ ሲሆን፣ በከተማዋ በነበረው የኮሚኒኬሽን መቋረጥ ምክንያት ከዓለም ተገልሎና የሚያየውን አሰቃቂ ድርጊት መግለጽ ተስኖት ቆይቷል።
"በቢሮው ውስጥ ሰዎች በስልካቸው ሲያወሩ ሳይ ስሜታዊ ሆንኩ፤ ላለፉት ሦስት ዓመታት ስልኬ ምንም ድምጽ አልነበረውም፤ ሲም ካርዱን እንዳስገባሁ ግን እንባዬ ፈሰሰ" ብሏል ለቢቢሲ።
ስልኩ በመጨረሻ ሲከፈት የሦስት ዓመታት የሃዘን መልዕክቶች ይጎርፉ ጀመር። የሞቱ የሥራ ባልደረቦቹ ዜና እና በሕይወት መኖሩን የሚጠይቁ ጓደኞቹ መልዕቶች ነበሩ።
"ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ ሰው ደውሎ የሞትኩ መስሎት እንደነበር ነገረኝ። ፖርት ሱዳን መሆኔን ሰምቶ ቢደውልም በቪዲዮ ደውዬ እስከሚያየኝ ድረስ አላመነም ነበር፤ ካየኝ በኋላ ግን ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ" ይላል።
መሐመድ እንደሚለው በተወሰነ መልኩ የመረጃ ልውውጥ መቋረጡ ከሁከቱ እኩል ይረብሽ ነበር።
ሁኔታውን ሲገልጽ "በድሮን እና በቦምብ የሚፈጸመውን ስልታዊ ግድያ እንዲሁም ለ18 ወራት በኤል ፋሸር ላይ ተጥሎ በነበረው ከበባ ምክንያት የሚፈጸመውን እልቂት እያየሁ ምንም መናገር አለመቻሌ የትንፋሽ ማጠር ስሜት ይፈጥርብኝ ነበር" ይላል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከተማዋን ሲቆጣጠሩ "በምድር ላይ የመጨረሻው የፍርድ ቀን የመጣ ነበር የሚመስለው" ብሏል።
የኤል-ፋሸር መያዝ በካርቱም በሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጀመረው ጦርነት እጅግ አሰቃቂ ምዕራፍ ነበር።
ጦርነቱ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተስፋፋ ሲሆን በተለይም ኤል-ፋሸር በሚገኝበት እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጠንካራ ይዞታ በሆነው በምዕራባዊው ዳርፉር ክልል እጅግ አሰቃቂ ሆኗል።
ጦርነቱ ወደ አራተኛ ዓመት ሲሻገር አገሪቱ በመንግሥት ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙ ቀጣናዎች ተከፋፍላለች። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በዓለም አስከፊ በተባለው ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ተፈናቅለዋል፤ ሌሎች ደግሞ በዓለማችን አስከፊው ሰብዓዊ ቀውስ ተገፍተው ከአገራቸው ወጥተዋል።
የአሜሪካ የዲፕሎማሲ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ሁለቱም ተዋጊዎች በየፊናቸው ውጊያውን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ድጋፍም እያገኙ ነው።
የመሐመድ ታሪክ ጦርነቱ ንጹሐንን ከምግብ፣ ከቤት፣ ከሕይወት አልፎም ከማንነታቸው እንዴት እንደሚያራቁት የሚያሳይ ነው።
በኤል-ፋሸር የሚገኙ ንጹሐን በከበባው ውስጥ በነበሩበት ወቅት በከተማዋ የረሃብ አደጋ መከሰቱን በተባበሩት መንግስታት ድጋፍ የሚደረግለት የምግብ ተቆጣጣሪ ተቋም አስታውቋል።
መሐመድ "በየመንገዱ የሞቱ ሕፃናትን እናይ ነበር " ይላል።
"ሴቶች በረሃብ እና በጥማት ምክንያት ልጆቻቸውን መሸከም አቅቷቸው መንገድ ላይ ጥለዋቸው ሲያለቅሱ አይተናል። የምናውቃቸውን ሰዎች እንኳ የምናደርግላቸው ነገር አልነበረም። ምግብ የለም፣ ውሃ የለም፣ የመጀመሪያ እርዳታ የለም። ስለዚህ እያለቀስክ አስክሬናቸውን እየዘለልክ ጉዞህን ትቀጥላለህ" ሲል ሁኔታውን ይገልጸዋል።
ብዙዎች በቅርባቸው ባለው የተሻለ ደኅንነት ወዳለው ወደ ታዊላ ከተማ ለመሸሽ በሚያደርጉት ጥረት መንገዱ በአስክሬን እና በቁስለኛ ተሞልቶ ነበር። " በጣም በጣም ብዙ፤ በቁጥር የማይገለጽ ነበር "ይላል።
እርዳታ ለመጠየቅ የሚያስችል ስልክ ቢኖር ኖሮ ብዙ ቁስለኞችን ጥለን ለመሄድ ባልተገደድን ነበር ሲል ተናግሯል።
"ከሰውነት ያፈነገጡ በመሆናቸው ልገልጻቸው የማልችላቸው ነገሮች አሉ፤ የሚያስቆጨው ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ይህንን እውነታ በድምጽ እና በምስል አለማስቀረታቸው ነው።"
"የዓለም ሚዲያ እስካሁን በኤል ፋሸር ምን እንደተፈጠረ አያውቅም" ሲል በምሬት ይናገራል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪዎች የግል ጥሰቶች መፈጸማቸውን ቢያምኑም፣ የጥፋቱ መጠን በጠላቶቻቸው የተጋነነ መሆኑን ይናገራሉ። ሆኖም ሁለቱም ወገኖች በጦር ወንጀል ይጠረጠራሉ።
በከተማዋ የነበሩት መገናኛዎች ከጦርነቱ መጀመርያ አንስቶ በውጊያውና በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የኤሌክትሪክ ኃይል ብዙ ጊዜ በመጥፋቱ በጣም ይቆራረጡ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሙሉ በሙሉ ተዘጉ።
አንዳንድ ሰዎች የስታርሊንክ መሳሪያዎችን በድብቅ በማስገባት በሳተላይት ኢንተርኔት መጠቀም ቢችሉም በጣም ውድ እና ጦሩ ከተማዋን በተቆጣጠረበት ወቅት በመከልከሉ አገልግሎቱ የተገደበ ነበር። አር እስ ኤፍም ያገኘውን መሰል መሳሪያ ሁሉ ያወድም ነበር።
ጋዜጠኞች በሁለቱም ወገኖች "ለስለላ ትጠቀማላችሁ" በሚል ጥርጣሬ ለአደጋ ይጋለጡ ስለነበር እውነቱ ሳይወጣ ቆይቷል።
መሐመድም እንደሌሎች ሱዳናውያን ሁሉ በሐምሌ 2017 ዓ.ም. ወደቤቱ በመመለስ ላይ ሳለ ከእርሱ በሁለት ሜትር ርቀት ላይ ድብደባ ተፈጽሞ ነበር።
ከጥቃቱ ቢተርፍም ወደየትም መደወል የማይችለውን ስልኩን እንደያዘ ለግማሽ ሰዓት መሬት ላይ እንደተኛ ያስታውሳል።
"በእርግጥም ቆስዬ ቢሆን ኖሮ እሞት ነበር" ይላል።
ድሮኖች በከተማዋ ሲበሩ ቢመለክትም ሰዎች ከድበደባው ራሳቸውን አንዲከልሉ ማስጠንቀቅ የሚችልበት ምንም ዓይነት የመገናኛ ዘዴ አልነበረውም።
እንዲያውም ኔትወርክ የሌለው ስልክም ቢሆን በሚያሳየው ብርሃን ምክንያት ዒላማ የመሆን ስጋት ሊፈጥር ይችል ነበር።
"ድብደባው ሲጀመር ክፍል ውስጥ አልጋ ስር አሊያም ከመሬት በታች በተቆፈረ ምሽግ ውስጥ ትደበቃለህ፤ ወይም ወዳገኘኸው ነገር ከለላ ትፈልጋለህ። አንዳንድ ጊዜ ይህ እጅግ ሞቃታማ በሆነ የአየር ሁኔታ እስከ 7 ሰዓታት ሊዘልቅ ይችላል፤ ምንም ሳትናገር ዝም እንዳልክ ትቆያለህ፤ የምታየውንም መናገር አትችልም" በማለት ያስረዳል።
መሐመድ በርካታ ህጻናት ሲሞቱ ተመልክቷል።
"የአህያ ጋሪ እንኳን ሲንቀሳቀስ በድሮን ሲመታ ሕጻናት ይኖሩበታል" ብሏል።
መሐመድ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥም ተስፋ አልቆረጠም ነበር። ከጎረቤቶቹ ጋር በመሆን ቁርዓን እየቀሩ እና እየጸለዩ መከራውን ለማለፍ ሞክረዋል።
"ከከሰዓቱ የፀሎት ጊዜ ቀጥሎ የቁርዓን ክፍሎችን እናነባለን፤ ድብደባ ባለ ጊዜ ደግሞ በሰሜን ሲሆን ወደ ደቡብ፤ በደቡብ ሲሆን ደግሞ ወደሰሜን እንሸሽ ነበር።"
በመጨረሻም በጥር ወር ከሁለት ወራት በላይ በተደረገ ጉዞ በቻድ በኩል አድርጎ የወታደራዊው መንግሥት መቀመጫ ወደሆነችው ፖርት ሱዳን ሲደርስ "የአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እንደደረስኩ በግንባሬ ተደፍቼ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፤ በሰላም እደርሳለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር" ብሏል።
ምንም እንኳን መሐመድ አሁን ሰላማዊ ቦታ ቢገኝም፣ ማንነቱን የሚገልጹ ሰነዶችን ሁሉ በጦርነቱ አጥቷል። ሰነዶቹን መልሶ ለማግኘትም ከቢሮክራሲው ጋር ሌላ ትግል ገጥሟል።
"ለ22 ቀናት ወደ የተለያዩ ቢሮዎች ተመላልሻለሁ፤ በመጨረሻ እናትህ እና ሌሎች ምስክሮችን ይዘህ ና አሉኝ። እኔስ ፈጣሪ ይመስገን ምስክሮች ሰለነበሩኝ አቀረብኩኝ። ነገር ግን በጦርነቱ ምክንያት ማንም የሌለው ሰው እጣ ፈንታ ምንድን ነው?"
አሁን መሐመድ ከዓለም ጋር ተገናኝቷል፤ ሆኖም ከተመለከተው እና ካገጠሙት ልምዶች አንጻር ዓለም ለሱዳን ፊቷን እንዳዞረች ይሰማዋል።
"ዓለም ላይ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚባል ነገር የለም" ይላል በምሬት።
"የተባበሩት መንግሥታት የሚባል ነገር የለም። የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ቢኖሩ ኖሮ በኤል-ፋሸር ሰዎች በየዕለቱ እንዲህ አይሞቱም ፣ አይራቡም ፣ አይጠሙም ፣ በድሮንና በፈንጂ አይደበደቡም ነበር።"
"ተኩስ አቁም የለም፤ መድሐኒት የለም፤ መሠረታዊ የሕይወት ማቆያዎችም የሉም።"
ዓለም የሱዳንን ሰብዓዊ ፍላጎት ማሟላትም ሆነ ጦርነቱን ማስቆም አልቻለም። የተባበሩት መንግሥታት በ2026 ግምገማው ያስፈልገኛል ካለው 2.87 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እስካሁን የተሟላው 16.2% ብቻ ነው።
መሐመድ ሱሌይማን አሁን የሚያያት ሱዳን የተከፋፈለች እና ሕዝቧ የተበታተነባት አገር ናት። ሆኖም የታሪኩን እውነት መናገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያምናል።
"በእርግጥም የተከሰቱ ነገር ግን ለመተረክ አንዲት ነፍስ ያልተረፈችባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ትውስታው እኛ ጋር ብቻ ይቆያል። እስከምንሞት ግን ቀጣዩ ትውልድ በትውልድ አገሩ በክብርና በኩራት ይኖር ዘንድ ሁኔታውን እንዲስተካከል እውነታውን እንናገራለን ።"