ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ዘመን ፖለቲከኛን የአሜሪካ አምባሳደር አድርጋ ሾመች

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአፓርታይዱ መንግሥት ባለሥልጣን የነበሩትን ሮልድ ማየር ለአሜሪካ አዲስ አምባሳደር አድርገው ሾሙ።

አገሪቱ ባለፈው ዓመት ኢብራሂም ራሳል፤ ዶናልድ ትራምፕን "የነጮች የተበዳይነት መንፈስ እየቀሰቀሱ" ነው በሚል ባቀረቡት ትችት ከዋሽንግተን ከተባረሩ በኋላ በአሜሪካ ከፍተኛ ልዑክ አልነበራትም።

ይህም ቀድሞውኑ የሻከረውን የሁለቱ አገራትን ግንኙነት ያባባሰው ሲሆን፤ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ደግሞ ግንኙነታቸው ተሸርሽሯል።

የራማፎሳ ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግወይና የአዲሱን አምባሳደር መታጨት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"ሲሪል ራማፎሳ ማየር በአሜሪካ አምባሳደር እንዲሆኑ መሾማቸውን አረጋግጣለሁ" ብለዋል።

የ78 ዓመቱ ማየር እ.አ.አ በ1990ዎቹ በደቡብ አፍሪካ አናሳ ነጮች የሚመሩትን የዘር መድልዎ ስርዓት እንዲያበቃ ከአሁኑ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጋር ዋና ተደራዳሪ በመሆን ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ናቸው።

አዲሱ አምባሳደር አፓርታይድ እየተባለ የሚጠራውን የዘር መድልዎ ያስተዋወቀው የናሽናል ፓርቲ ተወካይ ነበሩ።ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ደግሞ በኔልሰን ማንዴላ የሚመራውን አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ወኪል ነበሩ።

በዚህ ወቅት ሁለቱ ፖለቲከኞች ወዳጅነት መመስረታቸው ይነገራል።

ማየር ባለፈው ዓመት ራማፖሳ የአገሪቱን የተለያዩ ችግሮች እንዲፈታ የተቋቋመ ብሔራዊ ምክክር ሂደትን እንዲመሩ ከመረጧቸው 32 ታዋቂ ደቡብ አፍሪካዊያን ውስጥ አንዱ ናቸው።

አዲሱ አምባሳደር በአፓርታይድ መንግሥት ወቅት የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፤ በኋላ ላይ እ.አ.አ በ1994 ኔልሰን ማንዴላ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የአንድነት መንግሥቱን ተቀላቅለዋል።

ከሁለት ዓመት በኋላ ይህን ኃላፊነታቸውን በመልቀቅ የአንድነት ዲሞክራሲ ንቅናቄ የጋራ መስራች ሆነዋል። በኋላ ላይ ግን ገዢውን ኤኤንሲ ፓርቲ ተቀላቅለዋል።

ማየር 'አፍሪካነር' ተብለው የሚጠሩት ነጭ ደቡብ አፍሪካዊ ሲሆኑ ተራማጅ እንደሆኑ ይታመናል። በአክራሪ ነጮች ዘንድ ግን በተለይም በሰላም ንግግሩ ወቅት በነበራቸው ሚና እንደ ከሃዲ ይቆጠራሉ።

'አፍሪካነሮች' በደቡብ አፍሪካ ቀደምት አውሮፓ ሰፋሪዎች ሲሆኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሁኑ ወቅት የዘር ፍጅት እና ግድያ እያስተናገዱ መሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም ይህ ክስ በተለያዩ ወገኖች በስፋት ውድቅ የተደረገ ነው።

ትራምፕ ይህ ክሳቸው አሜሪካ ለደቡብ አፍሪካ ትሰጠው የነበረውን እርዳታ እንድትገታ እና ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን እንደ ስደተኛ ተቆጥረው ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ፖሊሲ ለመከተላቸው አንድ ምክንያት ነው።

ራማፎሳ የአንድ ዘር ወይም ባህል ሰዎች ተለይተው እየተገደሉ ነው የሚለውን ክስ "ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው" ብለዋል።

የአዲሱ አምባሳደር ሹመት በደቡብ አፍሪካ የተደበላለቀ ስሜት የፈጠረ ሲሆን፤ አንዳንዶች ፖለቲካዊ ብልጠት ሲሉት ሌሎች ደግሞ በተለይም በነበታቸው የፖለቲካ ተሳትፎ እና በዕድሜያቸው ስጋት አንስተዋል።

ሹመቱን የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪ የሆኑት ጁሊየስ ማሊማ "በዲሞክራሲያችን ትግል ላይ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ስድብ ነው" ብለውታል።

ፕሬዝዳንት ራማፖሳ ውሳኔያቸውን በመከላከል ማየር "ደቡብ አፍሪካን በደንብ ይወክላሉ" ሲሉ የአገሪቱን ፖሊሲዎች በደንብ የሚያውቁ ሠው ናቸው ብለዋል።