ቀጥታ , ከፑቲን እና ዢ ጋር የሚወያዩት ትራምፕ ቻይና ገብተዋል

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የሦስዮሽ ውይይት ሲያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል። የኒውክሌር መሣሪያ ትጥቅን መቀነስ ከውይይት አጀንዳዎቻቸው መካከል መሆኑ ተገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የናይጄሪያ 36 ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ እንዲያደራጁ እና እንዲያሰማሩ ሊፈቀድ ነው

    የናይጄሪያ ፖሊስ አርማ

    ከናይጄሪያ የፌደራል ኃይሎች ጎን ለጎን ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ እንዲያደራጁ እና እንዲያሰማሩ ሊፈቀድ ነው።

    የአገሪቱ 36 ግዛቶች ለቀረበው ረቂቅ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።

    ረቂቁ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ሕግ ሆኖ እንዲተገበር ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ፊርማቸውን ማኖርም ይጠበቅባቸዋል።

    ግዛቶች ፖሊስ እንዲያሰማሩ በፌደራል እና በግዛቶች ደረጃ ሕጉ መተግበር እንዳለበት ተገልጿል።

    ረቂቁ የቀረበው ናይጄሪያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሰላም ማጣት እየተፈተነች ባለችበት ወቅት ነው።

    የፌደራል ኃይሉ የጅምላ እገታ፣ በማኅበረሰቦች መካከል የሚፈጠር ግጭት እና ዝርፊያን ለመቆጣጠር እየሞከረ ይገኛል።

    የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የፖሊስ ኃይል እጥረት ክፍተት ፈጥሯል። ፖሊሶች በአግባቡ ሥልጠና እንደማይሰጣቸው እና በቂ መሣሪያ እንደሌላቸውም ተመልክቷል።

    አሁን ላይ ተግባራዊ እየሆነ ያለው አሠራር በ1999 በወጣው ሕገ መንግሥት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ፖሊሶች የሚሰማሩት በማዕከላዊ መንግሥቱ ሥር ነው።

    ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ አደራጅተው እንዲያሰማሩ መፍቀድ አለመረጋጋት ሲከሰት በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጡ እንደሚረዳ ይታመናል። ፖሊሶቹ ማኅበረሰባቸውን በተሻለ ሁኔታ እንደሚገነዘቡ በማንሳትም ሐሳቡን የሚደግፉ አሉ።

  2. ጋና የገዛችው የ60 ሚሊዮን ዶላር ፕሬዚደንታዊ ጄት ቁጣ ቀሰቀሰ

    በ60 ሚሊዮን ዶላር የተገዛው ፕሬዚደንታዊ ጄት
    የምስሉ መግለጫ, ፈረንሳይ ሰራሹ ፋልኮን 6ኤክስ እያረጀ ያለውን የፕሬዚደንቱን ጄት እንደሚተካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል

    የጋና መንግሥት አዲስ የገዛው የ60 ሚሊዮን ዶላር ፕሬዚደንታዊ ጄት ሕዝባዊ ቁጣ ቀሰቀሰ።

    መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበትን ፕሬዚደንታዊ ጄት የገዛው በርካታ ዜጎች በኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ባለበት ወቅት ነው።

    60 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ፈረንሳይ ሰራሹ 'ፋልኮን 6ኤክስ' ፖለቲካዊ ውዝግቦችን ያስከተለ ሲሆን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም "ቅድሚያ ለሚሰጠው ነገር ቅድሚያ ባለመስጠት" የፕሬዚደንት ጆን ማሃማን አስተዳደር ከስሰዋል።

    ሆኖም መንግሥት እያደገ የመጣው የአገሪቷ ኢኮኖሚ እየተሻሻለ በመምጣቱ የጄቱ ዋጋ ተመጣጠኝ መሆኑን እና እያረጀ የመጣውን የፕሬዚደንቱን ጄት ለመተካት በማስፈለጉ ግዥው በምክንያት የተፈፀመ መሆኑን አስረድቷል።

    ውዝግቡ የተከሰተው የማሃማ አስተዳደር ጋና ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም እርዳታ እንድትጠይቅ ያስገደዳትን እና ለዓመታት ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲያገግም ለማድረግ እየጣረ ባለበት ወቅት ነው።

    የጋና አየር ኃይል፣ የፈረንሳይ ኤርስፔስ ኩባንያ በሆነው ዳሶልት አቪየሽን የተመረተውን እና 60 ሚሊዮን ዶላር የወጣበትን አውሮፕላን ሰኞ ዕለት ተረክቧል።

    ፕሬዚደንታዊ አውሮፕላኑ የተገዛው ባለፈው ታኅሳስ ወር ምክር ቤቱ የአገሪቷን የጦር አውሮፕላኖች የማዘመን ሰፊ ፕሮግራም አካል አድርጎ ግዥውን ካፀደቀው በኋላ ነው። ይህም ከኤርባስ የተገዙ አራት ሄሊኮፕተሮችን ያካትታል።

    ጋና ጄቱን ሰኞ እለት የተረከበች ቢሆንም የተገዛበት ወቅት እና ዋጋን በተመለከተ በኦንላይን እና በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዘንድ ትችትን አስከትሏል።

    አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ለአውሮፕላኑ የወጣው ገንዘብ በሌሎች ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ነገሮች ላይ መዋል ነበረበት ብለዋል።

    አንድ የኤክስ ተጠቃሚ “ገንዘቡ ከ100 ሺህ በላይ ነርሶችን እና 200 ሺህ መምህራንን መቅጠር ይችላል” ብሏል።

    መንግሥት በበኩሉ የጋና የኢኮኖሚ ሁኔታ ጥሩ መሻሻል አሳይቷል ሲል ትችቱን ውድቅ አድርጓል።

    • ተያያዥ ዜና፡
  3. በሱዳን ጦርነት በዚህ ዓመት ብቻ 2 ሺህ 230 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል - ተመድ

    የድሮን ጥቃት እንደደረሰበት የተገለጸው የገበያ ሥፍራ
    የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ጥቅምት ወር በአቢዬ ግዛት በገበያ ሥፍራ የድሮን ጥቃት መድረሱ ከተገለፀ በኋላ የአካባቢ ባለሥልጣናት አካባቢውን ጎብኝተዋል

    በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት በዚህ ዓመት ብቻ 2 ሺህ 230 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንዳረጋጋጠ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታወቀ።

    ከእነዚህ መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት የተገደሉት በድሮን ጥቃቶች መሆኑን ገልጿል። ይህም “የግጭቱ መገለጫ ባህሪ እየሆነ መጥቷል” ብሏል።

    የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ተርክ “ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የጦርነት ሕጎችን ችላ ማለታቸውን” አውግዘው፤ ይህም የጦር ወንጀል ሆኖ ሊቆጠር እንደሚችል ተናግረዋል።

    በሱዳን መንግሥት ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ከሦስት ዓመት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን እልባት ያላገኘ ሲሆን በዓለም አስከፊ ከሆኑ ሰብዓዊ ቀውሶችን አንዱን አስከትሏል።

    እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ከቅርብ ወራት ወዲህ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የድሮን ጥቃቶችን ፈፅመዋል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ከባለፈው ዓመት ጥር እስከ ሰኔ ወር ያሉትን ጊዜያት በሚሸፍነው ሪፖርቱ “በሱዳን እየጨመሩ የመጡት የድሮን ጥቃቶች የግጭቱን ገፅታዎች የሚያሳዩ ናቸው፤ ተፋላሚዎቹ ከጦር ግንባሮች እና በቁጥጥራቸው ሥር ካሉ ቦታዎች ርቀው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል” ብሏል ።

    ድርጅቱ ከሪፖርቱ ጋር አብሮ ባወጣው መግለጫውም በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 2 ሺህ 230 ከፍ ማለቱን እና ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 630ዎቹ የተገደሉት በድሮን ጥቃቶች መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል። ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም አመልክቷል።

    በግጭቱ በቀጥታ ከተገደሉት በተጨማሪ የኃይል እና የውሃ መሠረተ ልማቶች የድሮን ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸው እየጨመረ መምጣቱንም ሪፖርቱ አክሏል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  4. የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ 19 ሰዎች ሞቱ

    አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ያለውን ቅጽበት የሚያሳዩ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ
    የምስሉ መግለጫ, አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ያለውን ቅጽበት የሚያሳዩ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ

    የሩሲያ ወታደራዊ የመጓጓዣ አውሮፕላን በሳይቤርያ ተከስክሶ ሁሉም 19 ተሳፋሪዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ ዘገበ።

    የሩሲያ መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ኤኤን-12 የተባለው ወታደራዊ አውሮፕላን በኬሜሮቮ ግዛት “ሰዎች በማይኖሩበት አካባቢ የታቀደ በረራ” ሲያካሂድ አደጋው ተከስቷል።

    አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፤ ትክክለኛውን መንስዔ ለማወቅ የሩሲያ አቪዬሽን ባለሥልጣን ምርመራ ከፍቷል።

    የአካባቢው አገረ ገዢ ኢላያ ሴርዴዩክ የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞች ተሰማርተው “በፍጥነት እሳቱን እንዳጠፉ” ተናግረዋል።

    አደጋው የተከሰተው ያጉኖቮ በተባለ መንደር ሲሆን ፖሊስ በአካባቢው እንቅስቃሴን እንዳይደረግ አግዷል።

    አገረ ገዢው እንዳሉት አሁን ላይ ዋነኛው ሥራ ለሚካሄደው ምርመራ ድጋፍ መስጠት ነው።

    የእሳት አደጋ ሠራተኞች ሥራቸውን ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችንም አጋርተዋል።

    አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ያለውን ቅጽበት የሚያሳዩ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ።

  5. በዌስት ባንክ የ72 ዓመት ፍልስጤማዊት በእስራኤል ሰፋሪዎች መገደሏ ተገለጸ

    የሚያለቅሱ ሴቶች
    የምስሉ መግለጫ, የፋዳ አል ፋሂዳ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማክሰኞ ዕለት በአከል ዱዩክ አል ታህታ መንደር ተፈጽሟል

    በእስራኤል በኃይል በተያዘው እና በቅርቡ የእስራኤል ሰፋሪዎች በገቡበት የዌስት ባንክ መንደር ውስጥ በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ አንዲት ሴት መገደሏን እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ክስተቱን በተመለከተ ከሁለቱም ወገን የሚወጡ መረጃዎች የተለያዩ ናቸው።

    በአካባቢው የሚኖሩ ፍልስጤማውያን፣ በፍልስጤም ባለሥልጣናት ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ጀሪቾ አቅራቢያ በሚገኘው አል ዱዩክ አልታህታ ሰፋሪዎቹ ጥቃት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ የፍልስጤም መኪና የእስራኤል ተሽከርካሪን በመግጨት ጥቃት መፈፀሙን ገልጿል።

    ከዚያም በምላሹ ተኩስ በከፈተው እስራኤላዊ ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን አስረድቷል። ሆኖም ጦሩ ተተኩሶባቸው የተገደሉትን ሴት በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

    በአካባቢው የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እንዳሉት ግን ሰኞ ምሽት የተፈፀመው ጥቃት የደረሰው እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በጀመሩት ትንኮሳ ነው።

    ፍልስጤማውያን ሕፃናት ድንጋይ መወርወር ጀመሩ ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ከዚያም ሰፋሪዎቹ ተኩስ መክፈታቸውን እና በቤታቸው ደጅ ላይ የነበሩ ፋዳ አል ፋሂዳ የተባሉ የ72 ዓመት ሴት መገደላቸውን ተናግረዋል።

    የሟች የልጃቸው ሚስት የሆነችው ኔማ አል ፋሂዳ፣ ፋዳ ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመትተው መሞታቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

    በቅርቡ በዌስት ባንክ በሚገኝ አዲስ አካባቢ እስራኤላውያን መስፈራቸውን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።

    ሰፋሪዎቹ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት "ምስጢራዊ" ባሉት ዘመቻ በመንደሯ የሚገኙ ስምንት ቤቶችን ገዝተው ገብተዋል።

    መኖሪያ ቤቶቹ የእስራኤል ኃይሎች ሙሉ ቁጥጥር በሚያደርጉበት አካባቢ የሚገኙ ናቸው።

    በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እስራኤል የምታካሂደው ሁሉም ሰፈራ ሕገ ወጥ ነው።

    • ተያያዥ ዜናዎች፡
  6. ለትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ የአሜሪካ አምባሳደር ገለጹ

    ማሲንጋ

    በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ፣ አሜሪካ በትግራይ ክልል ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ እና በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ የወደፊት ግንባታን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

    አምባሳደር ማሲንጋ፣ ከሌሎች አምባሳደሮች እና ከተባበሩት መንግስታት ልዕኡካን እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰኞ ኅዳር 8/ 2019 ዓ.ም. በመቀለ ባደረጉት የጋራ ጉብኝት ከክልሉ አመራሮች እና ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

    የኤምባሲው ድረ ገጽ ላይ ውይይቱን በተመለከተ በወጣው መግለጫ፣ በውይይቱ ወቅት አምባሳደሩ “መረጋጋት፣ አካታችነት እና ጠንካራ ተቋማት ለሁሉም የትግራይ ሕዝብ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይሎች ናቸው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

    እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ለክልሉ ነዋሪዎች የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለማስፋት እና ሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍሎች ከዕድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስፈላጊ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።

    አምባሳደር ማሲንጋ በተለይም በቀጣይነት በክልሉ በሚታየው ድርቅ የተጎዱ ማኅበረሰቦች ሕይወት አድን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማረጋገጥ አሜሪካ ያላትን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

    አምባሳደሩ አክለውም አሜሪካ ከትግራይ ሕዝብ፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ትግራይ እና መላው ሰሜን ኢትዮጵያ ወደ መረጋጋት እና እድገት እንዲሸጋገሩ ለመደገፍ እንደምትሠራ ገልጸዋል።

    በተለይም ክልሉ ከገጠሙት ችግሮች በማገገም ወደ ልማት እንዲመለስ “ከክልሉ ሕዝብ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ ነን” በማለት የአሜሪካ መንግሥትን አቋም አስታውቀዋል።

    የፌዴራል መንግሥት መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከተማዋ በገባው በዚህ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ውስጥ፣ ከአሜሪካ አምባሳደር በተጨማሪ ከስምንት ሀገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካተታቸው ተዘግቧል።

    የጉዞው ዋና ዓላማ በትግራይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በአካል ለመመልከትና በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ነው ተብሏል።

    በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ጦርነት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ የአሜሪካ ኤምባሲ ሁለቱ ኃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ ሲያሳስብ የቆየ ሲሆን፣ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋም በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፣ የህወሓት መሪዎች “መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመክፈት ባሳለፉት ደካማ ውሳኔ ማዘናቸውን” ገልጸው ነበር።

    አክለውም “ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ብልህ እንዲሆኑ” በመምከር፣ አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደተሳሳተ መንገድ ለመምራት የሚሞክሩ ተጨማሪ አመራሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል አማራጩ እንዳላት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

  7. ትራምፕ ቻይና ከመግባታቸው አስቀድሞ ፑቲን እና ዢ ውይይት ጀመሩ

    ዢ ጂንፒንግ፣ ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን
    የምስሉ መግለጫ, ዢ ጂንፒንግ፣ ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቻይና የሚካሄደውን የእስያ ጉባዔ ለመታደም ሸንዘን ገብተዋል።

    በጉባዔው ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግም ይገኛሉ።

    የኒውክሌር መሣሪያ ትጥቅ መቀነስን በተመለከተ የሦስትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

    ትራምፕ ቻይና ከመግባታቸው አስቀድሞ ፑቲን እና ዢ ውይይት ማድረግ ጀምረዋል።

    ሰኞ ዕለት ወደ ቻይና የሚያደርጉትን ጉዞ የጀመሩት ትራምፕ እግረ መንገዳቸውን ትናንት ፊሊፒንስ ገብተው ሌላ ጉባዔ እየታደሙ የሚገኙ ሲሆን ዛሬ ቻይና ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ትራምፕ በፊሊፒንሱ ጉባዔ ላይ ከሕንድ እና አውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር ተገናኝተዋል።

    የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁንየር የእስያ አገራት መሪዎች ለትራምፕ ተምሳሌታዊ “ድል” እንዳቀዳጁ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ መሪዎች የሦስዮሽ ውይይት ሲያደርጉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

    ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ውይይት እንዲደረግ መጠየቃቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር የኒውክሌር መሣሪያ ትጥቅን ለመቀነስ የሦስትዮሽ ውይይትን እንደሚደግፉ ጠቁመዋል።

    “ስለ ብዙ ጉዳዮች” እንደሚወያዩ የተናገሩት ትራምፕ “የኢራንን ጦርነት ለማስቆም እየሞከርን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

    መሪዎቹ የኢራን እና የዩክሬንን ጦርነት ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩም ዋይት ሃውስ ቀደም ብሎ አስታውቋል።

    በቻይና በኩል ስለ ውይይቱ አጀንዳዎች ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም።

  8. የኅዳር 9 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የማክሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።