የአውሮፓ ኅብረት የ12 የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶች በግዛቱ እንዳይበሩ አገደ

የፎቶው ባለመብት, Eritrean Airlines
የአውሮፓ ኅብረት ከአቪዬሽን ደኅንነት ጋር በተያያዘ የ12 የአፍሪካ አገራት ንብረት የሆኑ በርካታ አየር መንገዶች በአህጉሪቱ ውስጥ እንዳይበሩ ከለከለ።
አየር መንገዳቸው ላይ ክልከላ ከተጣለባቸው አገራት መካከል ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲ እና ታንዛኒያ ይገኙበታል።
በዚህ ውሳኔ መሠረት የሊቢያ፣ የአንጎላ፣ የኮንጎ-ብራዛቪል፣ የዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ የኦኳቶሪያል ጊኒ፣ የላይቤሪያ፣ የሳኦ ቶሚ እና ፕሪንሲፒ እንዲሁም የሴራሊዮን አየር መንገዶች በሙሉ ወደ አውሮፓ ከመብረር ታግደዋል።
ይህንን ተከትሎም፣ በአገራቱ ውስጥ የሚገኙ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አየር መንገዶች በሙሉ ከበረራ ታግደዋል። ከእነዚህም መካከል ታንዛኒ 34፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ 13፣ ሱዳን 12፣ ሊቢያ 10 አየር መንገዶች ታግደውባቸዋል።
ዕገዳው በአንዳንድ አገራት ላይ ሙሉ ለሙሉ የሚጣል ሲሆን በሌሎች ላይ ደግሞ በተወሰኑ አየር መንገዶች ላይ ብቻ ተግባራዊ የሚሆን ነው። ሙሉ ዕገዳ ከተጣለባቸው 12 አገራት በተጨማሪ በስም የተጠቀሱ የአልጄሪያ እና የዚምባብዌ አየር መንገዶች በተናጠል ታግደዋል።
በአውሮፓ ኅብረት የአየር ትራንስፖርት ደኅንነት ግምገማ መሠረት በ12 የአፍሪካ አገራት ላይ ሙሉ ለሙሉ እና በተወሰኑ አገራት በተናጠል በአየር መንገዶች ላይ በተጣለው እገዳ ምክንያት 89 የሚደርሱ የአፍሪካ አገራት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ታግደዋል።
ይህ ዓይነቱ አውሮፓ የአየር መንገዶች ምዘና እና ፈቃድ አሠራር የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2006 ነው። በዚህ አሠራር ከታገዱ በኋላ መመዘኛውን የሚያሟሉ አየር መንገዶች የመብረር ፈቃድ ሊያገኙ ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock















