የኤአይ ኩባንያው አንትሮፒክ አክሲዮን በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ክብረ ወሰን ያዘ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ክላውድ የተባለውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መገልገያ ባለቤት የሆነው ኩባንያ አንትሮፒክ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአክሲዮን ገበያ ያቀረበው ድርሻ 81 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ክብረ ወሰን ሰበረ።
ይህም አንትሮፒክ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ውድ ኩባንያዎች አንዱ አድርጎታል።
የዚህን ኩባንያ አክሲዮን ለመግዛት የባለሀብቶች ፍላጎት በእጅጉ በመጨመሩ፣ መጀመሪያ ከታቀደው በላይ አክሲዮኖች ተሽጠዋል። የአክሲዮኑ ዋጋም ከተገመተው ከ70 እስከ 78 ዶላር የሚደርስ ዋጋ ከፍ ብሎ 83 ዶላር ደርሷል።
አክሲዮኖቹ ሐሙስ በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ላይ ግብይት የሚሸጡ ሲሆን፣ ይህም ዕድሜው አምስት ዓመት ብቻ የሆነውን ኩባንያ በ1.5 ትሪሊዮን ዶላር ያህል ዋጋ እንዲገመት ያደርገዋል።
ይህ የአክሲዮን ሽያጭ በፍጥነት እያደገ ላለው የኤአይ ዘርፍ ወሳኝ የመፈተሻ አማራጭ ይሆናል ተብሎ ተወስዷል።
አንትሮፒክ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ብቻ የተመሠረተ ኩባንያ ሆኖ አክሲዮኑን ለሕዝብ የሸጠ የመጀመሪያው ድርጅት ነው።
በኤኤይ መሠረተ ልማቶች እና የኤኤይ መሣሪያዎች ልማት ውስጥ እጅግ ብዙ ገንዘብ በዓለም ዙሪያ ውጪ ተደርጓል። ሆኖም እነዚህ መዋዕለ ንዋዮች መቼ እና እንዴት ትርፍ ማስገኘት እንደሚጀምሩ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ለመሳብ በቻለው ከፍተኛ የአክሲዮን ሽያጭ ምክንያት አንትሮፒክን በአውሮፓውያኑ 2021 ያቋቋሙት ሰባቱ መሥራቾች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ያላቸው ሰዎች ለመሆን ችለዋል።


















