ትራምፕ፣ ዢ እና ፑቲን ዛሬ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ በአካል ስብሰባ ሊያደርጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ፣ የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው ዢ ጂንፒንግ ዛሬ ሐሙስ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ በአካል የሦስትዮሽ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የሩሲያ አቻቸው ፑቲን በእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ (ኤፔክ) ለመሳተፍ በደቡባዊ ቻይና ሼንዘን ከተማ ይገኛሉ። አስተናጋጃቸውም የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ናቸው።
የእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ በመካሄድ ላይ ሲሆን የዚህ ጉባኤ ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር የሆነው የሦስቱ መሪዎች ስብሰባ በሰዓታት ውስጥ እንደሚጀመር ይጠበቃል። የአሜሪካ፣ የሩሲያ እና የቻይና ፕሬዝዳንቶች በአካል ተገናኝተው ውይይት ሲያደርጉ ይህ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ረቡዕ ሼንዘን አየር ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ዢ በፈገግታ ተቀብለዋቸዋል። የቻይና መሪ እንግዶችን በአየር ማረፊያ ተገኝተው ሲቀበሉ ማየት እጅጉን ያልተለመደ ነገር ነው።
አንድ የውጭ አገር መሪ እንዲህ ዓይነት አቀባበል ሲደረግለትም ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ይታመናል። ቀጥሎም ትራምፕ ከፑቲን ጋር ሰላምታ የተለዋወጡ ሲሆን ሦስቱ መሪዎች ሲጨባበጡ የሚያሳዩ ፎቶዎች ወጥተዋል።
መሪዎቹ የሚያደርጉት የሦስትዮሽ ስብሰባው በምን ጉዳይ ላይ እንደሚተኩር እስካሁን በትክክል አልታወቀም።
ስብሰባው የሚካሄደው ‘ካይሊን ቪላ’ ተብሎ በሚጠራው ታዋቂ ስፍራ እንደሚሆን ተገምቷል። በአውሮፓውያኑ 1997 የተከፈተው እና በመንግሥት የሚተዳደረው ይህ ግቢ የቻይና እና የውጭ አገራት መሪዎችን የማስተናገድ ረጅም ታሪክ አለው።
ቻይና ከመደበኛ የስብሰባ አዳራሽ ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ስፍራ መምረጧ ውይይቱ “ራሱ የቻለ ትልቅ ስብሰባ ሳይሆን ከጉባኤው ጎን ለጎን የሚደረግ ውይይት” መሆኑን እንደሚጠቁም በዴፖል ዩኒቨርሲቲ የመሪዎች ጉባኤ ዲፕሎማሲ ባለሙያ የሆኑት ሚንሴዮን ኩ ተናግረዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት “ዢ ይህንን ይፈልጋሉ፤ ምክንያቱም ቻይና የኤፔክ አስተናጋጅ በመሆኗ የእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ ዋናው ኹነት እንዲሆን እንጂ በሦስትዮሽ ስብሰባው እንዲጋረድ አትፈልግም” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሦስቱ ልዕለ ኃያላን አገራት ባሻገር፣ ከመላው ዓለም የተውጣጡ መሪዎችም በኤፔክ ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል፤ ተከታታይ ስብሰባዎችንም እያደረጉ ነው።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ አገራቸው አሜሪካ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ከእስያ አገራት ጋር የንግድ ስምምነቶችን እየተፈራረሙ ነው።
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ ደግሞ አገራቸው ከቤጂንግ ጋር ግንኙነቷ ከተቀዛቀዘ ወዲህ በቻይና የመጀመሪያውን ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው።
ተያያዥ ዘገባዎች፦










