የዩክሬንን የሚደግፈውን የአሜሪካ መከላከያ ኩባንያ በመሰለል የተጠረጠረ ሩሲያዊ በቁጥጥር ሥር ዋለ
ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ በሚሰጥ አንድ የቴክኖሎጂ እና የመከላከያ ኩባንያ ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችን ለመሰለል በመሞከር የተጠረጠረ ሩሲያዊ በካሊፎርኒያ ሲልከን ቫሊ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ።
ኢጎር ዲዩ የተባለው ግለሰብ በሳን ፍራንሲስኮ አቅራቢያ በምትገኘው ፓሎ አልቶ ከተማ ድብቅ የስለላ ዘመቻ ለማካሄድ የውጭ መንግስት ወኪል ሆኖ በመስራት ተከሷል። በስለላው ዒላማ ተደርጎ የነበረው ኩባንያ ‘ፓላንቲር ቴክኖሎጂስ’ እንደሆነ ቢቢሲ ተገንዝቧል።
ዲዩ በተጨማሪም ሠራተኞችን በመከታተል እና የሐሰት የመታወቂያ ሰነዶችን በመያዝ ክስ ቀርቦበታል።
በክስ ሰነዱ ላይ የኩባንያው ስም አልተጠቀሰም። ይሁን እንጂ፣ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት የምትጠቀምበትን ሶፍትዌር የሚያመርት እንዲሁም በአክሲዮን ገበያ ላይ የሚገበያይ የቴክኖሎጂ እና መከላከያ ኩባንያ ተብሎ ተገልጿል።
የሰሜን ካሊፎርኒያ ዲስትሪክት የአሜሪካ አቃቤ ህግ ክሬግ ሚሳኪያን “የቀረቡት ክሶች ኩባንያው ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታካሂደው ጦርነት እገዛ በማድረጉ ምክንያት የአሜሪካ የቴክኖሎጂ እና መከላከያ ኩባንያ ሠራተኞችን ዒላማ ለማድረግ እና ለማዋከብ በመንግሥት የተደገፈ ዘመቻ መኖሩን ያሳያሉ” ብለዋል።
አሰሪዎቹ ሩሲያን “’እናት አገር’ እያሉ ይጠሯት የነበረ ሲሆን፣ ኩባንያው በዩክሬን በሩሲያ ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሳሪያዎችን ያቀርብ ስለነበር ስለ ኩባንያው መረጃ እንዲሰበስብ መመሪያ ሰጥተውት ነበር” ተብሏል።
በዘርፉ ያሉ አንድ ምንጭ ዒላማ የተደረገው ፓላንቲር መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ዘመቻው ግን የኩባንያውን የግል ሲስተሞች ሰብሮ መግባት አለመቻሉን ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት እኚህ ምንጭ፣ አንድ የሩሲያ ሰላይ በአሜሪካ ምድር ተገኝቶ ኩባንያውን ለመሰለል ሲሞክር ሲያዝ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል።
ፓላንቲር በቀረቡት ክሶች ዙሪያ እስካሁን ምንም አይነት መግለጫ አልሰጠም።
ተያያዥ ዘገባ፦