አሜሪካ የኢራንን ደሴት መደብደቧን ተከትሎ ኩዌት ከሁለት ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት ተሰነዘረባት
የኢራን እና አሜሪካ ፍጥጫ መካረሩን ተከትሎ፣ ኩዌት እና ባህሬን ማክሰኞ ሌሊት ከቴህራን የተሰነዘሩባቸውን የአየር ጥቃቶችን መመከታቸውን አስታወቁ።
ኩዌት በኢራን የድሮን ጥቃት የደረሰባት ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሁለቱ አገራት ጥቃት የተፈጸመባቸው፣ የአሜሪካ የጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚገኘው የቀሽም ደሴት ላይ ያከን የኢራን ሚሳዔል ማስወንጨፊያ ከደበደበ በኋላ እንደሆነ የአሜሪካ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የኢራን ጦር በበኩሉ የአሜሪካ ኃይሎች የሚገኙበትን አሊ አል ሳሌም የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል። የኩዌት ባለሥልጣናት ግን ጉዳት ስለመድረሱ አልገለጹም።
የኩዌት ጦር ማክሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ የተሰነዘሩትን “የድሮን ስጋቶችን” መመከቱን እና በሰዎች ላይም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።
የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ጥቃቱን አውግዟል። ጥቃቱ “የኩዌትን ሉዓላዊነት በግልጽ የጣሰ፣ ደኅንነቷን እና መረጋጋቷን በቀጥታ አደጋ ላይ የጣለ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግን በከፍተኛ ሁኔታ የጣሰ ነው” ብሏል።
የባህሬን ጦር ደግሞ ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ አየር መከላከያ ስርዓቶች “በርካታ የኢራን የአየር ጥቃቶችን በአየር ላይ እንደጠለፉ እና እንዳወደሙ” አስታውቋል።
የአሜሪካ ባሕር ኃይል 5ኛ ፍሊት የሚገኝባት ባህሬን፣ ከሁለት ወራት ፋታ በኋላ ባለፉት ስድስት ቀናት ውስጥ አራት ጥቃቶች እንደተፈጸሙባት ገልጻለች።
በሌላ በኩል፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት ንብረት የሆነው የነዳጅ ኩባንያ ማክሰኞ ዕለት በባሕረ ሰላጤው ሲጓዝ በነበረ አንድ የነዳጅ ጫኝ መርከቡ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመበት አስታውቋል። በዚህ ጥቃት አንድ የመርከብ ሠራተኛ የደረሰበት አለመታወቁን ጠቅሷል።
ኢራን እና አሜሪካ የጥቃት ልውውጥ ውስጥ መግባታቸው እንዲሁም በሚያደገጉት ድርድር ላይ ለውጥ አለመታየቱ፣ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት ወደ ከፋ ደረጃ ሊያድግ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ጦርነቱ የተጀመረው አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው የካቲት መጨረሻ ላይ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።
በሁለቱ አገራት የተደበደበችው ኢራን፣ እስራኤል ላይ እንዲሁም የአሜሪካ ወታደራዊ ንብረቶችን እና ሠራተኞችን በሚያስተናግዱ የባሕረ ሰላጤው አረብ ሀገራት ላይ የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።