በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ፣ አሜሪካ በትግራይ ክልል ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ እና በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ የወደፊት ግንባታን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ፣ ከሌሎች አምባሳደሮች እና ከተባበሩት መንግስታት ልዕኡካን እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰኞ ኅዳር 8/ 2019 ዓ.ም. በመቀለ ባደረጉት የጋራ ጉብኝት ከክልሉ አመራሮች እና ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
የኤምባሲው ድረ ገጽ ላይ ውይይቱን በተመለከተ በወጣው መግለጫ፣ በውይይቱ ወቅት አምባሳደሩ “መረጋጋት፣ አካታችነት እና ጠንካራ ተቋማት ለሁሉም የትግራይ ሕዝብ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይሎች ናቸው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ለክልሉ ነዋሪዎች የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለማስፋት እና ሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍሎች ከዕድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስፈላጊ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ በተለይም በቀጣይነት በክልሉ በሚታየው ድርቅ የተጎዱ ማኅበረሰቦች ሕይወት አድን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማረጋገጥ አሜሪካ ያላትን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።
አምባሳደሩ አክለውም አሜሪካ ከትግራይ ሕዝብ፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ትግራይ እና መላው ሰሜን ኢትዮጵያ ወደ መረጋጋት እና እድገት እንዲሸጋገሩ ለመደገፍ እንደምትሠራ ገልጸዋል።
በተለይም ክልሉ ከገጠሙት ችግሮች በማገገም ወደ ልማት እንዲመለስ “ከክልሉ ሕዝብ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ ነን” በማለት የአሜሪካ መንግሥትን አቋም አስታውቀዋል።
የፌዴራል መንግሥት መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከተማዋ በገባው በዚህ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ውስጥ፣ ከአሜሪካ አምባሳደር በተጨማሪ ከስምንት ሀገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካተታቸው ተዘግቧል።
የጉዞው ዋና ዓላማ በትግራይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በአካል ለመመልከትና በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ነው ተብሏል።
በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ጦርነት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ የአሜሪካ ኤምባሲ ሁለቱ ኃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ ሲያሳስብ የቆየ ሲሆን፣ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋም በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፣ የህወሓት መሪዎች “መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመክፈት ባሳለፉት ደካማ ውሳኔ ማዘናቸውን” ገልጸው ነበር።
አክለውም
“ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ብልህ እንዲሆኑ” በመምከር፣ አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደተሳሳተ መንገድ ለመምራት የሚሞክሩ ተጨማሪ አመራሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል አማራጩ እንዳላት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።