ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምሥራቅ አርሲ ሦስት ወረዳዎች በነዋሪዎች እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሰው ምንድን ነው?
በምሥራቅ አርሲ ዞን ሁለት ወረዳዎች እሁድ እና ሰኞ ዕለት በተፈጸሙ ጥቃቶች 13 ሰዎች መገደላቸውን እና አንድ ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን ነዋሪዎች እና የአካባቢው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገረ ስብከት ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
የአካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን ስም ዝርዝር ይፋ ደያረጉ ሲሆን፣ የአካባቢው አስተዳደር ባለሥልጣናት ደግሞ ስለተፈጸመው ጥቃት እና ስለደረሰው ጉዳት መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በምሥራቅ አርሲ አገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ የቢቢሲ ምንጭ ጥቃቱ እሁድ ግንቦት 23/2018 ዓ.ም. መጀመሩን ተናግረው ስልጣና ወረዳ ልዩ ስሙ በቼቶ በተባለ አካባቢ ሁለት፣ አሰኮ ወረዳ ደግሞ 11 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
እኚሁ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የቢቢሲ ምንጭ በጥቃቱ የ101 ዓመት እድሜ ያለው "ጠለታ ገብርኤል" ቤተ ከርስቲያን ሙሉ በሙሉ በእሳት ወድሟል ብለዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት የአርሲ እና ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ባወጡት መግለጫ በምሥራቅ አርሲ አገረ ስብከት በአሰኮ፣ በሺርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች "13 ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸውን፣ ከ280 በላይ ምእመናን መፈናቀላቸውን እና የ101 ዓመት ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን" አመልክተዋል።
በተጨማሪም ካራ ኩፍተና መድኃኔ ዓለም በተባለው ቤተ ክርስቲያን ላይ "ዘረፋ" መፈጸሙን የገለጹት ጳጳሱ "ምእመናን ጽላቱን ይዘው ተሰደዋል፤ መኖሪያ ቤታቸውም ተቃጥሏል" ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በአካባቢው ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች "በሃይማኖታቸው ብቻ ቤታቸው እየተለየ ተቃጥሏል፤ ንብረታቸው እና ከብቶቻቸው ተዘርፈዋል" ሲሉም አስታውቀዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በአካባቢው የቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው በጥቃቱ ሚኒሻ የነበረው ወንድማቸው መገደሉን ገልጸው "ቤተክርስቲያኑ [ጠለታ ገብርኤል] ከታቦተ ሕጉ ውጪ ሙሉ በሙሉ ወድሟል" ብለዋል።
የአገረ ስብከቱ ምንጭ ግንቦት 23/2018 በነበረ ጥቃት ደጀሰላሙ ተቃጥሎ የነበረው ኩፍቴና መድሃኒዓለምን ግንቦት 24 ለ25 አጥቢያ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መቃጠሉን ጨምረው ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተገደሉት ሟቾቹ ነዋሪዎች መሆናቸውን የተናገሩት እኚህ ግለሰብ በአሰኮ ወረዳ 280 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
ቢቢሲ በደረሰው ጥቃት ላይ መረጃ ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ እና የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አራርሳ መርዳሳ በተደጋጋሚ ቢደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ የአርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ሶሪ ወጊን ስለተፈጸመው ጥቃት ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ላቀረበላቸው ጥያቄ "እስከአሁን የደረሰን መረጃ የለም፤ እናጣራለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው አካበቢዎች አንዱ የሆነው የሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ አስተዳዳሪ ሐሰን መሐመድም ሰዎች ስለሞቱበት እና ንብረት ስለወደመበት ክስተት "መረጃ የለንም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከጥቃቱ ጋር ስሙ እየተነሳ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት የቡድኑ ቃል አቀባይ መሆናቸውን የሚገልጹት ጂሬኛ አያና ምላሽ እንዲሰጡ ቢቢሲ በጽሑፍ መልዕክት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ዘገባው እስከወጣበት ጊዜ መልስ አልሰጡም።
የምሥራቅ አርሲ አገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ከፍያለው ሸንቁጤ "እዚያ አካባቢ ትንሽ እርስ በርስ አለመስማማት አለ" በማለት ግድያዎች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሰኞ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ምርጫ መካሄዱን በማስታወስ በእነዚህ አካባቢዎች "እርስ በርስ መጨራረስ" የተደረሰው "ምርጫውን ለማደናቀፍ ይሁን ወይም ሌላ ምክንያት ስለመኖሩ አለመታወቁን" ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ጥቃቱ የተፈጸመው በምን ምክንያት እና በማን እንደሆነ ለይቶ ለመናገር አሁን እንደማይችሉ ጨምረው አስታውቀዋል።
በአካባቢው የፀጥታ አካላት እና የሚያጣራ ቡድን ማክሰኞ ዕለት ግንቦት 25/2018 ዓ.ም. መሰማራቱን ተናግረው ሁኔታዎች መረጋጋታቸውን ገልጸዋል።
በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን በተመለከተም "ግማሹ ዘጠኝ ይላል፤ ግማሹ ሰባት ይላል ይሄም ራሱ መጣራት አለበት" ብለዋል።
በአካባቢው ግንቦት 23 እና 24 የተኩስ እሩምታ እንደተከፈተ ጥቆማ እንደደረሰባቸው መረጃው እንዳላቸው የሚናገሩት ኃላፊው አንድ ቤተክርስቲያን ላይ "ትንሽ የእሳት አደጋ" መድረሱን በመግለጽ ይህንንም ወደ ቦታው የተሰማራው ቡድን አጣርቶ እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል።
የተፈጠረውን በዝርዝር ለማስረዳት አጣሪ ቡድኑ የሚያመጣውን መረጃ አይተው ለመናገር እንደሚመርጡ በመግለጽ ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።
የቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ግለሰብ በበኩላቸው በአካባቢው ባለፉት ስድስት ዓመታት "በሸኔ ታጣቂዎች" ጥቃት በተደጋጋሚ ሲፈጸም እንደነበር ገልጸው፤ የተወሰኑ ግለሰቦች ራሳቸውን ለመከላከል "በግላቸው መታጠቃቸውን" ይናገራሉ።
የተወሰኑ ሰዎች ከታጣቂዎቹ ጋር ሲታኮሱ ቀሪዎቹ ግን እየሸሹ ባሉበት መገደላቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ከተገደሉት መካከል "አስከሬናቸው ተነሰቶ ያልተቀበረ አለ" ያሉት የቤተክርስቲያኑ አገልጋይ ቀሪዎቹ ግን በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በጅምላ መቀበራቸውን ተናግረዋል።
ግንቦት 23 እና ግንቦት 24 በነበረው ጥቃት ከአድማ በታኝ፣ ከሚሊሻ እንዲሁም ሙስሊም ከሆኑ የአካበቢው ነዋሪዎች የተገደሉ መኖራቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በምሥራቅ አርሲ በሽርካ ወረዳ ግንቦት 23/2018 ምሽት በአንድ ቤት ይኖሩ የነበሩ ሁለት የእህትማማች ልጆች በጥቃት አድርሾቹ ከተወሰዱ በኋላ ተገድለው መገኘታቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል።
የሟቾቹ ንብረት እና ከብቶች መዘረፋቸውን በመግለጽ አስር ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ሚታና ጋዶ የሚባል አካባቢ "ገድለው ጥለዋቸው ሄደዋል" ብለዋል።
አንደኛው ግለሰብ "ሰቅጣጭ በሆነ ሁኔታ" መገደሉን የሚናገሩት ነዋሪው የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. ጋዶ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን መፈጸሙን ተናግረዋል።
የሟቾቹ ግለሰብ ወንድም ከሳምንት በፊት ታግቶ መወሰዱን የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ እስካሁን የደረሰበት አለመታወቁን ተናግረዋል።
ግለሰቦቹ በማን ተይዘው እንደተወሰዱ እና እንደተገደሉ ሲጠየቁ "ይሄ የተለመደ ነው፤ በአካባቢው ሸኔ ተብሎ የሚጠራ ቡድን እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል። ከዚህ በፊትም ተከታታይ እገታዎችን እና ግድያዎችን ይፈጽማል" ብለዋል።
ከዚህ በፊትም የተፈጸሙት ግድያዎች "እምነት ተኮር" መሆናቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ "አሁንም በዚያው መልኩ የተፈጸመ" መሆኑን አስረድተዋል።
በአካባቢው ባለፉት ሦስት ዓመታት ተመሳሳይ ግድያዎች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን የሚያስታውሱት ነዋሪው "በርካታ ሰው ሕይወቱን አጥቷል" ይላሉ።
በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ማፈናቀሎች "እምነት ተኮር" በመሆናቸው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።
እነዚህ ተመሳሳይ ጥቃቶች "እልባት ያላገኙት" ለምን እንደሆነ ሲናገሩም "በአካባቢው አስተዳደር ውስጥ ያልጠሩ ሁኔታዎች አሉ" ብለዋል።
በሽርካ ወረዳ ከ500 የማያንሱ አባዎራዎች ከዚህ በፊት በተፈጸሙ ጥቃቶች መፈናቀላቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህ ችግር ከመፈጠሩ በፊት እነርሱን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ቢቢሲ በሽርካ ወረዳ ነዋሪን ያነጋገረው ማክሰኞ ግንቦት 25 ሲሆን የአካባቢው ሁኔታ መረጋጋቱን ሰምቷል።
ሌላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ የአሰኮ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው ግንቦት 23/2018 በነበረው ጥቃት "ሸኔ ተብለው የሚጠሩት" አንድ ሚሊሻን ጨምሮ አስር ሰው ገድለዋል ብለዋል።
በጥቃቱ ከ280 በላይ ነዋሪዎች መፈናላቸውን አንድ የ101 ዓመት ዕድሜ ያለውን ቤተክርስቲያን መቃጠሉን ተናግረዋል።
ግንቦት 23/2018 ዓ.ም. የተገደሉትን ነዋሪዎች ስም የሚዘረዝሩት እኚህ ግለሰብ ከ80 ዓመት እስከ 25 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ነዋሪዎች በቤታቸው ውስጥ ሳሉ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ተገድለዋል ብለዋል።
አማረ በላይነህ እና ተሬ ደሴ የሚባሉት ግለሰቦች ግንቦት ሰኞ 24/2018 ዓ.ም. መገደላቸውን ተናግረው በዕለቱም መኖሪያ ቤቶችን እያቃጠሉ እንደነበር ተናግረዋል።
"የክርስቲያን ቤት ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል" ያሉት ነዋሪው እሁድ ግንቦት 23 ከጠዋት ጀምሮ ጥቃቱ መፈጸሙን ተናግረው ሰኞ ዕለትም መቀጠሉን እና በአካባቢው "የሸኔ ባንዲራ" ተክለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ግንቦት 23/2018 ዓ.ም. በድንገት ወደ አካባቢው መጥተው መተኮስ እና ቤቶችን ማቃጠል መጀመራቸውን የሚናገሩት ነዋሪው፣ "በቤታቸው የተገኙትን እየገደሉ፣ የሸሹትን ቤታቸውን እያቃጠሉ ሄደዋል" ብለዋል።
280 አባወራዎች መፈናቀላቸውን የሚገልጹት እኚህ ነዋሪው እነዚህ ሁሉ ቤት መካከል የምን ያህሉ እንደተረፈ እንዳላወቁ እና የሟቾቹ ቀብር ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጽሟል ብለዋል።
የጥቃቱ መንስዔ "ሃይማኖት ተኮር" ነው የሚሉት እኚህ ግለሰብ እሁድ እና ሰኞ ግድያው እና ቃጠሎው ሲፈጸም ወደ አካባቢው የመንግሥት የፀጥታ አካላት እንዳልመጡም ጨምረው አስታውቀዋል።
ፀጥታ አካላት ግንቦት 25 ማክሰኞ ዕለት መድረሳቸውን ነገር ግን ቢቢሲ እስካነጋገራቸው ሰዓት ድረስ ምንም ዓይነት ተኩስም ሆነ ቦታውን ማስለቀቅ እንዳልተካሄደ ጨምረው አስታውቀዋል።
በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ላይ በአካባቢው በተፈጸመው ተመሳሳይ ጥቃት 12 ዓመት ልጃቸው በመገደሏ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በአዳማ የሚገኙ ሌላ ነዋሪ አሁን ሦስት መኖሪያ ቤታቸው መቃጠሉ እንደተነገራቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአካባቢው ጥቃት መፈጸም ከጀመረ ከአምስት ዓመት ያህል መሆኑን ያስታወሱት እኚህ ግለሰብ "ብንጮህም የሚሰማን የለም" ሲሉ በስጋት ሲኖሩ እንደነበር ተናግረዋል።
"ቤት ንብረታችን ወድሞ፣ ከብት ንብረቶቻችን ጠፍተው ባዶ እጃችንን ቀርተናል" የሚሉት እኚህ ግለሰብ "ቀድም ሲልም ሦስት ቤት ተቃጥሎብኝ ተመልሶ ተሠርቶ ነበር ከትናንት ወዲያ በነበረው ጥቃት ዳግመኛ ተቃጥሎብኛል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዳማ ዘበኝነት እና የጉልበት ሥራ ተቀጥረው ሰባት ልጆቻቸውን በየዘመዱ በትነው እየኖሩ መሆኑን የሚናገሩት ግለሰቡ "የ12 ዓመት ልጃችን ከተገደለች በኋላ ባለቤቴ ታማሚ ሆና እርሷን እያስታመምኩ ነው" ሲሉ ጨምረው አስረድተዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው አርሲ ዞን ውስጥ በሚገኙ ቦታዎች በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ጥቃቱ እምነትን መሠረት ደያረገ እና ዒላማ የተደረጉት ሰዎችን መኖሪያ፣ ንብረት እና አብያተክርስቲያን ጭምር ያወደመ መሂኑን ይናገራሉ።
በአርሲ ዞን በተመሳሳይ ስፍራዎች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑት ጥቃቶች በማን እንደሚፈጸሙ አስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።
የክልሉ እና የአካባቢው ባለሥልጣናትም በተደጋጋሚ ስለሚፈጸሙት ጥቃቶች እንዲሁም ስለፈጻሚዎቹ በተደጋጋሚ መረጃ እንደሌላቸው ይናገራሉ ወይም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይሆኑም።
በተደጋጋሚ በሚከሰቱት ጥቃቶች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዒላማ እንደሚሆኑ ነዋሪዎች ከመናገራቸው በተጨማሪ እነሱን ከጥቃቱ ለመታደግ የሞከሩ የአካበቢው ነዋሪ የሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ተዘግቧል።
ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ በአካባቢው በተፈጸመ ጥቃት 25 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በምእመናኖቹ ላይ የሚፈጸመው ጥተት እየተባባሰ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት እንዲያስከብር መጠየቁ ይታወሳል።