ጋዜጠኞች ምርጫውን ለመዘገብ ሲንቀሳቀሱ ክልከላ እንደገጠማቸው ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
የኢትዯጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቦርዱ ተመዝግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን “በውስን አካባቢዎች” ሥራ እንዳቆሙ አስታወቀ።
ትናንት እሑድ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የተባለው መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎቹ የምርጫ ዝግጅቱን ለመቃኘት በምርጫ ጣቢያዎች ሲንቀሳቀሱ ከምርጫ አስፈፃሚዎች እና ከፀጥታ ኃይሎች ክልከላ እንደተደረገባቸው አስታውቋል።
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 “ሁለት የብልጽግና ፓርቲ ታዛቢዎች መሆናቸውን የገለጹ ግለሰቦች” ከበላይ ትዕዛዝ እስኪሰጣቸው ድረስ ክልከላ ካደረጉ በኋላ ፈቃድ ቢሰጡም ምሥል መቅረፅ ግን እንደከለከሉ ገልጿል።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በአንድ የምርጫ ጣቢያ የፀጥታ ኃይሎች ተመሳሳይ ክልከላ ማድረጋቸውን መገናኛ ብዙኃኑ አስታውቋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደግሞ ጥበቃ ለማድረግ የተሰማሩ የፖሊስ አባላት ምንም እንኳ በምርጫ ቦርድ ለዘጋቢዎቹ የተሰጠን መታወቂያ ቢመለከቱም “በስፍራው መዘገብም ሆነ ፎቶ ማንሳት ከልክለዋል” ብሏል።
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማም ተመሳሳይ ክልከላ እንደገጠመው ገልጿል።
ቢቢሲ ምርጫውን በአገር ውስጥ ለመዘገብ ፈቃድ አልተሰጠውም።
ቦርዱ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ አካባቢዎች ለመዘገብ “ደብዳቤ” እንዲፃፍላቸው መጠየቃቸውን ጠቁሞ፤ መገናኛ ብዙኃንን ከሥራ ማስቆም “የተሳሳተ” ነው ብሏል።
አክሎም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር መሠረት “ማንኛውም ሰው ቦርዱ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ሲያስፈጽም የመተባበር ግዴታ አለበት” በማለት አሳስቧል፡፡
ቦርዱ ምርጫውን እንዲዘግቡ 68 መገናኛ ብዙኃንን እና 1,815 ጋዜጠኞችን መመዝገቡን ገልጿል። እነዚህ ባለሙያዎች በምርጫ ጣቢያዎች 200 ሜትር ንፍቀ ክበበ ውስጥ ገብተው መዘገብ የሚያስችላቸውን መለያ ባጅ መስጠቱን ተናግሯል።