በመገናኛ ብዙኃን 'አፈና' እና 'በፉክክር ማነስ' ትችት የተነሳበት የነገው ጠቅላላ ምርጫ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች በሚስተዋሉበት ሁኔታ ነገ የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ "እምብዛም ፉክክር የማይኖረው" መሆኑት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሲናገሩ ቆይተዋል።

በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ካሉት ግጭቶች ባሻገር የትግራይ ክልል በምርጫው አለመሳተፍም ሌላው ፖለቲከኞች የሚያነሱት ነጥብ ነው።

ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይ የተጣለው ክልከላም በተያያዥነት ይነሳል። ቢቢሲ ምርጫውን በአገር ውስጥ ለመዘገብ ፈቃድ አልተሰጠውም።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በምርጫው ወቅት በመገናኛ ብዙኃን ላይ አጠናክረውታል ያለውን "አፈና እንዲቀለብሱ" ከቀናት በፊት አሳስቧል።

ዓለም አቀፉ የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ቡድን በአውሮፓውያኑ 2025 ባወጣው ዝርዝር፤ በመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ኢትዮጵያ ከ180 አገራት 148ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ኦሮሚያ ክልል ባለው የፀጥታ ሁኔታ እና የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ለምርጫ የሚጋብዝ ስላልሆነ በአዲስ አበባ ብቻ ለመወዳደር መወሰኑን ማስታወቁ አይዘነጋም።

የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ምርጫው "በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዝቅተኛ ፉክክር የሚካሄድበት" እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"የምንሳተፈው ሕጉ በተከታታይ በምርጫ አለመሳተፍን ስለማይፈቅድ ነው" ያሉት ፕ/ር መረራ በምርጫው የሚወዳዱት "ከፓርቲነት እንዳይሰረዙ" ሲሉ መሆኑንም አስረድተዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ያለፈው መስከረም ላይ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት "ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞችን በዘፈቀደ ማሰሩን" በመኮነን የሚደርሰው ጫና እንዲቆም ጠይቋል።

የሮይተርስ የዜና ወኪል ሦስት ጋዜጠኞች ፈቃድ መሰረዙን ተከትሎ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ "በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እና ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን ላይ አፋኝ የሆነ የቁጥጥር እርምጃ መተግበሩ አሳሳቢ አካሄድ ነው" ማለቱም ይታወሳል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የሚደግፉ አስተያየት ሰጪዎች የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎችም ፕሮጀክቶችን በመጥቀስ በአገሪቱ "ለውጥ እንደሚስተዋል" ይጠቅሳሉ።

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከተማን "ከማዘመን" አንጻር የሚመለከቷቸው እንዳሉ ሁሉ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን በማጣቀስ ትችትም ይነሳባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማሻሻል የወሰዷቸው እርምጃዎች በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና በዓለም ባንክ የተደገፉ ናቸው።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው አለመረጋጋት እንዲሁም በትግራይ ክልል ዳግመኛ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚለው ስጋትም ምርጫው ላይ ጥያቄ ካስነሱ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ከሚፈጠሩ ግጭቶች በተጨማሪ ነዋሪዎች በታጣቂዎች መታገታቸው እና መገደላቸውም በተለያየ ወቅት ሲዘገብ ቆይቷል።

በአማራ ክልል በፋኖ ኃይሎች እና በመንግሥት መካከል በቀጠለው ግጭትም በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በግጭቶች የተነሳ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በሰዎች ሕይወት ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ባሻገር የመሠረተ ልማት ውድመትም መድረሱ ተዘግቧል።

ግጭቶችን የሚከታተለው አክሌድ ባወጣው መረጃ መሠረት በአውሮፓውያኑ 2024 በእነዚህ አካባቢዎች ባለው ግጭት ምክንያት ከ9,400 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

መንግሥት በበኩሉ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች 97% የሚሆኑ አካባቢዎች ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በአማራ ክልል ከሚገኙ 138 የምርጫ ክልሎች መካከል በስምንቱ ምርጫ እንደማይደረግ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ቦርዱ በተጨማሪም የዘንድሮው አገራዊ ምርጫ በትግራይ ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ጋር አንድ ላይ ምርጫ እንደማይካሄድ ገልጿል።

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ጸሐፊ ምሥጢረሥላሴ ታምራት "በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ እንደማንችል ከዚህ ቀደም አስታውቀናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የክራይሲስ ግሩፕ የምሥራቅ አፍሪካ ባለሙያ ማግነስ ቴይለር በበኩላቸው "ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በድጋሚ እንደሚመረጡ እርግጠኛ ናቸው" ብለዋል።

"ነገር ግን ውስጣዊ የደኅንነት ጉዳዮች፣ የሽምቅ ውጊያዎች እና በሰሜኑ [የአገሪቱ ክፍል] አዲስ ጦርነት ይነሳል የሚለው ስጋት በዚህ መሸፈን የለባቸውም" ሲሉም አክለዋል።

በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው ውጥረት የሚጠቅሱት የክራይሲስ ግሩፕ የምሥራቅ አፍሪካ ባለሙያ፤ በሁለቱ ወገኖች በኩል ንግግሮች እንዲጀመሩ ቀጣናዊ አደራዳሪዎች ጣልቃ መግባት እንዳለባቸው ያምናሉ።

"ቢያንስ የተሳሳተ ስሌትን ይቀርፋሉ አልያም ልዩነታቸውን በመታኮስ ሳይሆን በንግግር እንዲፈቱ በመካከላቸው ያለውን ግለት ይቀንሳሉ" ይላሉ።

የግጭቶች መንሰራፋት እና ፖለቲካዊ ውጥረቱ እንዳለ ሆኖ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድምጻቸውን ለመስጠት መመዝገባቸውን ምርጫ ቦር አስታውቋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ የምትሰጠው የአዲስ አበባ ነዋሪ ፌኔት ደረጄ "የምርጫው ውጤት አወንታዊ ካልሆነ ከምጣኔ ሃብት እና ፖለቲካ አንጻር የእለት ከዕለት ኑሮዬ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ትምህርቴን መቀጠል አልችልም፤ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስም ያስቸግራል" ትላለች።

ግንቦት መባቻ ላይ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአፈጻጸም ሪፖርቱን ባቀረበበት መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "አገራዊ ምክክር እየተደረገ ያለው በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ያለ ማብቂያ የተቀመጠውን የአገሪቱን መሪ የሥልጣን ዘመን ለመገደብ" ነው ማለታቸው ይታወሳል።