ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፣ ዩኬ እና አውስትራሊያ የባሕር ውስጥ ድሮን ሊሠሩ መሆኑን አስታወቁ
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያ 'ኦከስ' ተብሎ በሚታወቀው ወታደራዊ ጥምረታቸው አማካኝነት የባሕር ስር ኬብሎችን ለመጠበቅ እና የመከላከያ አቅማቸውን ለማጠናከር ሲሉ በባሕር ውስጥ የሚንቀሳቀስ የድሮን ቴክኖሎጂ እያለሙ መሆኑን አስታወቁ።
የሰው አልባ የባሕር ስር ተሽከርካሪ ቴክኖሎጂው በሚቀጥለው ዓመት ዝግጁ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስወጣ ይፋ ባይደረግም የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሊ ግን አገራቸው 201 ሚሊዮን ዶላር እንደምታዋጣ ተናግረዋል።
የሦስቱ ሀገራት መከላከያ ሚኒስትሮች ሲንጋፖር ውስጥ በተካሄደው የደኅንነት ጉባኤ ላይ ይህንን ያስታወቁት፤ 'ኦከስ' ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዘግይቷል የሚል ትችት ከተነሳ በኋላ ነው።
ለዚህ ወቀሳ እውቅና የሰጡት የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር ሄሊ፤ "ለረዥም ጊዜ ኦከስ ውስጥ ብዙ አውርተናል፤ ያከናወንነው ግን ጥቂት ነው" ብለዋል። "አሁን በሦስቱ መንግሥታቶቻችን ሥር ይህ ተለውጧል" ሲሉም አክለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2021 የተጀመረው የኦከስ የመከላከያ ጥምረት መሠረት ሦስቱ አገራት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመስራት እና ወታደራዊ ልምዶችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል።
ይህ ጥምረት፤ በኢንዶ ፓስፊክ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን የቻይና የባሕር ላይ እንቅስቃሴ እንዲሁም አገሪቱ እንደ የደቡብ ቻይና ባሕር ባሉ አወዛጋቢ ግዛቶች የሚታዩ ውጥረቶች ለመጨመራቸው ያላትን ሚና ለመግታት የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል።
የሰው አልባ የባሕር ስር ተሽከርካሪ ቴክኖሎጂ በኦከስ 'ፒላር ቱ' ሥር የሚከናወን የመጀመሪያው ትልቅ ፕሮጀክት ይሆናል። 'ፒላር ቱ' አጋር አገራቱ እንደ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች፣ የባሕር ስር ሮቦቲክስ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ባሉ "የላቁ አቅሞች" ላይ በጋራ የሚሰሩበት ነው።
አገራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ በአዲሱ ፕሮጀክት አማካኝነት የሰው አልባ የባሕር ስር ተሽከርካሪው የባሕር ወለል መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ፣ ጥቃቶችን ለመፈጸም እንዲሁም የቅኝት፣ ስለላ እና የሎጂስቲክስ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ "እጅግ ዘመናዊ ሥርዓቶች" እንደሚዘጋጁለት አስታውቀዋል።
የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር ሄሊ፤ "ኃይሎቻችን በፍጥነት የላቀ የውጊያ ቴክኖሎጂ" የሚያስታጥቅ የሴንሰር እና የመሣሪያ ስርዓቶች ለሰው አልባ የባሕር ስር ተሽከርካሪው ይለማለታል ሲሉም ተናግረዋል።
መሣሪያው "አብዛኛው የዕለት ተዕለት ሕይወታችን የተመሠረተባቸው የባሕር ሥር ኬብሎች እና ማስተላልፊያ ትቦዎች" ላይ የሚቃጡ ስጋቶችን ለመግታት እንደሚረዳም ገልጸዋል።
አገራቱ ይህንን ፕሮጀክት ይፋ ያደረጉት ዩናይትድ ኪንግደም በአገሪቱ ሰሜናዊ አቅጣጫ የሚገኙ ኬብሎች እና ማስተላልፊያ ትቦዎች ላይ ሩሲያ ድብቅ ዘመቻ እያካሄደች ነው የሚል ክስ ካሰማች ከአንድ ወር በኋላ ነው።
ታህሳስ ላይ የናይትድ ኪንግደም እና ኖርዌይ የባሕር ስር ኬብሎችን ለመጠበቅ እንዲቻል በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ የሚንቀሳቀሱ የሩሲያ ሰርጓጅ መርከቦችን የሚያድኑበት ስምምነት ተፈራርመዋል።