ኦፕራ ዊንፍሬ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የሴቶች ትምህርት ቤቷን ልትዘጋ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ዝነኛዋ የቴሌቪዥን ትዕይንት አሰናጅ አሜሪካዊቷ ኦፕራ ዊንፍሬይ በደቡብ አፍሪካ ለ20 ዓመታት ያህል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን የሴቶች ትምህርት ቤቷን በሚቀጥለው ዓመት እንደምትዘጋ አስታወቀች።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2027 የትምህርት ዘመን መጨረሻ ላይ፣ በጆሃንስበርግ አቅራቢያ የሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤት ለአካባቢው የትምህርት ባለሥልጣናት ተላልፎ እንደሚሰጥ በመግለጫዋ ተናግራለች።
በ'ኦፕራ ዊንፍሬይ ሊደርሺፕ አካዳሚ ፎር ገርልስ' የተመዘገቡ እና ትምህርት ቤቱ ሲዘጋ የማይመረቁ ተማሪዎች ሌላ ቦታ ሙሉ የትምህርት ዕድል ያገኛሉ ተብሏል።
አነስተኛ ገቢ ካላቸው የተገኙ ከ1,000 በላይ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ተመርቀዋል። ዊንፍሬይ ትምህርት ቤቱን የከፈተችው እአአ በ2002 ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ጋር ከተገናኘች በኋላ ነው።
ከጆሃንስበርግ በስተደቡብ በምትገኘው ሄንሊ-ኦን-ክሊፕ መንደር የሚገኘው በ40 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው ይህ ትምህርት ከተከፈተ በኋላ የተለያዩ ውንጀላዎች ቀርበውበት ያውቃል።
አንዳንዶች ለትምህርት ቤቱ መዘጋት ይህንን እንደ ምክንያትነት ጠቅሰዋል።
ለኦፕራ ዊንፍሬይ የአመራር አካዳሚ ፋውንዴሽን የሚሰራ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ግን ትምህርት ቤቱ በአስተዳደራዊ መዝረክረክ ምክንያት እንደሚዘጋ በኦንላይን የሚናፈሰውን አሉባልታ አስተባብሏል።
ዊንፍሬይ በመላ አገሪቱ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ሴት ተማሪዎች የነፃ ትምህርት ፕሮግራም እንዲያገኙ በገንዘብ በመደገፍ የትምህርት ፕሮጀክቷን ለመቀጠል እንዳሰበች ፋውንዴሽኑ ገልጿል።
የ72 ዓመቷ ዊንፍሬይ በሰጠችው መግለጫ "ሕልሜ ትምህርት ቤት መገንባት ብቻ አልነበረም" ብላለች።
"የወጣት ሴቶች ገደብ የለሽ አቅም ላይ ኢንቨስት ማድረግ ነበር። ያ ተልዕኮ በአንድ ትምህርት ቤት ብቻ አያበቃም። የወደፊት ሕይወታቸው በትምህርት ሊለወጥ በሚችል በእያንዳንዱ ልጃገረድ ላይ ይቀጥላል።"
"ይህ ቀጣይ ምዕራፍ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተጨማሪ ወጣት ሴቶችን እንድናገኝ እና ከ20 ዓመታት በፊት የተጀመረውን ተስፋ እንድንቀጥል ስለሚያስችለን በጣም ደስ ብሎኛል" ብላለች።
ትምህርት ቤቱ ለአካባቢው ባለሥልጣናት ከተሰጠ በኋላ ለምን ጥቅም ላይ እንደሚውል ባይታወቅም፣ የጋውቴንግ ግዛት የትምህርት ክፍል ግን "የአካዳሚውን ተልዕኮ ለመጠበቅ እና ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው" ብሏል።
"ይህ ልዩ ተቋም የጋውቴንግን ሕዝብ ማገልገል መቀጠሉን እናረጋግጣለን፤ የተመሠረተበትን ራዕይም እናከብራለን" ብሏል።
ትምህርት ቤቱ እአአ በ2007 ሲከፈት ሁለት ቴአትር ማሳያዎች፣ የዩጋ መስሪያ እና የውበት ሳሎን ስላለው አንዳንዶች የቅንጦት ትምህርት ቤት ሲሉ ተችተዋል።
በዚህ ላይ የወጣው ገንዘብ በመላ አገሪቱ ተጨማሪ ተማሪዎችን ለመርዳት በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሊውል ይችል ነበር ሲሉም ተደምጠዋል።
ከዚያም ትምህርት ቤቱ ከተከፈተ ከወራት በኋላ፣ አንዳንድ ተማሪዎች የቀድሞ የተቋሙ ሠራተኛ አባል በደል ፈጽማብናለች ሲሉ ከስሰዋል። በኋላ ላይ በተደረገ ምርመራ ከቀረበባት ክስ ነጻ ሆናለች።
በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቱ 281 ተማሪዎች ተመዝግበዋል። እንደ ኦፕራ ዴይሊ ድረ ገጽ መረጃ ከሆነ ብዙዎቹ የትምህርት ቤቱ ተመራቂዎች ዶክተሮች፣ ጠበቆች፣ መሐንዲሶች፣ አርቲስቶች እና ሥራ ፈጣሪዎች ሆነዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ የ2012 ተመራቂ የነበሩት እና በአሁን ወቅት በሜታ ውስጥ ከፍተኛ የምህንድስና ኃላፊ የሆኑት አንድሮኒካ ክላስ "የትምህርት ቤቱ እያንዳንዱ ክፍል በብዙ ፍቅር፣ እንክብካቤ እና ዝርዝር ነገሮች የተሞላ ነበር።
"ትምህርት ቤቱ ከየት እንደመጣሁ ከማሰብ ይልቅ ዝግጅት፣ ባህሪ እና ዓላማ አስፈላጊ እንደሆኑ አሳምኖኛል" ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።















