ውጊያቸውን ጋብ ያደረጉት አሜሪካ እና ኢራን ንግግር ላይ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ እና ኢራን ለተከታታይ ሦስተኛ ቀን ጥቃት ሳይለዋወጡ መዋላቸውን ተከትሎ፣ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት በተመለከተ "እጅግ ወዳጅነት የተሞላባቸው ድርድሮች እየተካሄዱ ነው" አሉ።
ሰኞ ምሽት በፕሬዝዳንታዊው አውሮፕላን ‘ኤር ፎርስ ዋን’ ውስጥ ሆነው ጋዜጠኞችን ያነጋገሩት ትራምፕ፣ “አንዳች መልካም ነገር ሊፈጠር የሚችልበት ጥሩ ዕድል እንዳለ አስባለሁ” ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አሁን የሚደረገው ድርድር የሚከሽፍ ከሆነ ውጊያው ከመገታቱ በፊት “ስናደርግ የነበረውን ነገር ወደ መፈጸም እንመለሳለን” በማለት አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ይህንን ቢሉም ኢራን ግን ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ድርድር እየተካሄደ አለመሆኑን አስታውቃለች።
ትራምፕ እንዳሉት ከአርብ ዕለት አንስቶ ኢራን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመግታት የወሰኑት ሁለቱን ተፋላሚ አካላት የሚያሸማግሉ አገራት ለንግግሩ ሌላ ዕድል እንዲሰጡ ጥያቄ ስላቀረቡላቸው ነው።
ኢራንም ጥቃት መፈጸም አቁማለች።
ሁለቱ አገራት የሚያደርጉትን ውጊያ ጋብ ያደረጉት፣ ለሁለት ሳምንት ገደማ አንዳቸው በሌላኛቸው ይዞታ ላይ ጥቃት ሲያደርሱ ከቆዩ በኋላ ነው። ውጊያው ማገርሸቱም ሰኔ ላይ የተፈረመውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት አደጋ ውስጥ ከትቶታል።
የአሜሪካ ጦር የፈጸማቸው ጥቃቶች “ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የንግድ መርከብ ጉዞን አደጋ ላይ ለመጣል ያላትን አቅም ለማዳከም” ያለሙ እንደሆኑ በወቅቱ ገልጾ ነበር። ይህ አዲስ ውጊያ የተቀሰቀሰው ኢራን በወሳኙ የነዳጅ መተላለፊያ መስመር ላይ የተጓዙ መርከቦችን ከመታች በኋላ ነበር።
የሁለቱ አገራት ግጭት ረግቦ ሊቆይ ይችላል የሚል ተስፋ በመፈጠሩም በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ በ9% ቀንሶ በበርሜል 87.59 ዶላር ሲሸጥ ታይቷል።
ፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላናቸው ውስጥ ሆነው ጋዜጠኞችን ያነጋገሩት ትራምፕ፤ ለአምስት ወራት ስትዋጋ ቆየችው አሜሪካ የተተኳሽ ክምችቷ እየቀነሰ ነው በሚል የወጡ ዘገባዎችን አጣጥለዋል።
“እጅግ ብዙ ተተኳሽ አለን። መካከለኛ ደረጃ [መሣሪያዎችም] በብዛት አሉን፤ ምንም ቢሆን ልንጠቀምበት ከምንችለው በላይ [አለን]” ብለዋል። “ብዙ አለን፤ ግን ተጨማሪ ቢኖረን ደስ ይለኛል” ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ “በርካታ መሣሪያዎች” እየተመረቱ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ከፍተኛ ዋጋ ያለው አሜሪካ ሰራሹ ‘ፓትሪዮትስ’ የተሰኙት ፀረ ባለስቲክ ሚሳዔሎች እየተመረቱ መሆኑንም አስታውቀዋል።










