በአዲስ አበባ ታግታ በተገደለችው ቅዱሳን ይርጋለም ሞት የተጠረጠሩት ግለሰቦች ወንጀሉን እንደፈጸሙ ማመናቸውን ፖሊስ አስታወቀ

ቅዱሳን ይርጋለም

የፎቶው ባለመብት, KIDUSAN YIRGALEM/INSTAGRAM

የምስሉ መግለጫ, ቅዱሳን ይርጋለም
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢትዮጵያን ወክላ በአውሮፓውያኑ 2026 'ሚስ ወርልድ' የቁንጅና ውድድር ላይ የምትሳተፈው ሩት ይርጋለም ታላቅ እህት የሆነችው ቅዱሳን ይርጋለም ታግታ መገደሏን ተከትሎ፤ የሩት የቅርብ ጓደኛን ጨምሮ አሥር ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

በግድያው የተጠረጠሩት የሩት የቀድሞ ጓደኛ እና ፍቅረኛዋ ከሌሎች ስምንት ተጠርጣሪዎች ጋር በመቀናጀት ሟችን "ጭካኔ በተሞላበት መልኩ በመግደል" እንደተጠረጠሩ ፖሊስ ለቢቢሲ ገልጿል።

ግድያው የተፈፀመው የሟች እህት ሩት በመጪው ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በቬትናም መካሄድ በሚጀምረው 'ሚስ ወርልድ 2026' ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገችበት ባለችበት ወቅት ነው።

የአገሯን ባህል ይበልጥ እንድትረዳ እና እንድታስተዋውቅ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላለፉት ሦስት ወራት ያህል ጉብኝት እያደረገች የነበረችው ሩት፤ በአርባ ምንጭ ከተማ ቆይታ እያደረገች እያለ ነው እህቷ መታገቷን የሰማችው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ቶማስ እሸቴ፤ ተጠርጣሪዎቹ ግድያውን የፈፀሙት "ገንዘብ ለመቀበል በማሰብ" መሆኑን በሰጡት ቃል እንዳመኑ አስረድተዋል።

"የገንዘብ ችግር አለብን፤ ያንን የገንዘብ ችግር ለማቃለል ይህንን ወንጀል ፈፅመናል" በማለት ተጠርጣሪዎቹ ለፖሊስ በሰጡት ቃል ማስረዳታቸውን ኮማንደሩ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ታጋቿን ለማስለቀቅ ከቤተሰቦቿ 2.5 ሚሊዮን ብር ጠይቀው እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

ገንዘቡን ለመቀበል የተለያዩ ድርድሮችን ሲያደርጉ እና ገንዘቡን የሚቀበሉላቸውንም ሰዎች ሲልኩ እንደነበርም ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዕድሜዋ 30 የነበረው ሟች ቅዱሳን ይርጋለም የልብስ ዲዛይነር ስትሆን፤ በተጓዳኝም የተለያዩ የጌጣጌጥ ሥራዎችን ትሸጥ ነበር።

ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በሰጡት ቃል እንዳመኑ የተናገሩት ኮማንደር ቶማስ፤ ወንጀሉን በየትኛው ቦታ እና በምን ዓይነት መንገድ እንደፈፀሙት እማኞች ባሉበት፣ ቦታው ድረስ መርተው በመውሰድ ማሳየታቸውን አስረድተዋል።

በምርመራው ወቅት የነበረውን ሒደት እንደ እማኝ ቀርቦ ሲከታተል የነበረው የሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር አዘጋጆች ተወካይ አቶ አበባው አበበ እንዳሉት፤ በወንጀሉ ከተጠረጠሩት ሰዎች መካከል አንዷ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ የሩት የቅርብ ጓደኛ የነበረች ናት።

ሩት ከተጠርጣሪዋ ጋር በጊዜ ሒደት ጓደኝነታቸው እየጠበቀ በመምጣቱ፤ እንደ ቤተሰብ በመቀራረብ ጭምር ይተዋወቁ እና ይጠያየቁም እንደነበር አቶ አበባው ያብራራሉ።

ነገር ግን ከባለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በመካከላቸው በተፈጠሩ የተለያዩ አለመግባባቶች ምክንያት ግንኙነታቸውን አቋርጠው እና ተራርቀው እንደነበር ተናግረዋል።

አቶ አበባው እንደሚያብራሩት፤ አርብ ሐምሌ 10/ 2018 ዓ. ም. የሩት የቀድሞ ጓደኛ ማንነቷን ደብቃ እና በሌላ ሰው ስም በመጠቀም ለቅዱሳን ደውላለች።

ደዋይዋ ሁለት ወር ያለፈውን የሩትን ልደት "ሰርፕራይዝ ለማድረግ" እንዳሰበች እና ሟች የምትሸጣቸውን ጌጣጌጦች መግዛት እንደምትፈልግ ገልጻ እንደቀጠረቻት ይናገራሉ።

ቅዱሳንም ጉዳዩን በማመን አርብ ረፋድ አካባቢ ሜክሲኮ በሚገኝ ጭማቂ ቤት የተገኘች ሲሆን፤ በቦታው ስትደርስ ግን የቀጠራት ሰው በሌላ ስም የደወለችው የእህቷ የቀድሞ ጓደኛ መሆኗን መመልከቷን አስረድተዋል።

አቶ አበባው እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዋ "ከዚህ ቀደም አስቀይሜያችሁ ስለነበር እውነቴን ብነግርሽ አትመጪልኝም ብዬ በማሰብ ነው በሌላ ሰው ስም የደወልኩልሽ" ብላታለች።

ሟች ቅዱሳን በበኩሏ ለተጠርጣሪዋ ምላሽ ስትሰጥ "እኛ ብንቀየምሽ ኖሮ እኮ እናትሽ ታማ በነበረበት ወቅትም ሆነ ስታርፍ መጥተን አንጠይቅሽም ነበር፤ ስለዚህ እኛ ምንም አልተቀየምንም" በማለት እንደመለሰችላት አስረድተዋል።

በመቀጠልም ተጠርጣሪዋ "አዲስ ቤት ተከራይቻለሁ፤ ስለዚህ መጥተሽ ቤቴን ብታይልኝ ደስ ይለኛል" ስትል ቅዱሳንን እንደጠየቀቻት እና አክላም "አሁን ላይ ሕይወቴ በጥሩ ሁኔታ ተሻሽሎልኛል፤ በዚያ ላይ ለአንቺም የምትሠሪያቸውን ሥራዎች ይዤ ስለመጣሁ እዚያው ቤቴ ሆነን እናወራለን" በማለት ኮዬ ፈጬ አካባቢ ወደ ተከራየችው ኮንዶሚኒየም ቤቷ እንደወሰደቻት ተነግሯል።

ቅዱሳን ይርጋለም

የፎቶው ባለመብት, KIDUSAN YIRGALEM/INSTAGRAM

የምስሉ መግለጫ, ቅዱሳን ይርጋለም

በአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ መሠረት፤ ተጠርጣሪዎቹ ቅዱሳንን ካገቱበት ኮዬ ፈጬ ከሚገኘው ኮንዶሚኒየም ሌላ ቤት በመከራየት አዘዋውረዋል።

ቅዱሳን ከታገተችበት አርብ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሞተች እስከታመነበት እሑድ ሐምሌ 12/ 2018 ዓ. ም. ድረስ "ምግብ እንዳልሰጧትም" ተነግሯል።

ተጠርጣሪዎቹ ቅዱሳን ላይ ግድያ ከፈፀሙባት በኋላ ለቤተሰቦቿ ደውለው ገንዘብ መጠየቃቸውን የምርመራ ሒደቱ ማሳየቱን ኮማንደር ቶማስ ገልጸዋል።

ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ አበባው እንዳሉት፤ ግድያው እሑድ ዕለት የተፈፀመ ሲሆን፤ አጋቾቹ ግን ሰኞ ዕለት እሷን በሕይወት ለማስለቀቅ በሚል ከቤተሰቧ ገንዘብ መጠየቃቸውን ቀጥለው ነበር።

የሩት የቀድሞ ጓደኛ እና ፍቅረኛዋ ቅዱሳንን "በግፍ ለመግደል" የወሰኑበት ዋና ምክንያት "ካየችሽ ስለምታውቅሽ ልታስይዘን ትችላለች" ብለው በመስጋት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የግድያ ሁኔታውን አስመልከቶ የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮማንደር ቶማስ ሲያስረዱ፤ "አሁን ላይ ለሚዲያ እና ለሕዝብ ለመናገር የማይመቹ አንዳንድ ከባድ ነገሮች አሉ" በማለት ዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

"በሟች ላይ የተፈፀመው ድርጊት እጅግ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ እና ጭካኔ የተሞላበት ነው" ሲሉ ወንጀሉ ምን ያህል ዘግናኝ እንደነበርም ገልጸዋል።

ይህንን አሰቃቂ ድርጊት በቀጥታ ፈፅመዋል ተብለው ከተጠረጠሩት የሩት የቀድሞ የቅርብ ጓደኛ እና ፍቅረኛዋ በተጨማሪ፤ ከጉዳዩ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ስምንት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ፖሊስ አሳውቋል።

በሚስ ወርልድ 2026 ውድድር ላይ አገሯን የምትወክለው የሟች እህት ሩት ይርጋለም፤ በእህቷ ሞት ምክንያት በከባድ ሐዘን ውስጥ እንደምትገኝ የሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ አዘጋጆች ተወካይ አቶ አበባው ተናግረዋል።

ሩት በመጪው ነሐሴ 3/2018 ዓ. ም. በሚጀምረው እና ከ170 በላይ አገራት በሚሳተፉበት ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ቬትናም እንደምታቀና ተገልጿል።