ዚምባብዌ ውስጥ አዲስ የዳይኖሰር ዝርያ ተገኘ

'ሙሳንጎ ማቱሳዶኔንሲስ' የሚል ስያሜ የተሰጠውን ዳይኖሰር የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Mark Witton

የምስሉ መግለጫ, 'ሙሳንጎ ማቱሳዶኔንሲስ' የሚል ስያሜ የተሰጠውን ዳይኖሰር የሚያሳይ ምስል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በደቡባዊ አፍሪካ ይኖር ስለነበረው ዳይኖሰር ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ ያደረገ አዲስ ዝርያ ዚምባብዌ ውስጥ ተገኘ።

'ሙሳንጎ ማቱሳዶኔንሲስ' የሚል ስያሜ የተሰጠው እና 4.5 ሜትር የሚረዝመው ይህ ዳይኖሰር፣ ዚምባብዌ ውስጥ የተገኘ አምስተኛው ዝርያ ሆኗል።

ዝርያው የተገኘው በዚምባብዌ 'ካሪባ' ሐይቅ ዳርቻ ላይ ሲሆን ከ210 ሚሊዮን ዓመታት በፊት 'ሌት ትሪያሲክ' ተብሎ በሚጠራው ዘመን ይኖር እንደነበር ይታመናል።

በዩናይትድ ኪንግደም፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባብዌ ትበብር የተደረሰበት ይህ ግኝት፣ በደቡባዊ አፍሪካ ይኖሩ ስለነበሩ የዳይኖሰር ዝርያዎች አዲስ መረጃ የሰጠ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል።

'ሌት ትሪያሲክ' የሚባለው ዘመን፣ ዳይኖሰሮች በምድር እንስሳት ላይ የበላይነት ከመያዛቸው አስቀድሞ በመላው ዓለም መስፋፋት የመጀመሩበት ጊዜ ነው።

በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ስፍራዎች ሰፊ ጥናት የተደረገባቸው ቢሆንም፤ ከአፍሪካ የተገኙ የቅሪተ አካል ግኝቶች እምብዛም ትኩረት አላገኙም።

በዚያ ዘመን አፍሪካ የአሁኖቹን ደቡብ አሜሪካ፣ ሕንድ፣ ኦስትራሊያ እና አንታርክቲካን ያካተተው 'ጎንድዋና' ተብሎ የሚጠራው ግዙፍ አህጉር አካል ነበረች።

አሁን የተገኘው 'ሙሳንጎ' የተሰኘው ዝርያ፤ ከአራት ይልቅ በሁለት እግራቸው ይራመዱ ከነበሩ የዳይኖሰር ዝርያዎች ጋር የቀደመ ዝምድና አለው።

'ሙሳንጎ' ላይ ጥናት የተደረገው የጀርባ አጥንት፣ የእጅ እና የእግር አጥንቶችን ያካተተ ቅሪተ አካል በመገኘቱ ነው። ጥናቱም እንደሚያሳየው የተገኘው ዳይኖሰር ሕይወቱ ያለፈው ሙሉ በሙሉ ዕድገቱን ሊጨርስ ሲል ነው።

አፈር ውስጥ የተቀበረ ቅሪተ አካል

የፎቶው ባለመብት, Paul Barrett

የምስሉ መግለጫ, የዳይኖሰሩ ቅሪተ አካል በዚምባብዌ 'ካሪባ' ሐይቅ ዳርቻ ተገኝቷል

ዕድሜው ስምንት ዓመት ገደማ እንደሆነ እና 4.5 ሜትር አካባቢ እንደሚረዝም ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል። ቁመቱ መካከለኛ መጠን ካለው መኪና ጋር እንደሚስተካከልም አስረድተዋል።

በተጨማሪም አጥኚዎቹ፣ ዳይኖሰሩ ዕፅዋትንም ሆነ ስጋ ይመገብ እንደነበር ያምናሉ። ምናልባትም ይመገብ የነበረው 'ፋይቶሶሮስ' የተባለውን አዞ መሰል ተሳቢ እንስሳ፣ 'ለንግፊሽ' የሚባለውን አሳ እንዲሁም ትናንሽ ዳይኖሰሮችን ይመገብ እንደነበር ተገምቷል።

በለንደን የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ፕሮፌሰር እና በ'ጆርናል ኦፍ ሰስተማቲክ ፓሌኦንቶሎጂ' ላይ የታተመው ይህ ጥናት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ፖል ባሬት፤ "እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በደቡባዊ አፍሪካ ይኖሩ የነበሩ ዳይኖሰሮች በአብዛኛው ተመሳሳይ እንደሆኑ ይታሰብ ነበር" ብለዋል።

"ይሁን እንጂ ጎንድዋና የተባለው ታላቅ አህጉር የተለያዩ የራሳቸው ባሕሪያት ካሏቸው በርካታ ትናንሽ ሥነ ምህዳሮች የተዋቀረ እንደነበር እነዚህ ግኝቶች አሳይተዋል" ሲሉም አብራርተዋል።