የአሜሪካ ጦር ዋና ፀሐፊ ለወራት የዘለቀ ውጥረትን ተከትሎ ሥልጣናቸውን ለቀቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ለ18 ወራት ያህል የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ዋና ፀሐፊ ሆነው ያገለገሉት ዳን ድሪስኮል የሥራ መልቀቂያ አስገቡ።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ፣ ዋና ፀሐፊው ሥራቸውን መልቀቃቸውን ያረጋገጠ ሲሆን ይህም የሆነው በእርሳቸው እና በመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት መካከል ለወራት ከዘለቀ ግጭት በኋላ ነው።

በአሜሪካ ታሪክ ወጣቱ የጦር ሠራዊት ዋና ፀሐፊ የነበሩት ድሪስኮል፣ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ "ድሮን" በመባል ይታወቃሉ።

"አሜሪካን ዳግም ጠንካራ ማድረግ" የሚለውን የትራምፕ አጀንዳ በማስፈፀም "እጅግ ውጤታማ" እንደሆኑ የሚነገርላቸው የ41 ዓመቱ ድሪስኮል፥ በወታደራዊ ዘመቻዎች ወቅት "እጅግ በጣም ጥሩ አመራር" እንደሰጡ ዋይት ሀውስ ለሲቢኤስ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ቢቢሲ ዋይት ሀውስን፣ ፔንታጎንን እና የአገሪቱን ጦር አስተያየት ጠይቋል።

ድሪስኮል በቅርብ ጊዜ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ወታደራዊ መሪዎች መካከል ሲሆኑ፣ የባህር ኃይል ሚኒስትሩ ጆን ፌላን ሚያዝያ ወር ላይ በድንገት ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወቃል።

ሥራቸውን ከለቀቁ ሌሎች ታዋቂ ወታደራዊ መሪዎች መካከል፣ የጦሩ አዛዥ ራንዲ ጆርጅ፣ የሠራዊቱ ጄኔራል ዴቪድ ሆድኔ እና ሜጀር ጄኔራል ዊሊያም ግሪን ይገኙበታል።

ሄግሴት ወደ ፔንታጎን ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ የባህር ኃይል የኦፕሬሽን ኃላፊ እና የአየር ኃይል ምክትል ዋና አዛዥን ጨምሮ ከአስራ ሁለት በላይ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ከሥራ አባረዋል።

ከመጋረጃ ጀርባ ያለው ድሪስኮልን እና ሄግሴትን ያላግባባው ጉዳይ ምን እንደሆነ በዝርዝር አይታወቅም። ሆኖም በሄግሴት ከሥራ እንዲለቁ ከተጠየቁት ጆርጅ ጋር ድሪስኮል መልካም ወዳጅነት እንዳላቸው ሲቢኤስ ጠቅሷል።

የጦር ኃይሎች ዋና ፀሐፊነት ቦታ፣ የብሔራዊ ዘብ እና ተጠባባቂ ወታደሮችን ጨምሮ በሥራ ላይ ያሉ ወታደሮችን የመምራት ኃላፊነትን የሚያካትት የአሜሪካ ጦር ከፍተኛ የሲቪል መሪነት ቦታ ነው።

ቀደም ሲል በጦር ኃይሎች ውስጥ ያገለገሉት ድሪስኮል፣ እአአ በ2009 ለብዙ ወራት በኢራቅ የዘመቱ ሲሆን ከ2007 ጀምሮ በመኮንንነት እንዲሁም በጦሩ የተለያዩ ክፍሎችም በኃላፊነት መርተዋል።

የጦር ኃይሎች ዋና ፀሐፊ በነበሩበት ወቅት የትራምፕ "ድሮን" የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አዳዲስ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን ለመቀበል እና ለማስተናገድ ባላቸው ቁርጠኝነት የተነሳ ነው።

ባለፈው ዓመት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም የውጭ ጉዞዎችን በማድረግ እና ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጋር በመገናኘት በተደረጉ ንግግሮች ላይ ድሪስኮል የመሪነት ሚና ተጫውተዋል።

በዬል የሕግ ትምህርት ቤት የሚያውቋቸው የምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የቅርብ አጋር እና ጓደኛ ናቸው።

የአሜሪካ ጦር መሪ ሆነው በቆዩበት ወቅት፣ ትራምፕ የብሔራዊ ዘብን ወደ አሜሪካ ከተሞች ባሰማሩበት ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሰው ነበሩ።

ድሪስኮል ከአሜሪካ ጦር መሪነት በተጨማሪ፣ የአልኮል፣ የትምባሆ፣ የጦር መሳሪያዎችና ፈንጂዎች ቢሮ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል።