ሩሲያ በኒጀር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንዲከሽፍ ድጋፍ ማድረጓን አስታወቀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቅዳሜ ዕለት በኒጀር የተሞከረውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማክሸፍ ሂደት ጦሯ ድጋፍ ማድረጉን ሩሲያ ገለፀች።

በዕለቱ ጠዋት ላይ ፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት እና የአገሪቱ ቁልፍ ወታደራዊ የአየር ማረፊያን ጨምሮ በዋና ከተማዋ ኒያሜ ፍንዳታዎች እና ተኩሶች ተሰምተዋል።

ከሰዓታት በኋላ አመጹ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኒጀር ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

"በሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጦር አባላት እገዛ" የኒጀር ጦር ጥቃቱን ማክሸፉን የሞስኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ አክሎም፣ ኒጀር በጽንፈኞች ላይ ለምታደርገው ውጊያ "ድጋፍ ማድረጌን እቀጥላለሁ" ብሏል። አሁን ሁኔታው "በፕሬዝደንት [ጌነራል አብዱራህማን] ቲያኒ በሚመሩት ሕጋዊ ባለሥልጣናት" ቁጥጥር ስር መሆኑንም ጠቅሷል።

በአፍሪካ የሚገኘው የሩሲያ ጦር፣ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የጂሃዲስት ሰርጎ ገቦች እንቅስቃሴ መከላከል ፈተና ለሆነባቸው የሳህል ቀጣና ወታደራዊ መንግሥታት ቁልፍ የደኅንነት አጋር ሆኖ በመሥራት ላይ ይገኛል።

ኒጀር፣ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶን ያካተተው የሳህል አገራት ጥምረት፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው "አለመረጋጋትን ለመፍጠር በሚጥሩ ወታደሮች የተፈፀመ ክህደት ነው" ሲሉ አውግዘዋል።

በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ላይ ምን ያህል ወታደሮች እንደተሳተፉም ሆነ ስለደረሰው የጉዳት መጠን ባለሥልጣናት ያሉት ነገር የለም።

በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡትን የአገሪቱን ፕሬዝደንት በማውረድ ባለፈው ዓመት ቃለ መሃላ ፈፅመው ሥልጣኑን የተረከቡት የኒጀር ወታደራዊ መሪ ጌነራል ቲያኒ ስለ ቅዳሜ ማለዳው ክስተት በይፋ አልተናገሩም።

የሀገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ፣ በፕሬዝዳንታዊ ዘብ የተያዙ እና "ከዳተኞች" የተባሉ በርካታ ወታደሮችን የሚያሳይ ቪዲዮ አቅርቧል።

የኒጀር ፕሬስ አገልግሎት፣ የነዳጅ ማደያዎች፣ ሱቆች እና ሌሎች የንግድ ማዕከላት መከፈታቸውን ጠቅሶ እንቅስቃሴዎች ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለሳቸውን እሁድ ዕለት ዘግቧል።

የመንግሥት ደጋፊዎች በማዕከላዊ ኒያሜ በሚገኝ ህዝባዊ አደባባይ ወጥተው ለአገሪቱ ጦር እና ለቲያኒ አስተዳደር ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።

ቅዳሜ ዕለት ጥቃት የተፈፀመበት ወታደራዊው 'የአየር ሰፈር 101' በአገሪቱ የመጀመሪያ ፕሬዝደንት ዲዮሪ ሃማኒ የተሰየመው አየር ማረፊያ አካል ነው።

ስፍራው፣ የኒጀር ወታደራዊ አውሮፕላኖችን እና ድሮኖችን እንዲሁም የሳህል አገራትን የፀረ ሽብርተኝነት ወታደራዊ ጥምረት ያስተናግዳል። የሩሲያ እና የጣሊያን ኃይሎችም በቦታው እንደሚገኙ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ኒጀር፣ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ በወታደራዊ መንግሥት የሚመሩ አገራት ሲሆን፣ ከምዕራባውያን አጋሮቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠው ከሩሲያ ጋር ትስስራቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ።

ምንም እንኳ አጋርነታቸውን ከምዕራቡ ወደ ምስራቁ ዓለም ቢቀይሩም፣ በሦስቱም አገሮች የሃይማኖታዊ አክራሪ ጂሃዲስቶች የአመፅ እንቅስቃሴ ተስፋፍቶ ይገኛል።

የቅዳሜው አመፅ፣ የኒጀር መንግሥት ከውጫዊ ሰርጎ ገቦች ጋር ከሚያደርገው ፍልሚያ በተጨማሪ በራሱ ቡድን ውስጥም ደስተኛ ያልሆኑ አካላት መኖራቸውን የሚያሳይ ነው።

አመፁ የተቀሰቀሰበት የአየር ጦር ሰፈር፣ በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት ጊዜ በጂሃዲስቶች ዒላማ ሆኗል።

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች በኒያሜ ቁልፍ ቦታዎች የሚያደርጉት ክትትል መጨመሩን የኒጀር ባለሥልጣናት ተናግረዋል።