ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ እና ሩሲያ የካናዳ ተገንጣዮችን ጥያቄ እያቀጣጠሉ ነው ተባለ
የካናዳዋ ግዛት አልበርታ ያነሳችውን የመገንጠል ጥያቄ አሜሪካ እና ሩሲያ እያቀጣጠሉ መሆኑን አዲስ የወጣ ሪፖርት ጠቆመ።
ሪፖርቱን ይፋ ያደረጉት አጥኚዎች እንዳሉት፤ የአሜሪካ እና ሩሲያ ጣልቃ ገብነት የካናዳን "ዴሞክራሲያዊ ልዕልና" አደጋ ውስጥ ይጥላል።
በምዕራባዊቷ የካናዳ ግዛት አልበርታ በቅርቡ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ሐሳብ ቀርቧል።
አልበርታ ከካናዳ እንድትገነጠል ንቅናቄ የሚያደርጉ ነዋሪዎች ለሕዝበ ውሳኔ የሚያበቃ ፊርማ ማሰባሰባቸውን በተያዘው ሳምንት አስታውቀዋል።
በካናዳ ማዕከላዊ መንግሥት ውሳኔዎች ውስጥ አልበርታ መገለል ደርሶባታል በሚል የመገንጠል ጥያቄውን ሲያስተጋቡ ቆይተዋል።
ከግዛቷ ነዋሪዎች 25% የመገንጠል ጥያቄን እንደሚደግፉም ተገልጿል።
ግሎባል ሴንተር ፎር ዴሞክራቲክ ሪዚሊያንስ፣ ሴንተር ፎር አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ፣ ዳታ ኤንድ ኮንፍሊክት እንዲሁም ዲስኢንፎዋች የተባሉ ተቋማት በጥምረት ባወጡት ሪፖርት፤ "የውጭ አካላት እውነተኛ [የካናዳ] ግዛታዊ ጥያቄዎችን እየተጠቀሙባቸው ነው" ብለዋል።
በተለያዩ ሃብቶች የበለጸገችው አልበርታ የምጣኔ ሃብት ብዝበዛ እየደረሰባት ነው የሚለውን ጨምሮ ሌሎችም ከግዛቲቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን "የሩሲያ የመረጃ ማሰራጫዎች" እና ሌሎችም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ጥቅም ላይ እንዳዋሉት ሪፖርቱ ይጠቁማል።
አጥኚዎቹ "የመገንጠል ጥያቄን የውጭ ኃይሎች ሲያስተጋቡት፣ መገንጠልን የተለመደ ሲያስመስሉት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ሲያጣጥሉ የአንድ ግዛት ጥያቄ መሆኑ ያከትማል" በማለት ግኝታቸውን አስቀምጠዋል።
ይህም "ለካናዳ ዴሞክራሲያዊ ልዕልና፣ ብሔራዊ ደኅንነት እና ሉዓላዊነት" ስጋት የሚደቅን ነው ብለዋል።
ቢቢሲ በካናዳ ካለው የሩሲያ ኤምባሲ ስለ ጉዳዩ ምላሽ ጠይቋል።
ሪፖርቱን ካወጡት ተቋማት አንዱ የሆነው ዲስኢንፎዋች ኃላፊ ማርከስ ኮልጋ "ካናዳ ያለ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ውይይት ማድረግ መቻል አለባት" ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ምርመራ የተደረገባቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ከዚህ ቀደም ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የሚታወቁ ናቸው።
በእነዚህ ገጾች የተለቀቁ ይዘቶች የአልበርታን የመገንጠል ጥያቄ ለማቀጣጠል ያለሙ ናቸው ተብሏል።
ሩሲያ በአልበርታ ግዛት የመገንጠል ጥያቄ ውስጥ ያላት ጣልቃ ገብነት "ዶግማዊ፣ ኦፕሬሽንን የተከለተ እና ዘላቂነት ያለው ነው" ሲል ሪፖርቱ አመልክቷል።
"ዓላማው የአገር ውስጥ ቅራኔዎች የውጭ አገር ትርክትን እንዲከተሉ ጫና ማሳደር ነው" ሲልም ሪፖርቱ ያክላል።
የተከፈላቸው የድምጽ ተዋንያን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም "እውነተኛ የካናዳውያንን ድምጽ" ለማስመሰል እንደተሞከረ ተገልጿል።
አሜሪካውያን ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም "እሳቱ ላይ ጋዝ እያርከፈከፉ ነው" ሲሉ የዲስኢንፎዋች ኃላፊ ማርከስ ኮልጋ ተናግረዋል። እነዚህ አካላት "ፖለቲካዊ ግብ" እንዳላቸውም አክለዋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአልበርታን የመገንጠል ፍላጎት ከሚያቀነቅኑ መሪዎች ጋር ተገናኝተው "ጥያቄያቸው ትክክል እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥተዋል" ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል።
ባለፈው ጥር ላይ የትራምፕ አስተዳደር ግዛቷ ከካናዳ እንደምትገነጠል መናገራቸውን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ እና የአልበርታ መሪ "አሜሪካ የአልበርታን የመገንጠል ጥያቄ ማክበር አለባት" ብለዋል።
የመገንጠል ጥያቄው በቂ ድጋፍ ካገኘ የፊታችን ጥቅምት ሕዝበ ውሳኔ ሊካሄድ ይችላል።
የመገንጠል ጥያቄ ሁሉንም የሚያስማማ ባይሆንም፤ ግዛቷ በፖለቲካዋ እና ምጣኔ ሃብቷ ላይ የተሻለ የውሳኔ ሰጭነት አቅም እንዲኖራት የሚፈልጉ በርካቶች ናቸው።
የመገንጠል ጥያቄው ተቀባይነት ቢያገኝም ረዥም ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነው።
በካናዳ ሕግ መሠረት የመገንጠል ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኘው "በግልጽ" በአብላጫ ድምጽ ነው። በተጨማሪም ጥያቄው ግልጽ እንዲሆን እና የበላይ ተቆጣጣሪው ምክር ቤቱ እንዲሆንም ያስፈልጋል።