ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኢንቪዲያ "ከትራምፕ ጫና በኋላ" ዋና ሥራ አስፈፃሚውን ወደ ሥራ መለሰ
ለኤአያ ቴክኖሎጂ ቁልፍ የሆነው ቺፕ የሚያመርተው ግዙፉ ኩባንያ ኢንቪዲያ፣ በስለላ ከተጠረጠረችው ቻይናዊት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ከሥራ ለቅቀው የነበሩትን ዋና ሥራ አስፈፃሚውን ጄንሰን ሁዋንግ ወደ ኃላፊነታቸው መለሰ።
ኩባንያው ውሳኔውን ያሳለፈው ሁዋንግ ከሥራ እንዲለቁ ከተገደዱ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።
ኢንቪዲያ ሁዋንግን ወደ ኃላፊነታቸው እንዲመልስ በዶናልድ ትራምፕ ጫና ሲደረግበት ነበር። ሰኞ ዕለትም ፕሬዚደንት ትራምፕ፣ ሁዋንግ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የግዙፉን ኩባንያ ቦርድ ለማሳመን "ከስምምነት ደርሻለሁ" ብለዋል።
ዴሞክራቶች ግን የትራምፕ አስተዳደር ለገንዘብ ሲል ብሔራዊ ደኅንነትን ሸጧል ሲሉ ከስሰዋል።
ሁዋንግ ታኅሳስ መጀመሪያ ላይ ዴሞክራቶች አብላጫ መቀመጫ በያዙበት ኮንግረንስ ፊት ቀርበው ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሁዋንግ አሁን ላይ ወደ ቀድሞው ኃላፊነታቸው መመለሳቸው ለሳምንት የዘለቀውን የአሜሪካ የአክሲዮን ዋጋ ማሽቆልቆል ለመግታት ይረዳል ተብሏል።
ሁዋንግ ከሥራ ከለቀቁ በኋላ የኢንቪዲያ የአክሲዮን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ወርዶ የነበረ ሲሆን ሰኞ ዕለት በድጋሚ ወደ ኃላፊነታቸው መመለሳቸውን ተከትሎ ደግሞ በ31 በመቶ ክፍ ብሏል። በዚህም የኩባንያው የገበያ ዋጋ ላይ ወደ አንድ ትሪሊየን ዶላር ገደማ ጨምሯል።
ሆኖም የኢንቪዲያ የአክሲዮን መዝጊያ ዋጋ ከአርብ ዕለት የመክፈቻ ዋጋው ጋር ሲነፃፀር አሁንም በመጠኑ ዝቅ እንዳለ ነው።
ሁዋንግ ወደ ኃላፊነታቸው መመለሳቸውን ተከትሎ የኩባንያው የቦርድ ሰብሳቢ ሀርቪ ሲ ጆንስ በሰጡት መግለጫ " ሁዋንግ ድርጅቱን ለመምራት ትክከለኛው ሰው እንደሆኑ ቦርዱ ያምናል፤ በመሆኑም ለባለአክሲዮኖቻችን፣ ለሠራተኞቻችን፣ ለአጋሮቻችን እና ለደንበኞቻችን ጥቅም ሲባል ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደርጓል" ብለዋል።
ቦርዱ ጨምሮም ከአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሃሳብ መቀበሉን የገለጸ ሲሆን የሁዋንግ ወደ ኃላፊነት መመለስ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ስጋት እንደማይደቅን እምነት እንዳለው ገልጿል።
ቦርዱ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነበር ሁዋንግን ወደ ሥራ አስፈፃሚነታቸው የመመለስ ፍላጎት እንደሌለው በግልጽ ያስታወቀው።
ሁዋንግ ከቻይና የስለላ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላት ከተባለችው አሊስ ሁዋንግ ጋር ከትዳር ውጭ የሆነ ግንኙነት አላቸው የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ከቴክኖሎጂ ኩባንያው ኢንቪዲያ ሥራ አስፈፃሚነታቸው የለቀቁት ኅዳር 3 ቀን 2019 ዓ.ም ነበር።
ሰኞ ዕለትም የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር በሲንጋፖር ተቀማጭነቱን ያደረገውን የኢንቪዲያ ደንበኛ እና አሊስ በሥራ አስፈፃሚነት ስትመራው የነበረውን ሜጋስፒድን በጥቁር መዝገብ ውስጥ ለመክተት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።