ትራምፕ ኢራን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከተኮሰችው የበለጠ ድሮን እና ሚሳዔል ባለፈው ሳምንት አስወንጭፋለች አሉ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ኢራን “ባለፈው ሳምንት በአንድ ዓመት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ካስወነጨፈችው በላይ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን” ብትተኩስም፣ ምንም ጉዳት አልደረሰም ሲሉ እሁድ ዕለት ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ዴሞክራቶች በሁለቱም የኮንግረስ ምክር ቤቶች አብላጫ ድምፅ ያሸነፉበትን የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በኢራን እየተካሄደ ካለው ጦርነት መባባስ ጋር አያይዘው አንስተውታል።
ፕሬዝዳንቱ ጥቅምት 24/2019 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫን በተመለከተ “ሁለት ነገሮችን ተንብየው” እንደነበረ ጠቅሰዋል።
“አንደኛ፣ ዴሞክራቶች ካሸነፉ የአክሲዮን ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ ይወድቃል የሚል ነበር፤ ይህም ተከስቷል። ሁለተኛው ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ 81,000 ተቃዋሚዎችን የገደለችው እስላማዊቷ የኢራን ሪፐብሊክ ጥቃቷን ይበልጥ ታጠናክራለች የሚል ሲሆን ይህም ሆኗል” በማለት ጽፈዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ፣ በአሜሪካውያን ስለ ኢኮኖሚው አካሄድ እንዲሰጉ አድርጓል።
ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን ጨምሮ ከፍተኛ የሪፐብሊካን አመራሮች ፓርቲያቸው በምርጫው የተሸነፈበት አንደኛው ምክንያት ከኢራን ጦርነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው እሁድ ዕለት ባሰፈሩት ፅሑፍ፣ መራጮች የድምፃቸውን ትርጉም “አልተረዱም” ያሉ ሲሆን፣ ምርጫውንም “እጅግ ‘ያልተለመደ’” ሲሉ ገልጸውታል።
“የኢራን መሪዎች ዴሞክራቶችን የሚመለከቷቸው እንደ ደካማ፣ ውጤታማ ያልሆኑ እና አገር አጥፊ ነው፤ ነገር ግን ይህ እንዲሆን አልፈቅድም! ዴሞክራቶችም ሆኑ ኢራን የነዳጅ ዋጋ በተቻለ መጠን ለረጅም ጊዜ ከፍ ብሎ እንዲቆይ እጅጉን ተፋልመዋል፤ ከምርጫው በሏላ ግን የነዳጅ ዋጋ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ቀንሷል” ብለዋል።
አክለውም “መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት ይህንን አለመረዳታቸው በጣም ያሳዝናል፤ ነገር ግን አጠቃላይ ምርጫው እጅግ ‘ያልተለመደ’ ነበር” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።
- ተያያዥ ዘገባዎች