በአዲስ አበባ ስለሚካሄደው የአፍሪካ ትልቁ የሕብረተሰብ ጤና ጉባዔ አንዳንድ እውነታዎች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ኮንፈረንስ (ሲፒኤችአይኤ) አምስተኛው ጉባኤ ከዛሬ ሰኞ ኅዳር 14 እስከ አርብ ኅዳር 18 ቀን 2019 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ይካሄዳል።

በአህጉሪቱ ትልቁ የሆነው ይህ የሕብረተሰብ ጤና ጉባዔ ከ114 አገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይታደሙበታል። ከሁሉም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት የተወከሉ የአገር መሪዎች፣ የጤና ሚኒስትሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ተወካዮች እና ወጣቶች የሚሳተፉበት ግዙፍ የጤና ጉበኤ ነው።

በአዲስ አበባ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ከሚቀርቡት ሳይንሳዊ ምርምር ጽሑፎች ብዛት፣ በተጓዳኝ ከሚካሄዱ ዝግጅቶች እና ከዓለም አቀፍ ተሳትፎ አንፃር በጉባኤው ታሪክ ትልቁ እንደሆነ ተነግሯል።

ጉባዔው ላይ ከአፍሪካ አገራት በተጨማሪ ከ114 በላይ አገራትን የሚወከሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በአካል እና በበይነ መረብ ይሳተፉበታል።

ከቀደሙት አራት ጉባዔዎች ሲነጻጸር የዘንድሮውን የሚታደሙ ተሰብሳቢዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን የላቀ ነው።

ለቀናት በሚዘልቀው ጉባዔ ላይ ከ660 በላይ ተናጋሪዎች በተለያዩ መድረኮች ንግግር የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ በሚመርጧቸው በ189 ውይይቶች ላይ የሚታደሙ ይሆናሉ።

ይህ ጉባዔ ምንም እንኳ በጠቅላላ ተሳትፎ በ2023 ዛምቢያ ሉሳካ ላይ የተመዘገበውን ከፍተኛ ክብረ ወሰን የሚበልጥ ሲሆን፣ የዘንድሮው የአዲስ አበባ ጉባኤ ከምርምር ውጤት እና ከመርሃ ግብር ዝግጅት አንጻር ከቀደሙት ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ የሚጠጋ ዕድገት አሳይቷል።

ለአምስት ቀናት የሚካሄደው 5ኛው የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ጤና ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ የተባበሩት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ይካሄዳል።

ጉባኤው በአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) እና በኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፣ "የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት፦ ከጤና ጥገኝነት እና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና ተቋቋሚነት ለውጥ" በሚል መሪ ሐሳብ በአፍሪካ የሚመራ የጤና ሥርዓት ግንባታ ላይ ያተኩራል።

በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው በአውሮፓውያኑ 2021 የኮሮናቫይረስ አደጋ በደቀነበት ወቅት ነበር። በኮቪድ እና በክትባቱ ላይ ያተኮረውን ጉባኤ በበይነ መረብ አማካይነት 12 ሺህ ሰዎች ታድመውበታል።

ሁለተኛው ደግሞ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ኪጋሊ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን ከ14 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት ሲሆን በአካል የተገኙት 2800 ቀሪዎቹ ደግሞ በበይነ መረብ አማካይነት ነበር።

ሦስተኛው ደግሞ ዛምቢያ ሉሳካ ውስጥ ተካሂዶ ከ35 ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸው ሲነገር ከመካከላቸው 5,100 ያህሉ በአካል ከ30 ሺህ የሚልቁት በበይነ መረብ የተሳተፉበት ነው።

አራተኛው ደግሞ በደቡብ አፍሪካዋ ደርባን ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ 17 ሺህ የሚሆኑ ተሳታፊዎች በጉባዔው ላይ ታድመው ነበር።

አሁን በአዲስ አበባ የሚካሄደው አምስተኛው ጉባዔ ከቀደሙት ሁሉ በተሳታፊዎች ብዛት፣ በሚቀርቡ የምርምር ጥናቶች፣ በሚካሄዱ ተጓዳኝ ኹነቶች እና በሚቀርቡ ትዕይንቶች ብዛት ሁሉ ከቀደሙት በከፍተኛ ቁጥር ያላቀ በመሆን በጉባዔው ታሪክ ግዙፉ እንደሚሆን ተነግሯል።

በጉባዔው ላይ ንግግር የሚያደርጉ ተሳታፊዎችን በተመለከተ ከአዘጋጆቹ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ከከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የቡሩንዲው ፕሬዝዳንት ኤቫሪስ ንዳሽሚዬ፣ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ እና የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ጂን ካሲያ ይገኙበታል።

በተጨማሪም በጉባዔው ላይ የተለያዩ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ፖሊሲ አውጪዎች የሚሳተፉ ይሆናል። በዚህም የተለያዩ የአፍሪካ አገራትን በመወከል ከ58 በላይ የጤና ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣናት የሚገኙ ይሆናል።

እንዲሁም ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከሌሎችም የተለያዩ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት የሚወከሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የጉባዔው ይፋዊ መረጃ ያመለክታል።

ሳይንቲስቶች፣ የፈጠራ ባለሙያዎች፣ ከ125 በላይ የክትባት አምራቾች እና የኤአይ ተቋማት፣ የግል ዘርፍ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች እና ወደ አራት ሺህ የሚደርሱ ወጣት ባለሙያዎች እንዲሁም 200 የሴቶች መሪዎች የጉባዔው ተሳታፊ ናቸው ተብሏል።