በሊቢያ ወደብ የሩሲያ መርከብ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ባለሥልጣናት ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሊቢያ ቤንጋዚ የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር መልሕቋን ጥላ የነበረች የሩሲያ መርከብ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን የምሥራቅ ሊቢያ መንግሥት አስታወቀ።

ፍንዳታው የተከሰተው እሁድ ንጋት ላይ ወደ ሩሲያ እየተመለሰች የነበረችው መርከብ ነዳጅ እና የተለያዩ አቅርቦቶችን ለመሙላት በቆመችበት ሰዓት እንደሆነ የሊቢያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የምሥራቁን መንግሥት በመጥቀስ ዘግቧል።

በጥቃቱ ሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱን የወጣው መግለጫ ያመለክታል። ሞስኮው ስለ ክስተቱ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

የሊቢያ ጤና ሚኒስትር በበኩሉ፣ በትናንትናው ዕለት በቤንጋዚ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ጥቃት ከተፈጸመባት ሌላ የንግድ መርከብ ላይ የመጡ የቆሰሉ ሰዎችን መቀበሉን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል። ግለሰቦቹ የደረሰባቸው ጉዳት ቀላል መሆኑን እና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ በደረሱት ጥቃቶች የተነሳ "ከፍተኛ ስጋት" እንደፈጠረበት ገልጿል። "አፋጣኝ፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ" እንዲካሄድም ጠይቋል።

ተልዕኮው፣ "ሊቢያ የውጭ ግጭቶች የፍልሚያ የጦር ሜዳ መሆን አትችልም፤ መሆንም የለባትም» ሲል በኤክስ ገጹ ላይ አስፍሯል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፉ እና ቢቢሲ ቬሪፋይ ትክክለኛነታቸውን ያረጋገጣቸው ቪዲዮዎች፣ ጠዋት ላይ የተመታችው መርከብ በእሳት ተይይዛ እና ጭስ ሲወጣ አሳይተዋል። ከፕላኔት ላብስ የተገኘ የሳተላይት ምስል ደግሞ ቤንጋዚ ወደብ ላይ አንዲት መርከብ በእሳት ስትቃጠል ያሳያል።

በአሜሪካ የሚገኘው ቫንቶር የተባለ የደኅንነት መረጃ ተቋም የሰበሰባቸው ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስሎች ቅዳሜ ዕለት 'ፕሮጀክት 20380 ስቴሬጉሽቺ-ክላስ ኮርቬት (ሜርኩሪ)' የተባለች የሩሲያ የጦር መርከብ በወደቡ ላይ ቆማ እንደነበር ያመለክታሉ።

እሁድ ዕለት የተነሳው ምስል ደግሞ የዚያችው መርከብ አብዛኛው ክፍል እንደተገለበጠ እና የፊት ክፍሏ ብቻ እንዳልሰመጠ ያሳያል።

መቀመጫውን በምሥራቅ ሊቢያ ያደረገው የብሔራዊ መረጋጋት መንግሥት በበኩሉ፣ በስም ያልጠቀሳት አንዲት የሩሲያ መርከብ ከዚህ ቀደም በተፈጸመው የማሪታይም ስምምነት መሠረት የቤንጋዚ ወደብን ስትጠቀም እንደነበር ገልጿል።

የእሁዱ ክስተት ምርመራ እየተደረገበት መሆኑ መሆኑን ገልጿል። ባለሥልጣናት የጥቃቱን መነሻ እና ተጠያቂውን አካል ለመለየት ከሩሲያ አቻዎቻቸው እየሰሩ እንደሆነም አክሏል።

የምሥራቁ መንግሥት፣ በሊቢያ ወደብ የቆመችው መርከብ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ያወገዘ ሲሆን ድርጊቱን የማሪታይም ደኅንነት ጥሰት እና በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ጥቃት ሲል ገልጾታል።

ሊቢያ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትም ሆነ ከድንበሯ ውጭ ያለ የማንኛውም ሌላ ግጭት አካል አለመሆኗን አስታውቋል።

በሌላ በኩል፣ ትሪፖሊ የሚገኘው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው የሊቢያ መንግሥት በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በኩል ባወጣው መግለጫ፣ የውጭ ኃይሎችን ማስተናገድ እና ተቋማትን እንዲጠቀሙ መፍቀድ አደገኛ መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቋል።

እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ "ወደቦችን እና የሲቪል ተቋማትን ከውጭ ግጭቶች ጋር በተያያዙ ተግባራት ውስጥ ማሳተፍ" ሊያመጣው የሚችለው አደጋ "ከፍተኛ ፍርሃት" እንደፈጠረበት ገልጿል።

"የዜጎችን ሕይወት እንዲሁም ብሔራዊ ተቋማት እና ንብረቶች ደኅንነት ስጋት" ላይ እንደሚጥልም አስረድቷል።