ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በተስፋ እና በስጋት ወደ መደበኛ ሕይወት እየተመለሱ ያሉት የትግራይ ከተሞች
መስከረም 13/2018 ዓ.ም. ትግራይን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ግጭት ሲቀሰቀስ፣ የክልሉ ነዋሪዎች ለሁለት ዓመት ከተካሄደው እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ከሚነገርለት ጦርነት ቁስል ገና አላገገሙም ነበር።
ከአስር ቀን በኋላም የህወሓት መሪዎች እና ተዋጊዎቻቸው ከዋና ከተማዋ መቀለ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ጦር እና የትግራይ የሰላም ኃይሎች ከተሞችን ተቆጣጥረው የሰላም እና ደኅንነት ሁኔታን ለማሻሻል እየሞከሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንዳንድ የትግራይ ከተሞች ነዋሪዎች በመረጋጋት እና በደኅንነት ረገድ መሻሻል ቢኖርም ስለ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታ ስጋት አለን ብለዋል።
የፀጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል?
በግጭቱ ወቅት በመቀለ፣ በአዲግራት እና በሽረ ብዙ የግል እና የመንግሥት ተቋማት መዘረፋቸውን እና መውደማቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ዘረፋው በተለይም በዋና ከተማዋ የበረታ ሲሆን ቀስ በቀስ በሌሎች ከተሞች ተስፋፍቶ ነበር። በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውድመት ደርሶባቸዋል።
ሆኖም ነዋሪዎቹ የፀጥታ ኃይሎች በአንዳንድ የትግራይ ከተሞች ከገቡ በኋላ፣ ፖሊስ ወደ ሥራ መመለሱን ተናግረዋል።
የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ፍሩት ማዓር፣ ዝርፍያው እና ፍርሃቱ እንደቀነሰ እንዲሁም ሁኔታው አሁን የተረጋጋ እንደሆነ ትናገራለች።
በሴቶች የፀጉር ሳሎን ሥራ የምትተዳደረው ፍሩት "የትግራይ የሰላም ኃይሎች እና የመከላከያ ሠራዊት ከገቡ በኋላ የተሻለ መረጋጋት አለ" ካለች በኋላ፣ በአሁኑ ወቅት ምንም ሥራ የለም ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ግጭቱ ከመከሰቱ በፊት ሁለት ሴቶችን እና ሁለት ወንዶችን ቀጥራ ታሠራ ነበር።
ሁለቱ ወንዶችን ማሰናበቷን የምትናገረው ፍሩት ሁለቱ ሴቶች አሁንም ከእርሷ ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ገልጻለች።
"በግጭቱ ከነበረው ሁኔታ አሁን ይሻላል፤ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ገንዘብ የላቸውም፤ ሞራልም የለም። ስለዚህ ምንም ሥራ የለም ማለት ይቻላል።"
ፍሩት ያም ሆኖ በመቀለ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ መኖሩን ትናገራለች።
"ባለው ሁኔታ ሕዝቡ የተከፋፈለ ስሜት አለው። ደስተኛ የሆነ ሰው አለ። የሚጨነቅም አለ። ቆይቶ ምን ይፈጠር ይሆን? በሰላም እንኖር ይሆን? የሚል ስጋት አለ።"
ፍሩት አክላም በከተማዋ መውጫዎች አካባቢ ሽፍቶች በመኖራቸው ስጋት እንደፈጠሩ ጨምራ አስረድታለች።
የሽረ እንዳሥላሴ ነዋሪ የሆነው ዓወት በበኩሉ ከመንግሥት አገልግሎቶች በስተቀር ሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን እንደተጀመሩ ተናግሯል።
"ብዙ ሰዎች ወደ ሥራቸው እየተመለሱ ነው፣ ገበያው በአንጻራዊ ሁኔታ እየተረጋገ ይመስላል፤ ባንኮች ክፍት ናቸው፤ ገንዘብ [ካሽ] የለም እንጂ ሌሎች አገልግሎቶችን እየሰጡ ነው።"
ነጋዴዎች ለደኅንነታቸው በመፍራት እቃዎቻቸውን ወደየቤታቸው አጓጉዘው የነበረ ሲሆን፡ አሁን ወደ ሱቃቸው እየመለሱ መሆናቸውንም ተናግሯል።
የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎቶችም እየሠሩ መሆናቸውን ጨምሮ ገልጿል።
በትግራይ አብዛኞቹ አካባቢዎች ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ በኋላ የባንክ፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠው እንደነበር ይታወሳል።
የገበያ እና የሸቀጦች የዋጋ መናር
የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሲሚንቶ ነጋዴ የአካባቢጣቸው ደኅንነት ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሰ ነው በሚለው ሃሳብ ቢስማሙም፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ግን መኖሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌሎች የውቅሮ፣ የአዲግራት፣ የመቀለ እና ሽረ ከተማ ነዋሪዎች ግን ከጦርነቱ በኋላ የመሠረታዊ እቃዎች ዋጋ ላይ ቅናሽ አለመታየቱን ተናግረዋል።
አንዳንዶች በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ እና እየተባባሰ የመጣውን ድህነትን እንደ ዋና ምክንያት ይጠቅሳሉ፤ ሌሎች ደግሞ የትራንስፖርት ችግሮችን መንስኤ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የፍራፍሬ አምራቾች ከከተማው ውጭ ባሉ መግቢያዎች ላይ ሌቦች እንዳሉ እና ገበሬዎች ከገጠር ወደ ከተማው በመኪና ጭነው ሲገቡ እንዳይዘርፏቸው እንደሚፈሩ ፍሩት ትናገራለች።
በዚህም ምክንያት የገበያ ዋጋ ብዙም መረጋጋት እንዳላሳየ አስረድታለች።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፣ ባለ 5 ሊትር ዘይት በ2,000 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ አንድ ኩንታል ጤፍ ደግሞ 14000 ብር እየተሸመቱ ይገኛል።
የትራንስፖርት እና የነዳጅ ዋጋ
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁሉም ነዋሪዎች የፌደራል ኃይሎች የትግራይ ከተሞችን ከተቆጣጠሩ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ማሳየቱን ይናገራሉ።
የሽረ ከተማው ነዋሪ ዓወት የነዳጅ ዋጋ በሊትር ከአንድ ሺህ ወደ 400 ብር ወርዷል ብሎ በተለይ በከተማ አካባቢዎች የሕዝብ ትራንስፖርት ጀምሯል ብሏል።
ነገር ግን ከከተማ ወደ ከተማ ወይም ከወረዳ ወደ ወረዳ የሚደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ያለው ችግር ሙሉ በሙሉ አልተፈታም።
ግጭቱ ሙሉ በሙሉ ባልጠፋባቸው እና ከኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙት ከተሞች አስተማማኝ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጠቅሰዋል።
በዚህም ምክንያት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሚደረገው እንቅስቃሴ ውስን መሆኑን ይናገራሉ።
የሽሬ ነዋሪ የሆኑት ዓወት በትራንስፖርት ላይ ከፍተኛ መስተጓገል እንዳለ ጨምረው ተናግረዋል።
"አሁንም በትራንስፖርት ላይ እንግልቶች አሉ። በአንዳንድ ቦታዎች በተለይም ከወረዳ ወረዳ ለትራንስፖርት ክፍት ያልሆኑ ቦታዎች አሉ" ያሉት ዓወት አንዳንድ የተኩስ ድምፅ እንደሚሰሙ ተናግረዋል።
ረቡዕ ዕለት "መድፎች ከከተማ ወደ ገጠር ሲተኮስ ሰምተናል፤ በአንዳንድ ገጠር አካባቢዎች [ታጣቂዎች] እንዳሉ ጥርጣሬ አለ" ብለዋል።
በአዴት እና ዛና አካባቢዎች እንዲሁም በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ የሰመማ አካባቢዎች የመድፍ ተኩስ ሰምተናል ይላሉ።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአዲግራት ነዋሪ ከኢሮብ እና ከሌሎች የድንበር አቅራቢያ አካባቢዎች ወደ ከተማው የሚመጡ ሰዎች እንደሌሉ ገልጸዋል። ይህም ከደኅንነት ስጋት ጋር የተያያዘ ነው ብለው ያምናሉ።
"የነዳጅ ዋጋ ቀንሷል፣ ነገር ግን ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተመን ባለመውጣቱ ምክንያት እንቅስቃሴ በአግባቡ አልተጀመረም። ያለው እንቅስቃሴም በአሽከርካሪ እና በመንገደኞች ስምምነት የሚደረግ ስለሆነ ለአብዛኛው ተጠቃሚ አስቸጋሪ ነው።"
የመንግሥት መዋቅሮች መመለስ
የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም. የትግራይ ክልልን ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚያስተዳድር አምስት አባላት ያሉት 'የባለአደራ አስተዳደር' መቋቋሙን አስታውቋል።
ይህ እርምጃ በአስተዳደር እና በፀጥታ ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመፍታት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአንዳንድ የትግራይ ክፍሎች የአካባቢ አስተዳደሮችን የመምረጥ ሂደት ተጀምሯል።
ረቡዕ ዕለት በአዲግራት ከተማ የአስተዳዳሪዎች ምርጫ መደረጉን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ግለሰብ ተናግረዋል።
ከተማዋን እንዲያስተዳድሩ አምስት ሰዎች መመረጣቸውን እና ምርጫው የሚካሄደው ከሕዝቡ በቀጥታ ጥቆማ በመቀበል እንደሆነ ተናግረዋል።
ነዋሪዎች በምርጫ ሂደቱ ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች መኖራቸውን ቢናገሩም፣ ይህ ግን በክልሉ ያለውን የአስተዳደር ክፍተት ወደነበረበት ለመመለስ በጣም ጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።
ሽረ እና አድዋን በመሳሰሉ ከተሞች የከተማ አስተዳደር ምርጫ ገና አልተጀመረም።
ነገር ግን በሽረ የአገር ሽማግሌዎች ከትግራይ የሰላም ኃይሎች ጋር በመተባበር አብረው እየሠሩ እንደሆነ እና የፀጥታው ሁኔታም የተረጋጋ መሆኑን ቢቢሲ ሰምቷል።
ነዋሪዎች ምን ተስፋ ያደርጋሉ?
የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው በሽረ ያለው ሁኔታ ነዋሪዎች የተረጋጋ ነው ብለው ቢያምኑም ግጭቱ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
"ተስፋችን ሁሉም ነገር ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመለስ ነው። በማኅበረሰቡ ውስጥ የመሰላቸት ሁኔታ አለ" ሲሉ ከቀደመው ጦርነት ጋር በማነጻጽር አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
"አሁን እንደበፊቱ አይደለም፤ ነገሮች በጣም ተለውጠዋል፤ ሰዎች አሁን ወደ ሥራ እየተጣደፉ ነው። ከዚህ በፊት ገንዘብ፣ መድኃኒት እያዋጣን [ታጣቂዎች] ወዳሉበት በመውሰድ የመደገፍ ጥረት ነበር። አሁን እንዲህ የሚባል ነገር የለም።"
በዚህም ምክንያት አሁን ከተሞቹን ለማስተዳደር እየተረከበ ያለው ኃይል ተረጋግቶ ሥራውን ሊቀጥል ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው።
የመቀለ ከተማ ነዋሪዋ ፍሩት የተራዘመ ግጭት ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት አላት።
"የምንመኘው ሰላም ሊዘገይ እንደሚችል አስባለሁ፡ ምክንያቱም እነሱ [ህወሓት] አርፈው አልተቀመጡም፤ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። ኅብረተሰቡ ፖለቲካ ሰልችቶታል።
"ማንም ቢመጣ መሥራት እና መኖር እንፈልጋለን፤ ብልጽግና ወይም ሌላ አካል ቢመጣ፣ ሠርተን ለመግባት ሰላም እንፈልጋለን፤ ልጆቻችንን ለማሳደግ እና የቤት ኪራይ ለመክፈል ሰላም እንልጋለን።"