ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህወሓት እንዴት በፍጥነት ሊያፈገፍግ ቻለ? በቀጣይስ ምን ሊፈጠር ይችላል?
የትግራይ ክልል ግጭት መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ዳግም ካገረሸ ከ10 ቀናት በኋላ መስከረም 23 ነበር የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች መዲናዋን መቀለን ለቅቀው የወጡት። በቀጣይ ቀናትም ጥሎ አብዛኛውን የክልሉን አካባቢዎች ለየኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ለአጋሮቹ ለቅቀው ወጥተዋል።
ከሌሎች ስድስት አማጺያን ጋር በይፋ፣ እንዲሁም ከኤርትራ መንግሥት ጋር ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ጥምረት የፈጸመው የህወሓት ኃይል እንዴት በአጭር ጊዜ ብዙ ከተሞችን ጨምሮ አብዛኛውን የክልሉን ክፍል ለቅቆ ሊወጣ ቻለ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ህወሓት ከተሞችን ያለውጊያ ለቅቆ የወጣው እና ያፈገፈገው በስልታዊ ወታደራዊ ውሳኔ ቢልም፣ የፌደዴራሉ መንግሥት ግን ጦርነቱን ማሸነፉን ገልጿል።
በትግራይ እየተካሔደ ያለውን ጦርነት በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙ ሦስት የፖለቲካ እና ወታደራዊ ተንታኞች፣ የህወሓትን "በፍጥነት ማፈግፈግ" እና በቀጣይ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
"የጠበቅነው እና ያልነው ነው የሆነው"
እየሆነ ያለው "የጠበኩት ነው" የሚሉት የህወሓት የቀድሞ ከፍተኛ አመራር እና በአሜሪካ በመምህርነት ያገለገሉት አቶ ብስራት አማረ፣ የህወሓት ኃይሎች ክልሉን በፍጥነት ለቀው ለመውጣታቸው ከድርጅቱ ውስጣዊ ችግሮች ጋር የተያያዙ ሁለት ዋነኛ ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ።
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ ህወሓት "ያለምንም ማቆሚያ ወደ ቁልቁል ነው የወረደው" የሚሉት አቶ ብስራት፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ደግሞ ውስጣዊ መፈራረስ እንደገጠመው ያስረዳሉ።
ድርጅቱ በውስጡ "ተሰነጣጥቆ እና ፈራርሶ" ፖለቲካዊ ኃይሉ መከፋፈሉ በጦርነቱ እየታየ ላለው "ፈጣን ማፈግፈግ" አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ። በዚህ ክፍፍል ሳቢያ ፓርቲውንም ሆነ ክልሉን "መምራትም ሆነ ማስተዳደር አልቻለም" ይላሉ አቶ ብስራት።
ፓርቲው ተከፋፍሎ "ግማሹን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ይዞት ሄዷል። ወለዶ የሚባል ሌላ ድርጅትም ተፈጥሯል። መጨረሻ ላይ የቀረው እነ ደብረፅዮን (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር የሚመሩት ከሕዝብ የተገለለ የተወሰ ኃይል ነው" ይላሉ።
የፖለቲካ ኃይሉን ክፍፍል ተከትሎ የመጣው ሁለተኛው ምክንያት የክልሉ ታጣቂ ኃይል በሁለት መከፈሉ ነው። ታጣቂውን ሲመሩ የነበሩ ጄነራሎች ህወሓትን በተመለከተ ሁለት የተለያየ አቋም በመያዝ ወደ መከፋፈል አምርተዋል።
አንዱ ወገን "ይህ ድርጅት የኛ ነው፤ መፍረስ የለበትም" በማለት የህወሓት ጠባቂ ሆኖ መቀጠሉን የሚገልጹት የቀድሞው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አቶ ብስራት፣ የተቀሩት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ደግሞ "እኛ የአንድ ድርጅት አይደለንም" በማለት በተቃርኖ መቆማቸውን አንስተዋል። ይህም የክልሉን ታጣቂ ኃይል ለሁለት በመክፈል 'የትግራይ ሰላም ኃይል' የተባለ ፀረ-ህወሓት ታጣቂ ቡድን እንዲፈጠር አድርጓል።
ህወሓት አብሮት ከነበረው አቋም ሳይላቀቅ ዘመኑን የሚመጥን አስተሳሰብ ማራመድ እንዳልቻለም የሚተቹት አቶ ብስራት፣ "ይዞት የነበረውን የቆረቆዘ አመለካከት እንደያዘ ቀጥሎ በዚያው መሞትን መርጧል" ይላሉ።
የትግራይ ሕዝብም ፓርቲውን እንደተቃወመው አቶ ብስራት ገልጸዋል። እነዚህ ሁኔታዎች ተደማምረው ህወሓትን አቅም እንዳሳጡት ሲያስረዱም "ህወሓትን ለዚህ ያበቃው የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
እናም ጦርነት ከተጀመረ እንደቀድሞው "ሳይንዛዛ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል" የሚል እምነት አስቀድሞ እንደነበራቸው የተናገሩት አቶ ብስራት አማረ፣ "የጠበቅነው እና ያልነው ነው የሆነው" ሲሉ እምነታቸውን ያፀናሉ። "ከተሞች እኮ ያለውጊያ ነው የተያዙት፤ የቀረው ሻዕቢያ ያለበት አካባቢ ነው" ሲሉም ሁኔታውን አስረድተዋል።
ሌላው የዩኒቨርስቲ መምህር እና የፖለቲካ ተንታኝ ጌትዬ ትርፌም (ዶ/ር) ህወሓት በፍጥነት ለማገግፈጉ በአብዛኛው ከአቶ ብስራት ጋር የሚስማሙ ምክንያቶችን አንስተዋል።
እነዚህ ምክንያቶች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የህወሓትን "የአቅም ማነስ" የሚያሳዩ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ጌትዬ፣ "ህወሓት በአራት መመዘኛዎች ወድቋል" የሚል እምነት አላቸው።
ከእነዚህም የመጀመሪያው ከፌዴራል መንግሥቱ አንጻር ሲታይ "ጦርነት የመምራትም ሆነ የመሸከም አቅም የሌለው መሆኑ ነው" ይላሉ። የፓርቲው የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተከፋፍለው ግማሹ አዲስ አበባ መግባታቸው ህወሓትን ሲያዳክም፣ ለፌዴራሉ መንግሥት ደግሞ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን ያብራራሉ።
ከዚህ ቀደም "በወታደራዊም ሆነ በፕሮፓጋንዳ ዘርፍ ለህወሓት የጎላ ሚና ተጫውተዋል የሚባሉ ሰዎች ከነአጃቢዎቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው አዲስ አበባ መጥተዋል። አሁን የቀሩት የጥቂት ሰዎች ስብስቦች ናቸው" ይላሉ።
አክለውም፣ የቀሩት የህወሓት አመራሮች "በፖለቲካም በዕድሜም ያረጡ እና ያረጡ ናቸው። አሁን ያለውን ዳይናሚክስ [ተለዋዋጭ ሁኔታ] የሚሸከም ብቃትም ቁመናም የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል። እናም በየጊዜው ከህወሓት የወጡ የጦር እና የሲቪል አመራሮች ፓርቲውን በቁሙ እንደቀበሩት ይቆጠራል" ብለው የሚያምኑት ዶ/ር ጌትዬ፣ አሁን የቀረው "አልሞት ባይ ተጋዳዩ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ የፓርቲው ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ኃይል ክፍፍል፣ የፌዴራል መንግሥት ካለው "የቴክኖሎጂ አቅም" ጋር ተዳምሮ ለህወሓት ኃይል "እጅግ አደገኛ ስጋት ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
እርሳቸው አንደሚሉት ሁለተኛው ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ለፓርቲው ድጋፍ መንሳቱ እና ጦርነት የሚባል ነገር "መስማት እና ማየትም አለመፈለጉ" ነው።
ሌላው ጦርነቱ "ዓላማና ግብ የሌለው መሆኑ ነው" የሚሉት ተንታኙ፣ በመሆኑም ህወሓት ታጣቂ ለመመልመል መቸገሩን ጠቅሰው፤ ያለው "አነስተኛ ታጣቂ ኃይልም ቢሆን አማራጭ ስላጣ እንጂ የመዋጋት ፍላጎት የለውም" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የዲፕሎማሲ ተቀባይነት ማጣት ሌላው የህወሓት ውድቀት ማሳያ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት እና በደርግ ዘመነ-መንግሥት በጦር መኮንንነት ያገለገሉት ደረጀ ሀዋስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የትግራይ ክልል አብዛኛው ክፍል በፍጥነት ከህወሓት እጅ ወደ ፌዴራል መንግሥት እጅ መግባቱ "ጠቅላላ ወታደራዊ ሁኔታውን ሊነግረን አይችልም" ባይ ናቸው።
ህወሓት በፍጥነት ያፈገፈገው በድክመት ብቻ ሳይሆን በራሱ ስልታዊ ውሳኔም ጭምር ሊሆን እንደሚችል መላምቶችን አስቀምጠዋል።
ከአራት ዓመት በፊት በነበረው ጦርነት የህወሓት ኃይሎች መሸነፋቸው ከተነገረ በኋላ አገግመው እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ መድረሳቸውን ለዚህ በማሳያነት ያነሳሉ።
በአሁኑ ጦርነት ህወሓት በፍጥነት ያፈገፈገበትን ምክንያት ሲዘረዝሩ፣ አንደኛው ምክንያት የህወሓት የውስጥ መፈራረስ ውጤት ሊሆን እንደሚችል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፈጣን የሆነ የማፈግፈግ እና የተቀናጀ ወታደራዊ ስልትን የተከተለ የመሆን ዕድል ሊኖረው እንደሚችል፤ አሊያም ሙሉ በሙሉ በጦርነቱ የመሸነፉ አመላካች እንደሆነ ይገልጻሉ።
ከእነዚህ መላምቶች ውስጥ የህወሓት መፈራረስ እና ከፓርቲው የተገነጠለው "በእነ ጌታቸው የሚመራዊ አንጃ" የፈጠረው ተፅዕኖ የጎላ እንደሆነ ያምናሉ።
የተገንጣዩ ቡድን አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በአንጻራዊነት በህወሓት የትግል ታሪክ ውስጥ ያላደጉ እና አዲስ ቢሆኑም፣ እነ ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳይ ግን ብዙ ተከታይ ያላቸው እንደሆኑ ዶ/ር ደረጀ ያነሳሉ። ይህም ከፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሩ ባሻገር እስከታች ድረስ ያለውን መዋቅር አፍርሶት ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ፣ ይህም የጦርነቱ ዓላማ ተዋጊዎችን ጨምሮ በተከታዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ ሳያደርግ እንዳልቀረም ይገምታሉ።
"በፓርቲው መዋቅር ታች ድረስ ተከታይ ያላቸው ከሆነ ይሔ ጦርነት አስፈላጊ ነው ብለው እነ ደብረፅዮን በሚያውጁበት ጊዜ ካድሬዎቹም በቲዲኤፍ አባልነት ተቀላቅለው ሲዋጉ የነበሩት ተዋጊዎችም 'አይደለም ይሔ ጦርነት የፖለቲካ ዓላማ የለውም እና ልንሳተፍ አንፈልግም' የሚል ምልክት ለነደብረፅዮን ካሳይዋቸው ከተሞችን ለቅቀው መውጣት አለባቸው ማለት ነው።"
ከተሞቹን የመልቀቁ ጉዳይ ሌላ ወታደራዊ ጉዳይ ሊኖረው ቢችልም ቅሉ፣ "በዚህ ፍጥነት ይሔን ያህል ሊገሰግሱ የቻሉበት ምክንያት በእኔ ግምት የፖለቲካው መፈራረስ ጥልቅ በመሆኑ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።
በቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል?
የፌዴራሉ መንግሥት ጦርነቱ በህወሓት ሽንፈት መጠናቀቁን ጠቅሶ፣ ለትግራይ ክልል የባለአደራ አስተዳደር መሥርቷል።
ማፈግፈጉ ስልታዊ የወታደራዊ እርምጃው አካል መሆኑን የገለጸው ህወሓት በበኩሉ፣ ውጊያውን በራሱ መንገድ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያዎች ስለመቀጠላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። የፌዴራሉ ጦር የህወሓት ታጣቂዎችን የመለቃቀም ሥራ እየሠራ እንደሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲገልጹ፣ ህወሓት በበኩሉ አሁንም ጦርነቱን እንደሚያሸንፍ በመግለጽ ላይ ነው።
የቀድሞው የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ብስራት አማረ፣ ህወሓት ከዚህ በኋላ "አብቅቶለታል" የሚል እምነት አላቸው።
ህወሓት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ያለፉት 51 ዓመታት የነበረው ሁኔታ እና አሁን ያለው ሁኔታ "ምንም ግንኙነት የለውም" የሚሉት አቶ ብስራት፣ በቀጣይ ወደ ዋሻ መግባት እና የሽምቅ ውጊያ ማድረግ የሚባል ነገር በምንም ተዓምር አይሠራም" ይላሉ።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያታቸው፣ ፓርቲው በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት አጥቷል የሚል ነው።
ህወሓት የውጊያ ስልቱን "ወደ ተንቀሳቃሽ ውጊያ" እንደቀየረ መግለጹን የሚያነሱት አቶ ብስራት፣ ከሽምቅ ውጊያ "ትንሽ ላቅ ያለ" እንደሆነ በጠቀስ ይህ የውጊያ ስልት "ተለቅ ተለቅ ያሉ ኃይሎችን ይዘህ በመረጥከው ቦታ በብዙ አካባቢዎች ማድረግ" ሲሆን ለዚህ ደግሞ በቂ ኃይል እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ።
ይሁን እንጂ "የትግራይ ወጣት በጭራሽ የጥይት ድምፅ መስማት የማይፈልግ ሆኗል" በማለት ህወሓት በቂ ኃይል እንደሌለው ያነሳሉ። በተጨማሪም የሽምቅ ውጊያ ያለሕዝብ ድጋፍ የትም እንደማያደርስ ያስረዳሉ።
በመሆኑም "ይሔ ድርጅት ላይመለስ ሔዷል፤ የማንሰራራት ዕድል የለውም" የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
"ወድቆ መነሳት የሚባል ነገር በዚህ ሰዓት የለም። ምክንያቱም በዓላማ ነው የወደቀው፤ በአመራር ነው የወደቀው፤ ጊዜ ነው የጣለው፤ ሕዝብ ነው እምቢ ያለው። በኃይል በማስፈራራት ወጣቶችን ወደ ጦርነት ለማስገባት አዋጅ ማውጣቱ ለዚህ ማሳያ ነው።"
በመሆኑም ይላሉ አቶ ብስራት፣ "ወደ ኤርትራ የሚሔዱ የተወሰኑ አመራሮች ይኖራሉ።" እነዚህን አመራሮች የኤርትራ መንግሥት መደራደሪያ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ይገልጻሉ። ሌሎቹ ግን "እጃቸውን ይሰጣሉ" ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
ከአመራሮች ውጭ ያሉ የህወሓት ታጣቂዎች ግን ወደ ኤርትራ ሊሄዱ የሚችሉበት ዕድል እንደሌለ የሚገልጹት አቶ ብስራት፣ ምክንያቱም "የኢትዮጵያ ምላሽ ሌላ ስለሚሆን" ኤርትራ እንደማትቀበል አስረድተዋል።
ዶ/ር ጌትዬም የህወሓት አመራሮች ወደ ኤርትራ ሊያቀኑ ይችላሉ በሚለው የአቶ ብስራት አስተያየት ይስማማሉ። ይህን የሚያደርጉትም "በትግራይ በረሃዎች እየተዋጉ የመቀጠል አቅም እና ቁመና ስለማይኖራቸው ነው።"
ህወሓትን ጨምሮ 7 ታጣቂዎች የመሠረቱት ትብብር ለኅልውና፣ ከታክቲካዊ ትብብር ባለፈ ስልታዊ መሠረት እንደሌለው የሚገልፁት ዶ/ር ጌትዬ፣ ታጣቂዎቹ ኃይሎች የፖለቲካ አጀንዳቸውን በትጥቅ ትግል እንፈታለን ብለው እንደ አንድ ስልት ቢነሱም እንኳን "ይሔ ጉዳይ ተጠልፎ ሌላ ኃይል ገብቶበታል" ይላሉ።
ምክንያታቸውም የውጭ ኃይሎች የሆኑት "ኤርትራ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከታጣቂዎቹ ጀርባ አሉ" የሚል ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን በቀጥታ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት የማስገባት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ገልጸዋል።
"መንግሥት ራሱን ያዘጋጀው ከታጣቂዎች ጋር ለመዋጋት አይመስለኝም፤ ለቀጣናዊ ጦርነት ነው። ቀጣናዊ ጦርነት አድርጎ በማሸነፍ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ የበላይነት ይዞ የጂኦግራፊ [መልክዓ መድራዊ] ለውጥ ሊያመጣ ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ደረጀ ደግሞ ከሁለቱ ተንታኞች በተለየ መልኩ የጦርነቱ ቀጣይ ቢሆኖች በህወሓት አሁናዊ ቁመና ላይ ብቻ እንደማይመሠረት ያብራራሉ።
የህወሓት ፖለቲካዊ ክፍፍል ተዋጊዎቹ ድረስ መውረዱን ከቀጠለ ለፓርቲው ዳግም ማንሰራራት ከባድ እንደሚሆንበት ገልጸው፣ ነገር ግን "በአዲስ አመራር እንደገና ሊዋቀር" የሚችልበት ዕድልም እንዳለ ይታያቸዋል።
ክፍፍሉ ወደታች ቢወርድ እንኳን የእነ ደብረጽዮን እና የእነ ጄነራል ጻድቃን ቡድን "በአገር ሽማግሌዎች በኩልም ቢሆን ቅራኔያቸውን ፈትተው ከፌዴራል መንግሥቱም ጋር ተስማምተው ሊኖሩም ይችላሉ" በማለት ደረጀ ሀዋስ (ዶ/ር) ግምታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።
በሌላ በኩል፣ የህወሓት ወታደራዊ ኃይል መልሶ ሊደራጅ እንደሚችልም ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ ከመሳሪያ እና ከወታደር ብዛት በተጨማሪ "በፖለቲካ ዓላማ፣ በዕዝ አንድነት እና በድርጅታዊ ፅናት የሚወሰን ነው" ይላሉ።
በጦርነቱ ውሰጥ ከተሞች የተለቀቁት በውጊያ እንዳልሆነ የሚገልጹት ዶ/ር ደረጀ፣ ይህም የህወሓት ኃይሎች ጉዳይ ከተኩስ ይልቅ ፖለቲካዊ ክፍፍል ጥላ ያጠላበት መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል። እናም "ያ ለሁለት የተሰነጠቀው ተመልሶ እንዴት እንደሚጠገን የምትሰጠው መልስ የወደፊቱንም ሊያሳይ ይችላል" ባይ ናቸው።
የትግራይ ውስጣዊ ክፍፍል ከተጠናከረ ግን፣ አሰላለፉን ተከትሎ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ፉክክር ሁለቱን አገራት ወደ ጦርነት ሊስብ እንደሚችል ያምናሉ። ይህ የጦርነት አዝማሚያ "አፋፍ ላይ እንደደረሰ" በማንሳት፣ አንዳች ስህተት ከተፈጠረ ሁለቱም እናሳካለን የሚሉት ዓላማ ስላላቸው ያለከልካይ እንደሚዋጉ አስረድተዋል። እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት የዲፕሎማሲ ጫና እንኳን ጦርነቱን ሊያስቆመው ይችላል የሚል እምነት የላቸውም።
የትግራዩን ጦርነት ዳግም ማገርሸት ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ የኤርትራን ዲፕሎማቶች ስታባርር ኤርትራ በምላሹ ከኢትዮጵያ ጋር ሙሉ በሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣለች።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ "ወረራ" እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በደብዳቤ አሳውቃለች።
ኤርትራ በምላሹ ለምክር ቤቱ በጻፈችው ደብዳቤ "ኢትዮጵያ ራስን በመከላከል ስም ጦርነትን ምክንያታዊ ልታደርግ ነው" ስትል ከስሳለች።