በአፍሪካ ትልቁ የእንስሳት ሀብት ባላት ኢትዮጵያ ሥጋ ለምን ለብዙዎች ቅንጦት ሆነ?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

በኢትዮጵያውያን የምግብ ባህል ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ሥጋ ዋጋው በመወደዱ ምክንያት ከብዙዎች ገበታ እየራቀ ይመስላል።

በተለይም በአዲስ አበባ የሥጋ ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በእጅጉ መጨመሩን ተከትሎ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሥጋ ቤቶችን ዋጋ በመቃወም ሸማቾች ግዢ እንዲያቆሙ የሚያሳስብ ጥረት እያደረጉ ነው።

እንቅስቃሴው የአንድ ኪሎ የበሬ ሥጋ ዋጋ 6ሺህ እና 7ሺህ ብር ደርሷል፤ ሻጮች ዋጋውን እስካልቀነሱ ድረስ መግዛት እናቆማለን የሚል ነው።

ሰዎችም አሁን ላይ ሥጋ መመገብ ብርቅ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ ምሬታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየገለጹ ይገኛሉ።

በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በቲክቶክ የሚሳተፈው ኤፍሬም አብዶ፣ በአዲስ አበባ የሥጋ ዋጋ ከሦስት ዓመት በፊት 2 ሺህ ብር አካባቢ ከነበረበት ወደ 7 ሺህ ብር መድረሱን ይናገራል።

በአዲስ አበባ የሥጋ ቤቶች ዋጋ የተለያየ እንደሆነም ኤፍሬም ያብራራል።

በአንጻራዊነት ርካሽ የሚባሉ የሥጋ ቤቶች ቀደም ሲል 700 እና 800 ብር አካባቢ ይሸጡት የነበረው አንድ ኪሎ ሥጋ፣ አሁን ከ1600 ብር እስከ 2 ሺህ ብር መድረሱን እና ውድ የሚባሉት የሥጋ ቤቶች ደግሞ ከ5 ሺህ እስከ 7 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ ነው ይላል።

በአዳማ የፍየል ሥጋ ነጋዴ የሆኑት አቶ ኢፋ ዳቢ፣ በኑሮ ውድነቱ ምክንያት የደንበኞቻቸው ቁጥር በ70 በመቶ እንደቀነሰ ተናግረዋል።

አቶ ኢፋ ባለፉት ዓመታት የፍየል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የፍየል ሥጋ ዋጋ እንዲጨምር ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ለ10 ዓመታት በፍየል ንግድ ላይ እንደቆዩ የተናገሩት አቶ ኢፋ፣ በዚህ ወቅት አንድ ፍየል ከ5 ሺህ ብር ወደ 20 ሺህ ብር ከፍ ማለቱን አስረድተዋል። በዚህም በአዳማ የአንድ ኪሎ ግራም የፍየል ሥጋ ዋጋ 3500 ብር መድረሱን ገልጸዋል።

"ከ10 ዓመት በፊት በ100 ሺህ ብር የተሞላ የጭነት መኪና ፍየሎች እንገዛ ነበር፤ አሁን ግን በዚያው ገንዘብ ቢበዛ አራት ፍየሎችን ብቻ ነው መግዛት የሚቻለው" ይላሉ።

በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት እና የራሳቸውን ንግድ ያላቸው አቶ አስፋው፣ ቀደም ሲል ጓደኛሞች በቡድንም ሆነ በግል ተገናኝተው እርስ በርስ ሥጋ መገባበዝ የተለመደ እንደነበር ያስታውሳሉ። በጾም ወቅት ካልሆነ በስተቀር፣ እርሳቸው እና ጓደኞቻቸው ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ተገናኝተው ሥጋ ይመገቡ እንደነበር ይናገራሉ።

አሁን ግን በሥጋ ዋጋ መናር ምክንያት ከጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙበት ድግግሞሽ በወር ወደ አንድ ጊዜ መውረዱን ገልጸዋል። የሥጋ ዋጋ ከሰዎች የመግዛት አቅም ጋር ያለውን ልዩነትም አንስተዋል።

"ውድ ምግብ ቤቶችን ስንመለከት ቁጥራቸው ብዙ አይደለም። ነገር ግን በእነዚያ ቦታዎች ብዙ ሰዎችን ብናይም፣ አብዛኛው ሰው እዚያ ሄዶ ለመመገብ የሚያስችለው አቅም የለውም" ብለዋል።

አቶ አስፋው አክለውም፣ አሁን የሥጋ ዋጋ መናር ለእርሳቸውም ሆነ ለብዙ ሰዎች ዋነኛው ጭንቀት አለመሆኑን ገልጸው፣ እንደ ቤት ኪራይ ያሉ ወጪዎች በአሁኑ ወቅት የበለጠ ጫና እየፈጠሩባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የሥጋ ቤት ንግድ ዘርፍ በተለይ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ እድገት ያሳየ መሆኑን የሚገልጸው ሥጋ ቤቶችን በተለይም ቲክቶክ ላይ የሚያስተዋውቀው ተስፋ ነዳ ፣ በዚያን ወቅት በሆቴል እና በአጠቃላይ የመስተንግዶ ዘርፍ የንግድ እንቅስቃሴ በቀዘበት ሁኔታ ሥጋ ቤቶች አዲስ የንግድ አማራጭ ሆነው ብቅ ማለታቸውን ያስረዳል።

ከዚህ በፊት ሰዎች ለመገናኘት ካፌዎችን ይመርጡ እንደነበር፣ አሁን ግን ሥጋ ቤቶች ለመገናኛ እና ትልልቅ ውይይት ለማካሄድ ተመራጭ ቦታዎች እየሆኑ መምጣታቸውን ይገልጻል።

ሆኖም ሥጋ በኢትዮጵያውያን የምግብ ባህል ውስጥ ያለው ቦታ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ዋጋው ከሕዝቡ የመግዛት አቅም ጋር እየተመጣጠነ አይደለም የሚለው ተስፋ፣ ሥጋ የቅንጦት ምግብ ወደ መሆን ደረጃ ደርሷል ይላል።

ነገር ግን የሥጋ ዋጋ መናር በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ብቻ እንደማይፈታ እና የዘርፉን ተዋናዮች ያሳተፈ ውይይት እና ጥናት እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባል።

በከፍተኛ ዋጋ በሚሸጡት ሥጋ ቤቶች ላይ ተቃውሞ ያለው ኤፍሬም በበኩሉ እንቅስቃሴው በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ገልጾ፣ በብዙ ሥጋ ቤቶች የተጠቃሚዎች እንቅስቃሴ ቀንሶ እንደተመለከተም ይገልጻል።

ተስፋ እንደሚለው፣ በአዲስ አበባ ጥራታቸው እና አገልግሎታቸው ጥሩ ነው የሚባሉ የሥጋ ቤቶች ቁጥር 50 አይደርስም። ይህም ከከተማዋ ሕዝብ ቁጥር አንጻር ዘርፉ ገና ብዙ የማደግ ዕድል እንዳለው ያመለክታል ይላል።

ከገበያ ከብት የሚገዙ ነጋዴዎች፣ በመካከል የሚገኙ ደላሎች፣ ከብትን ከአንድ ነጋዴ ወደ ሌላ የሚያስተላልፉ አቅራቢዎች እና በመጨረሻም ለሸማቹ የሚሸጡ የሥጋ ቤት ነጋዴዎች በሰንሰለቱ ውስጥ እንዳሉም ይጠቅሳል።

በመካከሉ ያሉ አቅራቢዎች እና ደላሎች ቁጥር መብዛት በዋጋ ላይ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ቢጠቁሙም፣ የትኛው የአቅርቦት ደረጃ ላይ ዋጋው እንደሚጨምር በጥናት መለየት እንደሚገባ ይጠቅሳል።

ከዚህ በተጨማሪ የከብቶች ዝርያ፣ ጥራት፣ አመጋገብ እና የማድለብ ሂደት የሥጋ ዋጋን ሊወስኑ የሚችሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ሁሉም የሚያነሳው ነው።

የከብት አቅራቢዎች ምን ያህል ከብት ማቅረብ እንደሚችሉ፣ ከእያንዳንዱ ከብት ምን ያህል ሥጋ እንደሚገኝ እና የሥጋ ቤቶች የአገልግሎት ወጪዎች ምን ያህል እንደሆኑ ተለይተው በመገምገም የዋጋ ምክክር ሊደረግ እንደሚችል ያስረዳል።

በዚህ ሃሳብ የሚስማማው ኤፍሬም በበኩሉ በገበያው ውስጥ ያለውን የንግድ ሰንሰለት በቴክኒክ የሚያጠኑ ባለሙያዎች ሲሳተፉበት በማለት እንደእሱ አስተያየት ግን አንድ ኪሎ ስጋ ከ800 ብር ጀምሮ እስከ 3 ሺህ ብር ድረስ ቢሸጥ ለተለያዩ ሸማቾች የሚያስማማ የዋጋ ክልል እንደሚሆን ይገምታል።

በከብት ንግድ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ ደላሎች የዋጋ ጭማሪው ላይ ሚና እንዳላቸው የሚያምነው ኤፍሬም፤በሰንሰለቱ መካከል ገብተው የገበያውን ሥርዓት የሚያዛቡ አካላት ከሰንሰለቱ መውጣትን እንደ አማራጭ ይመለከተዋል።

እንቅስቃሴው ከሥጋ ዋጋ በላይ የኑሮ ውድነትን የሚመለከት ሰፊ ውይይት እየፈጠረ ነው። መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች፣ የቤት ኪራይ እና ሌሎች የኑሮ ወጪዎች በማኅበረሰቡ ላይ ጫና እያሳደሩ በመሆናቸው እንቅስቃሴው ከዚህ ሊያልፍ እንደሚችል ያምናል።

አጠቃላዩ ግሽበት እና ሥጋ

በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት እና የፖሊሲ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄተስፋ በበኩላቸው የሥጋ ዋጋ መጨመር ከሰፊው የዋጋ ግሽበት ችግር ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ይላሉ። የብር ምንዛሪ መዋዠቅ፣ ግጭቶች እንዲሁም የምርት እና የሥርጭት ችግሮች ለዋጋ ጭማሪው አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

የዋጋ ግሽበቱን ከሚያባብሱ ምክንያቶች መካከል ትልቁ የብር ዋጋ መዋዠቅ እንደሆነ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ይናገራሉ። እንደ ምሳሌም፣ ከዚህ በፊት አንድ ዶላር ወደ 56 ብር ይመነዘር እንደነበርና በኋላ ከ160 ብር በላይ እንደደረሰ ጠቅሰዋል።

ይህም ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ያብራራሉ። ከውጭ የሚገቡ ምግብ ሸቀጦች፣ ዘይት፣ ስኳር እና የሕፃናት ምግብን ጨምሮ በርካታ ምርቶች የዚህ ተጽእኖ ሊደርስባቸው እንደሚችል ገልጸዋል።

ሌላው ለዋጋ ጭማሪ የሚያበረክተው ምክንያት ግጭቶች፣ የምርት እና የሥርጭት መስተጓጎሎች እንደሆኑ ያነሱት ባለሙያው በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች ማምረት ሲቸገሩ፣ ሌሎች አካባቢዎችም ምርታቸውን ወደ ከተሞች እና ዋና ዋና ገበያዎች ማድረስ ላይ እንቅፋት እንደሚገጥማቸው አስረድተዋል። እንደ ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶች ከዋና መጋዘኖች ወደ ገበያ የሚደርሱበት ሂደት መስተጓጎልም በምርት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጠቅሰዋል።

እነዚህን ሰፊ የኢኮኖሚ ችግሮች ተከትሎ፣ በተለይ የሥጋ ዋጋ እስኪቀንስ ድረስ ሥጋ አንበላም የሚለው እንቅስቃሴ ምን ያህል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚለው ጥያቄ ይነሳል።

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት፣ ከአገሪቱ ሕዝብ መካከል የሥጋ ዋጋውን መክፈል የሚችሉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። ቤተሰብን ማስተዳደር እና ዘመድን መርዳት ያለባቸው ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋዮች እንኳ፣ በዚህ ደረጃ ያለውን ወጪ ለመሸከም ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ያስረዳሉ።

በተጨማሪም ገበሬዎች በስልካቸው ብዙ የገበያ መረጃ ስለሚያገኙ፣ የደለቡ ከብቶችን በከፍተኛ ዋጋ ለመሸጥ እየተነሳሱ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ሆኖም ከብቶችን በራሳቸው አደልበው የሚሸጡ አርቢዎች የሚያቀርቡት ዋጋ ከገበያው ጋር የማይመጣጠንበት ሁኔታ እንዳለ ይናገራሉ።

የሸማቾች ማኅበራት በዚህ ዓይነት ሁኔታ የዋጋ ጭማሪን ለመቋቋም ጠቃሚ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችልም ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ያብራራሉ።

በኢትዮጵያም የሸማቾች ማኅበራት እየተቋቋሙ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ በተጠናከረ መልኩ ከተደራጁ የዋጋ ጭማሪን ለመቋቋም እና ነጋዴዎች የንግድ ሕጎችን እንዲያከብሩ ለማድረግ ሊረዱ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ከሥጋ ዋጋ በተጨማሪ፣ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት እና የምግብ ወጪዎች የዋጋ ግሽበትን ለመለካት ከሚያገለግሉ መሠረታዊ የወጪ ምክንያቶች መካከል ናቸው።

ዶ/ር ኮንስታንቲኖስ እንደሚሉት፣ አንድ ኪሎ ሥጋ ሰባት ሺህ ብር እየተሸጠ ነው በማለት ሕዝቡ መወያየቱ እና እንቅስቃሴ መጀመሩ ራሱ አስፈላጊ ጅማሮ እንደሆነ ያምናሉ።

ሆኖም መንግሥት የገበያ ኢኮኖሚን እስከተከተለ ድረስ በዚህ ዓይነት የዋጋ ጉዳይ ላይ በቀጥታ ጣልቃ የመግባት ዕድሉ ውስን እንደሚሆን ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ይገልጻሉ።

የሥጋ ቤቶችም የማኅበረሰቡን ጥያቄ በመስማት የዋጋ አወሳሰናቸውን እንዲገመግሙ ጫና ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል።

የሥጋ ዋጋ እንዲቀንስ የተጀመረው እንቅስቃሴ በቀጥታ ዋጋን ያወርዳል? የሚለው ገና የሚታይ ቢሆንም፣ ሸማቾች በጋራ መደራጀታቸው፣ የዋጋ ጭማሪን መጠየቃቸው እና የሸማቾች ማኅበራት መጠናከር በገበያው ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው ያምናሉ።

የሥጋ ዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ ንግድ እና ፀጥታ ቢሮዎች ከሥጋ ቤት ባለቤቶች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል። በውይይቱም በእርድ ከብት ግብይት ላይ የደላሎች ጣልቃ ገብነት የዋጋ መናር እንደሚያስከትል መነሳቱንም ንግድ ቢሮው አስታውቋል።

የከተማዋ የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ የሥጋ ዋጋ የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባ መግለጻቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ የፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው ሕገወጥ ደላሎዎችን ከገበያው ለማስወጣት እና ቁጥጥርን ለማጠናከር እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

እንዲሁም የሥጋ ቤት ባለቤቶች በማኅበራቸው በኩል ተወያይተው በአጭር ጊዜ የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከ70 ሚሊዮን በላይ ከብቶች፣ 95 ሚሊዮን በላይ በጎችና ፍየሎች፣ እንዲሁም 8 ሚሊዮን ግመሎች ያሏት በአፍሪካ ትልቁ የእንስሳት ሀብት ባለቤት አገር መሆኗን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

የእንስሳት ሀብት ዘርፉ ከአገሪቱ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 20 በመቶ ያህሉን የሚያበረክት ሲሆን፣ በመላ አገሪቱ ለሚገኙ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎችም የኑሮ መሠረት ነው።