ለሰባት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የአባትነት ጥያቄ በፍርድ ቤት ውሳኔ አገኘ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በሶማሊያ ፑንትላንድ ግዛት በቤተሰቦች መካከል ግጭት አስከትሎ ለበርካቶች ሞት እና ጉዳት ምክንያት የሆነው በአንድ ልጅ ላይ የተነሳው የአባትነት ጥያቄ በርፍድ ቤት ውሳኔ አገኘ።

ለዓመታት የውዝግብ እና ግጭት ምክንያት የሆነው ሁለት አባቶች ከአንዲት ሴት የተወለደን የ16 ዓመት ታዳጊን አባት ነን በማለት ያነሱት ጥያቄ ወደ ቤተሰብ ግጭት አምርቶ በርካቶች ከተገደሉ በኋላ ነው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠው።

የሶማሊያ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሁለቱ አባቶች የልጁ ይገባኛል ጥያቄ ጋር ተያይዞ በቤተሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰባት ሰዎች ተገድለው፣ 21 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

በፑንትላንድ ግዛት አስተዳደር ዋና ከተማ ጋልካዮ ከተማ የተሰየሙት ዳኞች ሦስት የእስልምና ሃይማኖት ሊቃውንትን ያካተተ ሲሆን፣ ለአባትነት ጥያቄው ውሳኔ የሰጡት በዘረ መል (ዲኤንኤ) ምርመራ ውጤት ሳይሆን የሰዎችን ምስክርነት በመስማት ነው።

ዳኞቹ ልጁን ለ13 ዓመታት በአባትነት ያሳደገው ፋራህ አዋሌ አሊን የአባትነት ጥያቄን ውድቅ በማድረግ ሊበን ታህሊል ሃጂ አደን የተባለው ግለሰብ የልጁ አባት መሆኑን መወሰናቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ለዓመታት አባትነታቸውን ለማረጋገጥ ሲጥሩ የነበሩት ሁለቱ "አባቶች" ውሳኔውን በፀጋ መቀበላቸውን ለዳኞቹ አሳውቀዋል።

ይህ የአባትነት ጥያቄ ጉዳይ በሶማሊያ ለረዥም ጊዜ በሰፊው ሲያነጋግር የቆየ ሲሆን፣ ዋነኛው ትኩረት የልጁ እናት በሆነችው ሃሊሞ ዩሱፍ ሞሐመድ ምስክርነት እና ከሁለቱ ወንዶች ጋር በነበራት ጋብቻ ዙሪያ በነበሩ ሁኔታዎች ላይ ያጠነጠነ ነበር።

ከውሳኔው በፊት ጉዳዮን ለሦስት ቀናት ሲመለከት በቆየው የፍርድ ሂደት ወቅት እናት ሃሊሞ፣ ችሎቱ አባትነቱን ካጸናለት ከሊበን ታህሊል ሃጂ አደን ጋር በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2006 እንደተጋባች እና ከአራት ዓመታት በኋላ እንደተለያዩ ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።

ከዚያም በኋላ በጥቅምት 2010 ከፋራህ አዋሌ አሊ ጋር ተጋብታ ጋብቻቸው ከሦስት ዓመታት በኋላ አብቅቷል ብላለች።

እናት ሃሊሞ ዩሱፍ ሞሐመድ ልጇ የሊባን መሆኑን በጽኑ እንደምታምን እና ከፋራህ ጋር ምንም ልጅ እንዳልወለደች ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።

ከዚህ በተጨማሪም ሁለት ምስክሮች ሃሊሞ ከሊበን ጋር በተፈጸመው ጋብቻዋ ላይ በአካል እንደተገኙ ለችሎቱ መስክረዋል።

አባትነቱ በዳኞች የተረጋገጠለት ሊበን ለዳኞቹ እንደገለጸው፣ ከሃሊሞ ጋር በተለያዩበት ወቅት ከእርሱ ማርገዟን ነግራው ነበር።

የሁለቱ አባቶች እና ቤተሰቦቻቸው ውዝግብ እና ግጭት መነሻ የሆነው ልጅም በቪዲዮ አማካይነት ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል የሊበን ልጅ መሆኑን ገልጿል።

የመጨረሻ ውሳኔያቸውን ሲያሳልፉ ዳኞቹ የምስክሮችን ቃል፣ የእናትን ምስክርነት፣ የልጁን ቃል እንዲሁም አባትነትን ለማረጋገጥ በእስልምና ሕግ የተደነገጉ መርሆችን መሠረት ማድረጋቸው ተገልጿል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ስለ ዘረ መል (ዲኤንኤ) ምርመራ ምንም አልጠቀሰም። ሆኖም ዲኤንኤ በመጠቀም የሁለቱን የአባትነት ጥያቄ በቀላሉ መለየት እየተቻለ ዳኞቹ እንዳልተጠቀሙበት የፑንትላንድ ጠበቆች ማኅበር ሊቀ መንበር ማህሙድ ሲዒድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ዲኤንኤ እውነታን ለማረጋገጥ ከሚያገለግሉ ዘዴዎች አንዱ ነው። ሆኖም በ100 በመቶ እርግጠኝነት ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ ሌሎች በቂ ማስረጃዎች ካሉ የግድ ወደ ዲኤንኤ ምርመራ መሄድ አያስፈልግም" በማለት ነገር ግን ጉዳዩ ባለፈባቸው የሕግ ሂደት መቋጫ አግኝቷል ብለዋል።

ፍርዱ ከተሰጠ በኋላ ልጁን ለ13 ዓመታት በአባትነት አሳደግኩ የሚለው ፋራህ የዳኞቹን ውሳኔ እንደሚያከብር ነገር ግን ልጁን ለማሳደግ ለዓመታት ያወጣው ወጪ ምን እንደሚሆን ጥያቄ አቅርቧል።

ልጁን ለዓመታት እንደ አባት እንደተንከባከበ በመግለጽም፣ በዚያ ጊዜ ውስጥ ያወጣውን ገንዘብ ውሳኔውን ያሳለፉት የሃይማኖት ሊቃውንት እና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲያጤኑት ጠይቋል።

በሌላ በኩል የአባትነት ጥያቄው የጸናለት ሊበን በክርክሩ ወቅት ከጎኑ ለቆሙ የሃይማኖት ሊቃውንት፣ ዘመዶቹ እና የልጁ እናት ሃሊሞን እና ቤተሰቧን በማመስገን፣ በሂደቱ ያሳዩትን ትዕግሥት አድንቋል።

አስካሁን ለተፈጠረው ነገር "ዛሬ ሁሉንም ይቅር ብያለሁ" በማለትም፤ የአባትነት ጥያቄ አቅርቦ ውድቅ የተደረገበትን ፋራህን በስም ጠቅሶ በሁለቱ ቤተሰቦች መካከል ያለው ውጥረት እንዲያበቃ ጥሪ አቅርቧል።

በዚህ የአባትነት ይገባኛል ጥያቄ ዙሪያ የተነሳው ክርክር በመካከለኛው ሶማሊያ በምትገኘው ጋልካዮ ከተማ ግጭቶች ተከስተው የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል በርካቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሁለት ዓመት በፊት አሁን አባትነቱ የተወሰነለት የሊበን ወንድም በታጠቁ ሰዎች ተገድሏል።

በወቅቱ የፑንትላንድ የሙዱግ ክልል አስተዳዳሪ የነበሩት ፋይሳል ሼክ አሊ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ይህ ግድያ ከልጁ አባትነት ዙሪያ ካለው ውዝግብ ጋር የተገናኘ ነበር።

የፑንትላንድ ግዛት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በአጠቃላይ ሰባት ሰዎች ተገድለው 21 ሰዎች ቆስለዋል፤ ሆኖም ቢቢሲ እነዚህን አኃዞች በራሱ ለማረጋገጥ አልቻለም።

ሊበን ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ እንደተናገረው፣ በግጭቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ሕዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

"ሰዎች ሞተዋል፤ ሰዎች ተጎድተዋል፤ ወላጅ ያጡ ልጆችም አሉ" በማለት፤ እራሱም የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦችን እና በግጭቱ የተጎዱ ሰዎችን እንደሚደግፍ ቃል ገብቷል።

ዳኞቹም ሁለቱንም ቤተሰቦች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንዲያከብሩ እና ከተጨማሪ ግጭቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ምንም እንኳን ፍርድ ቤቱ የልጁን አባትነት ጥያቄ በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ቢሰጥም፣ ተያይዘው ለተፈጸሙት ግድያዎች እና ጉዳቶች ተጠያቂነት እንዲሁም ፋራህ ያቀረበው የካሳ ጥያቄ እንዴት እንደሚመለስ ያለው ነገር የለም።