አልዛይመርስን ለማከም በስኳር እና ኤዲኤችዲ መድኃኒቶች ላይ ሙከራ ሊደረግ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ለአልዛይመርስ አዲስ ሕክምና ለማግኘት የሚደረገው ምርምር የሚወስደውን ጊዜ የሚያሳጥር የመድኃኒት ሙከራ በዩናይትድ ኪንግደም ተጀመረ።

በተመሳሳይ ወቅት የተለያዩ መድኃኒቶች ላይ ሙከራ የሚደረግ ሲሆን፤ ለዓይነት 2 የስኳር ሕመም እና ለትኩረት ማጣት ሕመም (ኤዲኤችዲ) የሚሰጡ መድኃኒቶች ይገኙበታል።

እነዚህ መድኃኒቶች መዘንጋት እና ለማሰላሰል መቸገርን ሊቀንሱ ይችላሉ በሚል ምርምር እየተደረገ ይገኛል። መድኃኒቶቹ ሕሙማኑ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ሊያግዙም ይችላሉ።

የሙከራው የመጀመሪያ ተሳታፊ የሆኑት የ67 ዓመቷ አንጅላ በክሲይ አልዛይመርስ እንዳለባቸው የተነገራቸው ያለፈው ታኅሣሥ ላይ ነው።

'AD-SMART' የሚል ስያሜ በተሰጠው ሙከራ የሚሳተፉት አንጅላ "በቤተሰባችን አልዛይመርስ አለብን። እናቴ እና አክስቶቼም አለባቸው። አልዛይመርስ እንዳለብኝ ሲነገረኝ ከመደንገጥ ይልቅ ተበሳጨሁ። ሕይወቴን እንደሚገድበው አውቃለሁ" ይላሉ።

አንጅላ "ቢሆንም ግን በሽታው መገለጫዬ እንዲሆን አልፈቅድለትም" ይላሉ። ሙከራውን መቀላቀላቸው ብርታት እንደሰጣቸውም ይገልጻሉ።

"ዝም ብሎ ቁጭ ከማለት ቢያንስ አንድ ነገር እያደረግኩ ነው። ለራሴ በመቆም እየታገልኩት ነው።"

አልዛይመርስ የዳይሜንሽያ (የመርሳት ሕመም) ዓይነት ነው። በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ 600,000 ሰዎች ሕመሙ አለባቸው።

ባለፈው ወር አባታቸውን በአልዛይመርስ ያጡት የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም፤ የሚወዱትን ሰው በበሽታው መነጠቅ ምን ማለት እንደሆነ እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

በሽታው ቤተሰቦች ላይ የሚያሳድረውን ጫና እንደሚገነዘቡ ገልጸውም "ሙከራው በዩኬ በመጀመሩ ኩራት ይሰማኛል። ዘመነኛው ሕክምና በተቻለ ፍጥነት ለሕሙማን ይደርሳል" ብለዋል።

በዚህ ሙከራ የተለያዩ መድኃኒቶች እና የሕክምና ስልቶች በተመሳሳይ ወቅት ይከናወናሉ።

በሙከራው የሚሳተፉ አልዛይመርስ ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ሙከራዎች በተለየ ሁኔታ መድኃኒት የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። ውጤት የማያሳይ መድኃኒት ከሙከራው ወጥቶ በሌላ ሕክምና ይተካል።

እንዲህ ያለ ምርምር በካንሰር እና የአንጎል ነርቭን በሚጎዳው ሞተር ኒውሮን ሕመም ላይ ተሞክሯል።

ሙከራ የሚደረግባቸው መድኃኒቶች ለዓይነት 2 የስኳር ሕመም የሚሰጠው ሜትፎርሚን እና ለትኩረት ማጣት ሕመም (ኤዲኤችዲ) የሚሰጠው አንቶሞክቲን ናቸው።

መድኃኒቶቹ የተመረጡት በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን መሆኑ ተገልጿል።

አንጎል ላይ የሚፈጠር መለብለብ (ኢንፍላሜሽን) የሚያስከትለውን የኒውሮኖች ጉዳት ለመቀነስ ሊያግዙ እንደሚችሉ የምርምሩ ዋና ኃላፊ ፕ/ር ፔሬሽ ማልሆታ ይናገራሉ።

"ለረዥም ጊዜ የአልዛይመርስ ምርምር በአንድ መድኃኒት፣ በአንድ ሙከራ እና በአንድ መልስ ዙሪያ ሲያጠነጥን ነበር። የትኛው መድኃኒት ይሠራል የሚለውን ለማወቅ አሥርታት ሊወስድም ይችላል" ሲሉ እስካሁን የነበረውን አካሄድ አስረድተዋል።

"በካንሰር እና ሌሎችም ሕመሞች ላይ በተደረጉ ምርምሮች የተገኙ ውጤቶችን ወስደን የአልዛይመርስ ሕክምናን ለማሻሻል አውለናል" ብለዋል።

መድኃኒቶቹ ውጤታማ መሆናቸው የሚረጋገጠው የሕሙማንን የማሰላሰል እንዲሁም የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የማከናወን አቅም ካሻሻሉ ነው።

ከውስን አልዛይመርስ እስከተባባሰ የሕመሙ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወደ 1,200 ሰዎች በሙከራው ይሳተፋሉ።

መድኃኒቶቹ ላይ የሚደረገው የመጀመሪያ ዙር ሙከራ በአውሮፓውያኑ 2030 እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ሕሙማኑ የአእምሮ ብቃት ፈተናን ጨምሮ ሌሎችም ሙከራዎች ይደረጉላቸዋል።

የአንጅላ ባለቤት ስቲቭ በሙከራው ተሳታፊ ናቸው።

"በዚህ ሙከራ መሳተፋችን ከሕመሙ ማገገም አይቻልም ከሚል ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አውጥቶናል" ይላሉ።

በዩኬ የአልዛይመርስ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሼዎና ስኬልስ "አልዛይመርስ ላለባቸው ሰዎች ጊዜ ውድ ነው። ተጨማሪ የሕክምና መንገዶች ያስፈልጋሉ" ይላሉ።

የዩኬ የአልዛይመርስ ምርምር ተቋማት በሚመሩት ምርምር ውስጥ የአገሪቱ ብሔራዊ ጤና ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም ቡድኖች ይሳተፋሉ።