ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዜሌንስኪ በስታርሊንክ ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ኢሎን መስክ እና አሜሪካን ተማጸኑ
ለዩክሬን ቁልፍ የሆነው ስታርሊንክ የኢንተርኔት ትስስር ፍጥነቱ በመቀነሱ ምክንያት የሩሲያን ጥቃት ለመከላከል ከባድ እንደሆነ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተናገሩ።
አሜሪካ ለዩክሬን የምታቀርበው ስታርሊንክ ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳም ጠይቀዋል።
"ገደቡ ይነሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የዩክሬናውያንን ሕይወት እና የመሠረተ ልማት ደኅንነት ማስጠበቅ የምችለው በዚህ መንገድ ነው" ብለዋል።
ስታርሊንክ የሳተላይት ኢንተርኔት ሲሆን ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውል ስታርሺልድ የሚባል የኢንተርኔት ሥርዓትም አለው።
ኢሎን መስክ የሚያስተዳድረውን የስታርሊንክ ወታደራዊ ሥርዓት የአሜሪካ መንግሥት ለዩክሬን አቅርቧል።
ባለፉት ሳምንታት የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንደተዳከመ የገለጹት ዜሌንስኪ፤ የዩክሬን ባለሥልጣናት ከመስክ እና ከአሜሪካ ጋር በቅርበት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ለመስክ እና ለአሜሪካ መንግሥት "በትክክለኛው የታሪክ ጥግ መቆም አለባችሁ" ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቢቢሲ ከስታርሊንክ እና ከዋይት ሀውስ አስተያየት ጠይቋል።
ዩክሬን ለመደበኛ የወታደሮች ግንኙነት ስታርሊንክን ትጠቀማለች። የአገሪቱን አየር ክልል ጥሰው የሚገቡ ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን ለማምከን ደግሞ ስታርሺልድ ጥቅም ላይ ይውላል።
የኢንተርኔት ትስስሩ ፍጥነቱ መቀነሱ መጀመሪያ ላይ የታወቀው ባሳለፍነው ጥቅምት ላይ ነበር። ስለ ክስተቱ መስክ እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተለያየ አስተያየት ሰጥተዋል።
ስታርሺልድን የሚቆጣጠረው የአሜሪካ መንግሥት ስለሆነ ጉዳዩ በቀጥታ እንደማይመለከተው መስክ ተናግሯል።
ትራምፕ በበኩላቸው ኃላፊነቱ የእሳቸው እንዳልሆነ ጠቅሰው ቢልየነሩ መስክ ኢንተርኔቱን "ይመልሰው" ብለዋል።
የስታርሊንክ ጉዳይ በዜሌንስኪ እና ትራምፕ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት አስከትሏል።
ዩክሬን በሩሲያ ነዳጅ ማጣሪያ ላይ የምታደርሰው ጥቃት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ እንዲንር ማድረጉን ትራምፕ ተናግረዋል።
ዩክሬን በበኩሏ እነዚህ ነዳጅ ማጣሪያዎች ዋነኛ የሩሲያ የገቢ ምንጭ በመሆናቸው ዒላማ እንዳደረገቻቸው አስታውቃለች።
ዜሌንስኪ እንዳሉት ስታርሺልድ ላይ በተጣለው ገደብ ምክንያት የዩክሬንን ድሮኖች ለማምከን ተቸግረዋል።
"አምካኝ ድሮኖቻችን በሰዓት 161 ኪሎሜትር ከተጓዙ በኋላ መቀጠል ስለማይችሉ ከሩሲያ ጄቶች እኩል መብረር አልቻሉም" ብለዋል።
የሩሲያ ጄቶች በኢራን ሻሐድ አምሳያ የተሠሩ ናቸው ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
"ገደቡ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው። ገደብ መጣል ማለት በግዳጅ የተያዙት ግዛቶቻችን የእኛ እንዳልሆኑ ዕውቅና መስጠት ነው" ብለዋል።
ዩክሬን የአሜሪካ ሠራሹ ፓትሪዮት ሚሳዔል እጥረት እንደገጠማት አስታውቃለች። ሩሲያ ይሄንን ክፍተት ዩክሬን ላይ ጥቃት ለማድረስ ተጠቅማበታለች።