ትዕግሥት አሰፋ ክብረ ወሰን በመስበር ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ የለንደን ማራቶንን አሸነፈች

አትሌት ትዕግሥት አሰፋ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ትዕግሥት አሰፋ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዛሬው ዕለት በለንደን ከተማ በተካሄደው የሴቶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ የራሷን ሰዓት በማሻሻል አሸነፈች። ኬንያዊው አትሌት ሰባስቲያን ሳዌ ደግሞ በወንዶች ማራቶን ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።

ዛሬ እሁድ ሚያዚያ 18 2018 ዓ.ም. በተካሄደው በ46ኛው የለንደን ማራቶን በወንዶች ማራቶን የተወዳደረው እና የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን ያከናወነው ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጄልቻም ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።

ትዕግሥት ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 02 ሰዓት15.41 ሲሆን ሁለት ኬንያዊ አትሌቶችን አስከትላ ገብታለች።

የባለፈው ዓመት የለንደን ማራቶን አሸናፊው ሰባስቲያን ሳዌ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 1 ሰዓት 59.30 ደቂቃ ርቀቱ ብቻ ወስዶበታል።

ባለፈው ዓመት ለ45ኛ ጊዜ በተደረገው የለንደን ማራቶን አትሌት ትዕግሥት አሰፋ 2 ሰዓት 15.50 በመግባት እና ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ውድድሩን በአሸናፊነት ማጠናቀቋ ይታወሳል።

ሁለተኛ እና ሦስተኛ የወጡት ኬንያውያን ሔለን ኦቢሪ እና ጆሲሊን ጄፕኮስጊ ናቸው።

ሁለቱ የኬንያ ሯጮች ከ2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ በታች አጠናቅቀዋል።

ትዕግሥት አሰፋ ከውድድሩ በፊት በለንደን ለሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፤ በዚህ ውድድር ዳግመኛ ማሸነፍ እንደምትፈልግ ተናግራ ነበር።

ትዕግሥት ከውድድሩ በፊት ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እንዳደረገች እና "ድጋሚ በማሸነፍ ደስታዬን ማጣጣም ነው የምፈልገው" ብላ ነበር።

ባለፈው ዓመት ለ45ኛ ጊዜ በተደረገው የለንደን ማራቶን አትሌት ትዕግሥት አሰፋ 2 ሰዓት 15.50 በመግባት እና ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቅቃለች።

ከዚህ ቀደም በለንደን ማራቶን በማሸነፏ ትልቅ ደስታ እንደተሰማት ለቢቢሲ የተናገረችው ትዕግሥት፣ "የለንደን ማራቶን ትልቅ ውድድር ነው። እርሱን ሻምፒዮን መሆን ድጋሚ ሻምፒዮን መሆን ነው" ብላለች።

በወንዶች ምድብ በተደረገው ውድድር የኬንያው አትሌት ሰባስቲያን ሳዌ አዲስ ታሪክ በመጻፍ ውድድሩን በበላይነት አጠናቋል።

ሰባስቲያን ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት የመጀመሪያው ሰው ለመሆን ችሏል።

አትሌቱ ውድድሩን 1 ሰዓት 59.30 በመግባት አሸንፏል።

እስከመጨረሻው ከፍተኛ ፉክክር ያደረገው እና የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን ያከናወነው ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጄልጃ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።

ዮሚፍም ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች የገባ ሁለተኛ ሰው ለመሆን ችሏል።

ኢትዮጵያዊው ውድድሩን 1 ሰዓት 59.41 በመግባት አጠናቋል ።

ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ ከዚህ ቀደም ይፋዊ ባልሆነ ውድድር ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ማጠናቀቁ ይታወሳል።