አስፈላጊ ነገር ግን ጎጂ የሆነውን የጨው አወሳሰዳችንን እንዴት መመጠን እንችላለን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጨው ምግባችንን የበለጠ ያጣፍጠዋል። ለሰው ልጅ ሕይወትም አስፈላጊ ነው።
በጨው ውስጥ የሚገኘው ሶዲየም በሰውነት ውስጥ የሚኖረውን ትክክለኛውን የውሃ መጠን ለመጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ህዋሳትም ንጥረ ምግቦችን እንዲወስዱ ይረዳል።
በምግብ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ፕሮግራም “ዘ ፉድ ቼይን” ጨው በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ወሳኝ ሚና እና ለአንድ ሰው ከመጠን በላይ የሚባለው የጨው ፍጆታ ምን ያህል ነው የሚለውን ተመልክቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጨው አስፈላጊነት
በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ሩትገርስ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምግብ ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ብሪስሊን “ጨው ለሕይወት አስፈላጊ ነው” ሲሉ ጠቅለል አድርገው ይገልጻሉ።
“ጨው በተለይ በኤሌክትሪክ ለሚንቀሳቀሱ ህዋሶች አስፈላጊ ነው። ይህም ሁሉንም የነርቭ ህዋሳት፣ አዕምሯችንን፣ አከርካሪያችንን እና ጡንቻዎቻችንን ያጠቃልላል። ለቆዳ እና ለአጥንትም ወሳኝ ነው” ብለዋል።
ፕሮፌሰር ብሬስሊን አክለውም በጨው ውስጥ የሚገኘውን ሶዲየም በበቂ ሁኔታ ካላገኘን እንሞታለን ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
የሶዲየም እጥረት ወደ ሃይፖናትሬሚያ ያመራል። ይህም ግራ መጋባት፣ ብስጭት፣ ማስታወክ፣ መንቀጥቀት እና ራስን መሳትን ያስከትላል።
የዓለም ጤና ድርጅት በቀን ሁለት ግራም ሶዲየም የያዘ አምስት ግራም ጨው እንድንመገብ ይመክራል። ይህም ከአንድ ሻይ ማንኪያ ጋር እኩል ነው።
በዓለም ላይ ሰዎች የሚወስዱት አማካዩ የጨው መጠን 11 ግራም ነው። ይህም በልብ እና በደም ቧንቧ በሽታዎች፣ በጨጓራ ካንሰር፣ ከመጠን ባለፈ ውፍረት፣ በአጥንት መሳሳት እና በኩላሊት በሽታ የመያዝ ዕድልን ይጨምራል።
በዓለም ላይ 1.89 ሚሊዮን ሰዎች በየዓመቱ ከመጠን በላይ ጨው በመጠቀማቸው ሕይወታቸው ያልፋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዋነኛ የጨው ተጠቃሚዎች
በብዙ አገራት ውስጥ ከመጠን በላይ የጨው ፍጆታ የሚፈጠረው በተቀነባበሩ ምግቦች ውስጥ የሚጨመረው መጠን ባለመታወቁ ነው።
ምክንያቶቹ ታሪካዊ ሊሆኑም ይችላሉ። በካዛክስታን ያሉ ሰዎች በቀን ወደ 17 ግራም ጨው ይመገባሉ። ይህም ከሚመከረው መጠን ከሦስት እጥፍ በላይ ነው።
ማርያም የምትኖረው በካዛክስታን መዲና አስታና ውስጥ ነው።
“ከታሪካችን ጋር ይገናኛል። ለብዙ ዘመናት እንዳይበላሽ በብዙ ጨው አሽተን ያዘጋጀነውን ሥጋ ይዘን ከቦታ ቦታ እንዞር ነበር” ስትል ተናግራለች።
“ሰዎች ምግብ ለክረምቱ ጊዜ ያከማቻሉ። አንድ ሙሉ የላም፣ በግ ወይም ግማሽ የፈረስ ሥጋ እንዳይበላሽ ጠብቀው ሊያቆዩ ይችላሉ” ብላለች።
ከስምንት ዓመት በፊት የማርያም ልጅ አንዳንድ የጤና ችግሮች አጋጥመዋት ነበር። ዶክተሯ ስኳር፣ ስብ እና ጨው ያለባቸውን ምግቦችን እንድትቀንስ መክሯታል። ቤተሰቡ በፍጥነት ምግባቸው ላይ ጨው መጨመሩን አቆመ።
“አዲሱን አመጋገብ ስንጀመር ጣዕሙ ደስ የማይል ነበር። ምግቡን ለመብላት ልትሞክር ብትችልም ለመለየት ግን ይከብዳል” ብላለች።
የምግቡ ጣዕም መቀየር ግን ብዙም አልዘለቀም። የማርያም ቤተሰብ ጨው የሌለውን ምግብ ተላመደ።

የፎቶው ባለመብት, Maryam (contributor)
ሰውነት ለጨው ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል?
ጨው ስንመገብ በምላሳችን ላይ ባለው የጣዕም መለያ እና በጉሮሮ ውስጥ ባለው ለስላሳ ክፍል ይታወቃል።
“ጨው ለሰውነታችን እና ለአዕምሯችን ኤሌክትሪክ ያሠራጫል” ብለዋል ፕሮፌሰር ብሬስሊን።
“የጨው እንክብሎችን የሚሠሩት ሶዲየም ቅንጣቶች ምራቅ ሲነካቸው ይቀልጣሉ።”
እነዚያ የሶዲየም ቅንጣቶች ወደ ጣዕም መለያ ህዋሳት ውስጥ ይገቡ እና ህዋሱን ያንቀሳቅሳሉ።
“አነስተኛ የኤሌክትሪክ ብልጭታ ይፈጥራል” ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
ጨው ሃሳቦችን እና ስሜቶችን የሚያመለክቱ የኤሌክትሪክ ምልክቶችን ያስተላልፋል። ስለዚህ ሰውነታችን እና አዕምሯችን ይደሰታሉ።
ከመጠን በላይ የሚባለውስ ምን ያህል ነው?
የጨው መጠን በሰውነት ላይ ያለው ትክክለኛ ተጽእኖ በግለሰቡ አፈጣጠር ላይ የተመሠረተ ነው።
በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች በከፍተኛ የደም ግፊት ይሰቃያሉ። የጨው መጠንን መቀነስ ችግሩን ለመከላከል እና ለማከም ይረዳል።
“ጨው ሲበዛ ሰውነታችን መጀመሪያ የሚያደርገው ነገር ማሟሟት ነው። ሰውነታችን ውስጥ ውሃ ስለሚበዛ ያንን ለማንቀሳቀስ በሚል የደም ግፊታችን ይጨምራል” ሲሉ በአውስትራሊያ ኒውካስል ዩኒቨርስቲ የሥነ ምግብ እና የአመጋገብ ፕሮፌሰር የሆኑት ክሌር ኮሊንስ ያብራራሉ።
የዚህ መዘዝ አስከፊ ሊሆን ይችላል።
“አንጎል ውስጥ ያሉ እና ሌሎች ስስ የሆኑ የደም ስሮች ሊፈነዱ እና ስትሮክ ሊያስከትሉ ይችላሉ።”
በዩናይትድ ኪንግደም ዕለታዊው አማካዩ የጨው ፍጆታ ወደ ስምንት ግራም ዝቅ ብሏል። ይህም ግን ከሚመከረው አንጻር በስድስት ግራም ይበልጣል። ቅነሳው በመመሪያው ረድቷል። የምግብ አምራቾች የጨው መጠን እንዲቀንሱ በማስገደድ ጭምር ነው አማካዩን የጨው ፍጆታ መቀነስ የተቻለው።
እንድንወስድ የሚመከር የጨው መጠን ከአገር አገር ይለያያል። የሽንት ምርመራ በማድረግ ሰውነትዎ ውስጥ በጣም ብዙ ወይም አነስተኛ ጨው ስለመኖሩ ማወቅ ይችላል።
የጨው መጠንዎን ለማወቅ የሚወስዱትን ምግብ መመዝገብ ወይም በታሸጉ ምግብ ላይ የሚታየውን የሶዲየም ይዘትን የሚያሰላ መተግበሪያ መጠቀም ይችላሉ። ሁለቱም ዘዴዎች ሙሉ ለሙሉ ትክክለኛ አይደሉም ያሉት ኮሊንስ፣ ጠቃሚ አመላካች ግን ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጨው ለመቀነስ ጠቃሚ ዘዴ
የጨው መጠንዎ ከፍ ያለ ቢሆንም መቀነስ ቀላል ላይሆን ይችላል። አስታና የምትኖረው ማርያም የካዛክስታን ብሔራዊ ምግብ የሆነውን በሽባርማክን (ከፓስታ ጋር የተቀቀለ ሥጋን) ላለመብላት ብትሞክርም አሁንም ትቸገራለች። ወላጆቿ የችግሩን አሳሳቢነት ቢያውቁም ጨው ለመተው ፍላጎት የላቸውም።
ፕሮፌሰር ኮሊንስ ዳቦ ወይም ፓስታ ወይም ዝቅተኛ የጨው ይዘት ያለውን ማንኛውንም ሌላ የምግብ ዓይነት እንድንመርጥ ይመክራሉ።
“የራስዎን ምግብ የሚያበስሉ ከሆነ ከጨው ይልቅ ቅጠላ ቅጠሎችን እና ቅመሞችን ጨምሩ” በማለት በተቻለን አቅም የጨው ፍጆታችንን መጠን በመቀነስ ለሰውነታችን ጤንነት አስፈላጊ በሆነ መጠን መመገብ ይኖርብናል ብለዋል።















