ክርስቲያን በመሆናቸው እንግልት እና እስር የሚደርስባቸው ሰሜን ኮሪያዊያን

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ኪም ቦ-ቢን ሰሜን ኮሪያ ሳለች ዐይኗን ከፍታ መፀለይ ነበር የምታውቀው።
የዜጎችን እምነት የሚቆጣጠረው የኮሚዩኒስቱ የሰሜን ኮሪያ አገዛዝ ሥር ሆና የክርስትና እምነቷን እንዴት ደብቃ ማስኬድ እንዳለበት ተምራለች። እምነትን በግልፅ ማራመድ ለእስር ሊዳርግ ይችላል ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
ኪም በአርምሞ ትዘምራለች፣ በሁለት ጣቶቿ ብቻ ታጨበጭባለች። "ሰሜን ኮሪያ ውስጥ አንድ ቦታ ሦስት ሰዎች ካሉ እየተሰለልክ መሆኑን መጠርጠር አለብህ። ለዚህ ነው መሬት ላይ ቁጢጥ ስል ብቻ ዐይኔን ጨፍኜ የምፀልየው" ትላለች።
የ44 ዓመቷ ኪም አሁን ከደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴዑል ወጣ ብሎ ካለ መንደር ትኖራለች። ከአገር ቤት ከወጣች 15 ዓመታት ሆኗታል።
በእምነታቸው ምክንያት ለእስር ከተዳረጉ እና ድብደባ ከደረሰባቸው 570 ሰዎች መካከል አንዷ ናት። እነዚህ ሰዎች የክርስትና እምነት ተከታይ በመሆናቸው ምክንያት የደረሰባቸውን ስቃይ የሚዳስስ አዲስ ሪፖርት ወጥቷል።
ኮሪያ ፊውቸር የተባለው የብሪታኒያው የሰብዓዊ መብት ተቋም ነው ላለፉት አምስት ዓመታት ያደረገውን ዳሰሳ ይፋ ያደረገው። ተቋሙ የኪም ጆንግ ኡን አገዛዝ ዜጎች እምነታቸውን በነፃ እንዳያራምዱ ስለላ ያደርጋል፣ ፍርሃት ይነዛል፣ አልፎም ያስፈራራል ብሏል።
ሰሜን ኮሪያ ከሰብዓዊ መብት ተቋማት እና ከተባበሩት መንግሥታት የሚቀርብባትን የእምነት አፈና ወቀሳ አትቀበልም። እርግጥ ነው ፒዮንግያንግ ውስጥ የእምነት ተቋማት አሉ። ነገር ግን በመንግሥት ቁጥጥር የሚደረግባቸው እና ለይስሙላ የቆሙ ናቸው።
"የሰሜን ኮሪያው መሪ እንደ ፈጣሪ ነው የሚቆጠረው" ይላሉ በዶንግ-አ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶንግ-ዋን።
"ለዚህ ነው ከመሪው በላይ የሚታይ ፈጣሪን የማይፈቅዱት" ይላሉ። አክለው ፒዮንግያንግ የእምነት ነፃነት ለአገዛዙ ስጋት እንደሆነ ታስባለች ሲሉ ይሞግታሉ።
ክርስትና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኮሪያ የገባው በ1700ዎቹ ነበር። የፕሮቴስታንት ሚሽኖች ወደ ሰሜን ዘልቀው ያስፋፉት ደግሞ በ1880ዎቹ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ ምን ያህል የክርስትና እምነት ተከታዮቿ እንዳሏት ይፋ አታደርግም። ነገር ግን የተባበሩት መንግሥት መረጃ ከ200 እስከ 400 ሺህ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳያል። የተወሰኑት አስሮ ማቆያ ካምፖች ውስጥ ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 2011 አባታቸውን ተክተው ሥልጣን የያዙት ኪም ጆንግ ኡን እንደ ቀደሙት አገዛዞች ዜጎቻቸውን በዐይነ ቁራኛ ይከታተላሉ።
በ2013 እና 2014 በቻይና ድንበር በኩል ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት ደቡብ ኮሪያዊያን ሚሽነሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በስለላ ወንጀል የዕድሜ ልክ እስር እንደተፈረደባቸው ይታወሳል። እስካሁን ድረስ በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚታወቅ ነገር የለም። በሰዎቹ ጉዳይ ሁለቱ ኮሪያዎች አሁንም ይነታረካሉ።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy Kim Bo-bin
End of podcast promotion
በፍላሽ ዲስክ ተጭነው በድንበር በኩል የሚገቡ የደቡብ ኮሪያ የክርስትና አስተምህሮዎች እና መዝሙሮችም ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። በ2020 ሰሜን ኮሪያ ያወጣችው "የውጭ ጫና" ለመቆጣጠር ያሰበ ሕግ ከውጭ የሚመጡ ርዕዮተ ዓለማት እና ባሕሎችን የሚመክት ነው።
መፅሐፍ ቅዱስ ይዞ መገኘት እና ስብከት ማድረግ ለእስር ሊዳርግ ይችላል። ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን መፃሕፍት እና ቪድዮዎች ማሠራጨት ደግሞ በሞት የሚያስቀጣ ነው።
ሰሜን ኮሪያዊያን ፀረ-ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚሰጣቸው ገና ከልጅነታቸው ነው። ኪም ይህን ትምህርት ወስዳ ነው ያደገችው። አስተማሪዎቿ ኪም ኢል ሱንግ ከክርስትያን ቤተሰብ እንደተወለደ አሊያም ፒዮንግያንግ በአንድ ወቅት "የምሥራቁ ዓለም ኢየሩሳሌም" ትባል እንደነበር አልነገሯትም።
ይልቁንስ የሰሜን ኮሪያ መሥራች ከሆኑት ኪም ኢል ሱንግ እና ከልጃቸው ኪም ጆንግ ኢል በላይ ሌላ ትልቅ መሪ እንደሌለ እየተነገራት ነው ያደገችው።
ምንም እንኳ አገዛዙ ዜጎቹ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ቢያደርግም ሰሜን ኮሪያዊያን ግን ሕይወታቸው ከባድ በመሆኑ ፊታቸውን ወደ እምነት ከማዞር ወደኋላ አላሉም። እምነት "አገዛዙ ከሚኖሩበት እውነታ ለማራቅ የሚያደርገውን ሙከራ የሚመክቱበት አንድ ነገር ይሰጣቸዋል" ይላሉ የጥናቱ ተባባሪ ፀሐፊ የሆኑት ጄምስ በርት።
ኪም ከቻይና ጋር ድንበር በምታዋሰነው ሰሜን ሀምግዮንግ ግዛት ነው ያደገችው። ሥፍራው እጅግ ራቅ ያለ እና ድኅነት ያጎሳቆለው ነው። እዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰሜን ኮሪያዊያን ወደ ፒዮንግያንግ መሄድ እንኳ የማይፈቀድላቸው፣ ከፍተኛ ትምህርት እና የመንግሥት ሥልጣን ማግኘት እርም የሆነባቸው ናቸው።
ኪም በ2003 ለሥራ በሚል ወደ ቻይና ብታቀናም ከአንድ ቻይናዊ ጋር እንድትጋባ ተፈርዶባት አረገዘች። በ2007 ታስራ ወደ ከአገር እንድትወጣ ተደረገ።
የሰሜን ኮሪያ ፖሊሶች አንገትሽ ላይ መስቀል አለ ብለው ጠይቀዋታል። መስቀል ምን እንደሆነ እንደማታውቅ ተናግራ ነው ያለፈችው። ቢሆንም ለ23 ቀናት ድብደባ እንደደረሰባት እና ለሦስት ዓመታት የጉልበት ሥራ እንደተፈረደባት ትናገራለች።
ይህ የበርካታ ሰሜን ኮሪያዊያን ታሪክ ነው።
ኪም በ2012 ከሰሜን አምልጣ ወደ ደቡብ ኮሪያ አቀናች። በወቅቱ 30 ዓመቷ ነበር። ከሴት ልጇ ጋር ነው አገሯን ጥላ የወጣችው። አሁን ቀኑን ሙሉ ያለምንም ሰቀቀን ትፀልያለች። ዘወትር እሑድ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሚዘምሩ ሰዎች ቀንደኛዋ ናት።




































