የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች በወራት ውስጥ ዝግጁ የሚሆን አዲስ የኢቦላ ክትባት እየሰሩ መሆኑን ተናገሩ
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አሁን የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለማስቆም ጥቅም ላይ ሊውል እንዲሁም በወራት ጊዜ ውስጥ ዝግጁ ሊሆን የሚችል አዲስ ክትባት መስራታቸውን ገለጹ።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ በተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ 177 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 750 ደርሷል።
ቡንዲቡግዮ በተሰኘው እና እምብዛም ባልተለመደ በዚህ የቫይረስ ዝርያ ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው ሕይወታቸው ያልፋል። እስካሁን ድረስም የተረጋገጠ ክትባት አልተገኘለትም።
የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች ወረርሽኙ የሚስፋፋበት እንዲሁም በሙከራ ላይ ያለው ክትባታቸው የሚፈለግበት ሁኔታ ይፈጠር ከሆነ በሚል ሥራቸውን በፍጥነት እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦክስፎርዱ ክትባት ውጤታማ ስለመሆኑ እስካሁን ማረጋገጫ የለም። መጀመሪያ በእንስሳት ላይ ተሞክሮ ምርምር መደረግ ያለበት ሲሆን እርግጠኛ ለመሆን ደግሞ በሰዎች ላይ ይሞከራል።
ተመራማሪዎቹ ክትባቱን ለመስራት እየተጠቀሙት ያለው ቴክኖሎጂ በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ ስራ ላይ ሲያውሉት የነበረ ነው።
በኮቪድ ጊዜ የቫይረሱን ጄኔቲክ ኮድ በመውሰድ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመዋል። አሁን ደግሞ ቡንዲቡግዮ የተባለውን የኢቦላ ዝርያ ጄኔቲክ ኮድ ይወስዳሉ ተብሏል።
ክትባቱ ኦክስፎርድ ውስጥ በእንስሳት ላይ እየተሞከረ መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።