ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራን በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ባይግባቡም ድርድሩ ለውጥ እያሳየ መሆኑን ሁለቱም ተናገሩ

አሜሪካ እና ኢራን በዩራኒየም ክምችት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚኖር ቁጥጥር ላይ አለመግባባታቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች ሐሙስ ዕለት ቢወጡም የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በድርድሮቹ ላይ “ጥሩ ምልክቶች” መኖራቸውን ተናገሩ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች በወራት ውስጥ ዝግጁ የሚሆን አዲስ የኢቦላ ክትባት እየሰሩ መሆኑን ተናገሩ

    የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አሁን የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለማስቆም ጥቅም ላይ ሊውል እንዲሁም በወራት ጊዜ ውስጥ ዝግጁ ሊሆን የሚችል አዲስ ክትባት መስራታቸውን ገለጹ።

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ በተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ 177 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 750 ደርሷል።

    ቡንዲቡግዮ በተሰኘው እና እምብዛም ባልተለመደ በዚህ የቫይረስ ዝርያ ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው ሕይወታቸው ያልፋል። እስካሁን ድረስም የተረጋገጠ ክትባት አልተገኘለትም።

    የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች ወረርሽኙ የሚስፋፋበት እንዲሁም በሙከራ ላይ ያለው ክትባታቸው የሚፈለግበት ሁኔታ ይፈጠር ከሆነ በሚል ሥራቸውን በፍጥነት እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

    የኦክስፎርዱ ክትባት ውጤታማ ስለመሆኑ እስካሁን ማረጋገጫ የለም። መጀመሪያ በእንስሳት ላይ ተሞክሮ ምርምር መደረግ ያለበት ሲሆን እርግጠኛ ለመሆን ደግሞ በሰዎች ላይ ይሞከራል።

    ተመራማሪዎቹ ክትባቱን ለመስራት እየተጠቀሙት ያለው ቴክኖሎጂ በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ ስራ ላይ ሲያውሉት የነበረ ነው።

    በኮቪድ ጊዜ የቫይረሱን ጄኔቲክ ኮድ በመውሰድ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመዋል። አሁን ደግሞ ቡንዲቡግዮ የተባለውን የኢቦላ ዝርያ ጄኔቲክ ኮድ ይወስዳሉ ተብሏል።

    ክትባቱ ኦክስፎርድ ውስጥ በእንስሳት ላይ እየተሞከረ መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።

  2. የካናዳዋ አልበርታ ግዛት የአገሪቱ አካል ሆና በመቀጠሏ ጉዳይ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ልታካሂድ ነው

    የካናዳዋ አልበርታ ግዛት የአገሪቱ አካል ሆና ትቀጥል ወይስ የመገንጠል ጉዳይ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ አስገዳጅ ድምፅ ይሰጥ የሚለው የሚወሰንበት ሕዝበ ውሳኔ ሊካሄድ ነው።

    ይህ ሕዝበ ውሳኔ ከአስርት ዓመታት በኋላ የካናዳን አንድነት ፈተና ውስጥ የሚከት እርምጃ ሆኗል።

    የግዛቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳኒኤል ስሚዝ ሐሙስ ዕለት ሕዝበ ውሳኔው እንደሚካሄድ ያስታወቁት የአልበርታን መገንጠል የሚደግፉ ነዋሪዎች በተያዘው የአውሮፓውያን 2026 መጀመሪያ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎችን ፊርማ ካሰባሰቡ በኋላ ነው።

    አልበርታ የካናዳ ግዛት ሆና መቀጠሏን የሚደግፍ ሌላ የፊርማ ማሰባሰቢያ ላይ ደግሞ ከ400 ሺህ በላይ ፈርመዋል።

    በነዳጅ ሐብት በበለጸገችው ግዛት ውስጥ ነጻነትን የሚያቀነቅን እንቅስቃሴ እያደገ መጥቷል። ይህ እንቅስቃሴ የተነሳው ለዓመታት ከቆየው የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች አልበርታን ችላ ይሏታል የሚል ቅሬታ ነው።

    የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳዎችን እንደሚያሳዩት ግን አሁንም ቢሆን አብዛኞቹ የአልበርታ ነዋሪዎች መገንጠልን ደግፈው ድምጽ አይሰጡም።

    የግዛቷ ጠቅላይ ሚኒስትር በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ላይ እንደገለጹት ሕዝበ ውሳኔው የሚካሄደው ጥቅምት ላይ ነው።

    በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ የሚሰጠው አልበርታ በካናዳ ውስጥ ግዛት ሆና መቀጠል አለባት ወይስ መገንጠልን በተመለከተ አስገዳጅ የግዛት ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ሕጋዊው ሂደት መጀመር አለበት” የሚለውን ለመወሰን እንደሆነ አብራርተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ድምጻቸውን የሚሰጡት አልበርታ የካናዳ ግዛት ሆና መቀጠል አለባት የሚለውን በመደገፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

  3. አውሮፓ በሂደት አሜሪካ ላይ ያላትን ጥገኝት እንደምትቀንስ የኔቶ ዋና ፀሐፊ ተናገሩ

    የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ፤ ጥምረቱ ራሱን የሚያጠናክርባቸው መንገዶች እየተከተለ መሆኑን እና በሂደት አሜሪካ ላይ ያለውን ጥገኝነት እንደሚቀንስ ገለጹ።

    ዋና ፀሐፊ ስዊዲን ውስጥ እየተካሄደ ባለው የኔቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ይህ አካሄድ ለአሜሪካም ሆነ ለአውሮፓ አገራት ጠቃሚ ነው።

    እርምጃው አሜሪካ ሌሎች ቅድሚያ በምትሰጣቸው ጉዳዮች ላይ እንድታተኩር፤ የኔቶ አባላት የሆኑ የአውሮፓ አገራት ደግሞ የመከላከያ በጀታቸውን እንዲያሳድጉ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

    አሜሪካ ኔቶ ውስጥ የሚታወጣውን የገንዘብ መጠን ለማመጣጠን “አስፈላጊ” እምርጃ መሆኑንም አክለዋል።

    ዋና ፀሐፊው ሩተ ይህንን ያሉት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ ለከፈቱት ጦርነት የጦር ሠፈራቸውን ለማስጠቀም ፈቃደኛ ያልሆኑ የኔቶ አባል አገራት ላይ ወቀሳ ካሰሙ በኋላ ነው።

    ዋና ፀሐፊው፤ አውሮፓውያን አጋሮች ጦር ሠፈሮችን ክፍት ማድረግ በተመለከተ በሁለትዮሽ ስምምነት ማዕቀፍ መሠረት የአሜሪካን ፍላጎት እያሟሉ ነው ብለዋል።

    የአውሮፓ አጋሮች የሆርሙዝ ወሽመጥን በተመለከተ እያደረጉት ያለውን ጥረት ያነሱት ሩተ፤ "እንደ አውሮፓውያን አጋሮች፤ ለአሜሪካ ሊደረግ የሚችለውን ከፍተኛ ድጋፍ ማቅረብ እንችላለን” ብለዋል።

  4. ስፔናዊው የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ክለቡ አስታወቀ

    ለ10 ዓመት የዘለቀው የፔፕ ጋርዲዮላ የማንችስተር ሲቲ የአሰልጣኝነት ዘመን መጠናቀቁን ክለቡ ይፋ አደረገ።

    ጋርዲዮላ ከአሰልጣኝነት ኃላፊነታቸው ቢለቁም ዓለም አቀፍ የሲቲ ግሩፕ አምባሳደር ሆነው እንደሚቀጥሉ ክለቡ አስታውቋል።

    ፔፕ ጋርዲዮላ በማንችስተር ሲቲ የ10 ዓመት ቆይታቸው ሻምፕዮንስ ሊግን ጨምሮ 20 ዋንጫዎችን ለክለቡ ማንችስተር ሲቲ አስገኝተዋል።

    በዚህ ዓመትም የኤፍኤ ዋንጫ እና ካራባኦ ዋንጫ አሸንፈዋል።

    ፔፕ ከቀናት በፊት የውድድሩ ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚለቁ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲነገር የነበረ ሲሆን ዛሬ ክለቡ ይህንኑ አረጋግጧል።

    በመሆኑም ፔፕ የመጨረሻ ጨዋታቸውን እሁድ በማንችስተር ሲቲ ሜዳ ከአስቶን ቪላ ጋር አድርገው ያጠናቅቃሉ። በምትካቸው የቀድሞው ምክትላቸው እና የቼልሲ አሰልጣኝ የነበሩት ኤንዞ ማሬስካ እንደተሾሙ ተነግሯል።

  5. በሕንድ ሊደረግ የነበረው የአፍሪካ ጉባኤ በኢቦላ ስጋት ምክንያት ተራዘመ

    በሚቀጥለው ሳምንት ሊካሄድ የነበረው የሕንድ-አፍሪካ ጉባኤ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኡጋንዳ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ቀውስ ምክንያት መራዘሙ ተገለፀ።

    አራተኛው የሆነው ጉባኤው በአፍሪካ አገራት እና በሕንድ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማሳደግ ያለመ ነው።

    የዘንድሮው ጉባዔ ከአስር ዓመታት ቆይታ በኋላ ከግንቦት 20 እስከ ግንቦት 23 2018 ዓ.ም. ድረስ በዴሊ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ነው።

    ሕንድ እና የአፍሪካ ኅብረት ሐሙስ ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ ጉባዔው በአህጉሩ በተቀሰቀሰው የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ምክንያት መራዘሙን እና ጉባኤው ሊሰናዳበት የሚችል አዲስ ቀን ይፋ እንደሚሆን ገልፀዋል።

    እርምጃው የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱን “የዓለም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ” ብሎ ካወጀ በኋላ የመጣ ነው።

    እንደ ድርጅቱ መረጃ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች 600 ሲሆኑ፤ እስካሁን 139 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

    የቫይረሱ ምልክቶች እስኪታዩ ድረስ ከሁለት እስከ 21 ቀናት ይወስዳል።

  6. የፓኪስታን ልዑክ ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ዳግም ቴህራን ገቡ

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፓኪስታን ልዑክ ጋር ዛሬ አርብ በቴህራን ተገናኝተው ከአሜሪካ ጋር የተጀመረውን ጦርነት ለማስቆም ባቀረቡት የሰላም ዕቅድ ላይ መወያየታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ቴህራን እና ዋሺንግተን በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በከፍተኛ ደረጃ ተብላልቶ በተከማቸው ዩራኒየም ላይ መግባባት ላይ መድረስ አልቻሉም።

    ታስኒም የዜና ወኪል ፓኪስታን የአሜሪካን መልዕክት ለኢራን ካቀረበች ከሁለት ቀናት በኋላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳይድ ሞሺን ናቅቪ በቴህራን ለተጨማሪ ውይይት መገኘታቸውን ዘግቧል።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እየተደረጉ ባሉ ንግግሮች ላይ“ጥሩ ምልክቶች አሉ” በማለት ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ቀረጥ የምትጥል ከሆነ ግን ፋይዳ አይኖረውም ብለዋል።

    በንግግሩ ላይ የተወሰኑ ለውጦች ስለመኖራቸው “ጥሩ ምልክቶች አሉ” ያሉት ሩቢዮ “በጣም ተስፈኛ መሆን አልፈልግም. . . በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ምን አንደሚሆን እናያለን” ብለዋል።

    አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሐሙስ ዕለት እስካሁን ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ባይደርስም ልዩነቶች እየጠበቡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

  7. አሜሪካ ለታይዋን ልትሸጥ የነበረውን 14 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ በኢራን ጦርነት ምክንያት አቋረጠች

    አሜሪካ ለታይዋን ልትሸጥ የነበረውን 14 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ለኢራን ጦርነት በቂ ክምችት እንዳላት ለማረጋገጥ በሚል አቋረጠች።

    የአሜሪካ የባህር ኃይል ተጠባባቂ ኃላፊ ሁንግ ካኦ ሐሙስ ዕለት የመረጃውን ትክክለኛነት ለሴኔቱ አባላት አረጋግጠዋል።

    ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የተሰማው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሽያጩን ለማጽደቅ ቁርጠኛ እንዳልሆኑ እና በጉዳዩ ላይ ከታይዋን ፕሬዝዳንት ጋር እንደሚነጋገሩ ከገለጹ ከቀናት በኋላ ነው።

    የታይዋን ፕሬዚዳንት ቢሮ ቃል አቀባይ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች "አሜሪካ በጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ ስላደረገችው ማስተካከያዎች" ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።

    አሜሪካ ለታይዋን የምትሸጠው የጦር መሣሪያ ቤይጂንግን ለረዥም ጊዜ ሲያስቆጣት ነበር።

    ካኦ ሐሙስ ዕለት በሴኔት ፊት ቀርበው “አሁን ለኤፒክ ፊውሪ የሚያስፈልገንን መሣሪያ፣ ምንም እንኳ በቂ ቢኖረንም፣ ለማረጋገጥ ለተወሰነ ጊዜ አቁመነዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

    ካኦ የጦር መሣሪያ ሽያጭን በተመለከተ "ከታይዋን ጋር አልተነጋገርኩም" ብለዋል።

    አክለውም "ሁሉም ነገር እንዳለን እያረጋገጥን ነው፣ ነገር ግን አስተዳደሩ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለውጭ አገራት የሚደረገው የመሣሪያ ሽያጭ ይቀጥላል" ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ ባለፈው ሳምንት "ከቻይና ጋር ለመደራደር ጥሩ ነጥብ ነው” ቢሉም የመሣሪያ ሽያጩ እንዲቆም መወሰናቸውን ግን እስካሁን አላረጋገጡም።

    በተጨማሪም ለጋዜጠኞች "በሚቀጥሉት አጭር ጊዜያት ውስጥ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን" ሲሉ ተናግረዋል።

    እነዚህ አስተያየቶች የተሰጡት ፕሬዚዳንቱ ቤይጂንግ ደርሰው ከመጡ በኋላ ነው።

    ትራምፕ ከዢ ጂንፒንግ ጋር ባደረጉት ውይይት ታይዋን በአሜሪካ እና በቻይና መካከል በጣም ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነች ተናግረው ነበር።

    ትራምፕ በኋላ ላይ ለጋዜጠኞች ከዢ ጋር የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ሽያጭን በሚመለከት "በዝርዝር" መወያየታቸውን ተናግረዋል።

    እንደ አውሮፓውያኑ በ1982 አሜሪካ ለታይዋን በጉዳዩ ላይ ቤይጂንግን ላለማማከር ቃል ገብታ ነበር።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ጦር መሣሪያ ሽያጭ ከታይዋን ፕሬዝዳንት ላይ ቺንግ-ቲ ጋር ሊነጋገሩ መሆኑን ተናግረዋል

    ዋሽንግተን ለቻይና መንግሥት እውቅና በመስጠት ከታይዋን ጋር ያላትን ይፋዊ ግንኙት ካቋረጠችበት የአውሮፓውያኑ 1979 ወዲህ የአሜሪካ እና ታይዋን መሪዎች በቀጥታ ተነጋግረው አያውቁም።

    ቻይና ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ የምታይ ሲሆን፤ ከአንድነትን ለማምጣት ልትከተል ከምትችላቸው አማራጮች መካከል አንዱም በኃይል መጠቅለል ነው።

  8. አሜሪካ የታንዛኒያ ፖሊስ ሁለት አክቲቪስቶችን በማሰቃየታቸው ኃላፊው ላይ ማዕቀብ ጣለች

    የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ የታንዛኒያ ፖሊስ ባለሥልጣናት የምሥራቅ አፍሪካ አክቲቪስቶች ላይ “ስቅይት እና ጾታዊ ትንኮሳ” በማድረሳቸው ማዕቀብ ጣለች።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በመግለጫቸው ላይ የታንዛኒኣ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ፋውስቲን ጃከሰን ማፍዌሌን “በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ መሳተፋቸው በተጨባጭ መረጃዎች” በመረጋገጡ ማዕቀብ መጣሉን ገልጸዋል።

    የታንዛኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሃሙድ ታቢት ኮምቦ ለቢቢሲ ማፍዌሌ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የተጣለባቸው ማዕቀብ በይፋ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።

    ማዕቀቡ የተጣለው የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ታንዛኒያ ያላት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በሚመለከት ጠንከር ያለ ትችት ካቀረቡ በኋላ ነው።

    ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ቦኒፌስ ምዋንጊ እና አጋተር አቱሃይሬ የተባሉት አክቲቪስቶች ወደ ታንዛኒያ ያመሩት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ቱንዱ ሊሱን የፍርድ ሒደት ለመከታተል ነበር።

    በርካቶች የኬንያ መንግሥትን እና ባለሥልጣናትን በመገዳደር በደፋርነቱ የሚያውቁት ኬንያዊው ተሟጋች ቦኒፌስ ምዋንጊ በታንዛኒያ ወሲባዊ ስቅይቶች እንደተፈጸሙበት በተናገረበት ወቅት "ለመኖር እየታገልኩ ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

    ኬንያዊው ቦኒፌስ እና ኡጋንዳዊቷ አቱሃይሬ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ለበርካታ ቀናት ታስረዋል።

    የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ከታሰረ በኋላም እርቃኑን እንዲቀር ተደርጎ፣ እጁ እና እግሩን አስረው፣ ተገልብጦ (ወፌ ላላ) ውስጥ እግሩን እንደተገረፈ ተናግሯል።

    በመቀመጫው በኩል የተለያዩ ቁሶችን እንዲሁም አንደኛው እጁን በመጠቀም የተለያዩ ወሲባዊ ጥቃቶችን እንዳደረሰቡት ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ እና እያለቀሰ ለጋዜጠኞች አስረድቷል።

    አቱሃይሬ በበኩሏ በእስር ላይ እያለች እንደተደፈረች ተናግራለች።

    የታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም የፖሊስ ኃላፊ ቦኒፌስ የሰጠውን ምስክርነት ያልተቀበሉት ሲሆን፣ ክሱ ከአክቲቪስቶች የሚመጣ "አስተያየቶች" እና "የሰሚ ሰሚ" ነው ሲሉ ለቢበሲ ተናግረዋል።

    "እዚህ ቢሆኑ ኖሮ፤ ምን እያሉ እንደሆነ እጠይቃቸው ነበር። በሕግ እነዚህ ነገሮች የሰሚ ሰሚ ወይም የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ይባላሉ" ሲሉ ጁማኔ ሙሊሮ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

    ሐሙስ ዕለት ሩቢዮ በመግለጫቸው ላይ የታንዛኒያ ፖሊስ አባላት ሁለቱን አክቲቪስቶች “አስረዋል፣ አሰቃይተዋል እና ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል” ብለዋል።

    መግለጫው ማፍዌሌ የነበራቸውን ሚና ባይጠቅስም ነገር ግን ሁለት የሰብዓዊ መበት ተሟጋቾች “ለዚህ አስነዋሪ ተግባር ተጠያቂነት መውሰድ አለበት” ብለዋል።

    የታንዛኒያ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ማፍዌሌ በሳሚያ ሱሉሁ አስተዳደር ዘመን የአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው የመጀመርያው የታንዘኒያ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆነዋል።

    ቢቢሲ የታንዛኒያን ፖሊስ አስተያት ቢጠይቀም ምላሽ አላገኘም።

  9. አሜሪካ እና ኢራን በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ባይግባቡም ድርድሩ ለውጥ እያሳየ መሆኑን ሁለቱም ተናገሩ

    አሜሪካ እና ኢራን በዩራኒየም ክምችት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚኖር ቁጥጥር ላይ አለመግባባታቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች ሐሙስ ዕለት ቢወጡም የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በድርድሮቹ ላይ “ጥሩ ምልክቶች” መኖራቸውን ተናገሩ።

    የአሜረካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የኢራንን በከፍተኛ ደረጃ ተብላልቶ የተከማቸ ዩራኒየም ከአገሪቱ እንደሚያወጡ ተናግረዋል።

    አሜሪካ የኢራን ተብላልቶ የተከማቸ ዩራኒየም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረት መቃረቡን ታምናለች።

    ቴህራን በበኩሏ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ የሚውል መሆኑን በመግለጽ ትከራከራለቸ።

    “እናገኘዋለን፤ አንፈልገውም። አያስፈልገንም። ካገኘነው በኋላ እናወድመው ይሆናል፤ ነገር ግን እንዲኖራቸው ግን አንፈቀድም” ሲሉ በዋይት ሐውስ ለተገኙ ዘጋቢዎች ተናግረዋል።

    ሩቢዮ ለጋዜጠኞች ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ላይ ቀረጥ የምትጥል ከሆነ ዲፕሎማሲ ቦታ አንደማይኖረው ጨምረው ተናግረዋል።

    አክለውም በንግግሩ ላይ የተወሰኑ ለውጦች አሉ ሲሉ ተናግረዋል።

    “ጥሩ ምልክቶች አሉ” ያሉት ሩቢዮ “በጣም ተስፈኛ መሆን አልፈልግም. . . በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ምን እንደሚሆን እናያለን” ብለዋል።

    አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሐሙስ ዕለት እስካሁን ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ባይደርስም ልዩነቶች እየጠበቡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

    አክለውም የኢራን የተብላላ ዩራኒየም እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያላት ቁጥጥር አሁንም ያላግባቡ ነጥቦች መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

    ሁለት ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናት ከትራምፕ አስተያየት አስቀድመው ለሮይተርስ ጠቅላይ መሪው አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ ዩራኒየሙ ከአገር እንዳይወጣ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

  10. አሜሪካ ከሄዝቦላህ ጋር በተያያዘ በሊባኖስ የኢራን አምባሳደርን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች

    አሜሪካ ሐሙስ ዕለት በሊባኖስ የኢራን አምባሳደርን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ማዕቀብ ጣለች።

    ግለሰቦቹ ሄዝቦላህ ትጥቁን እንዳይፈታ በማድረግ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላምን አደናቅፈዋል በሚል ተወንጅለዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባለሥልጣናቱ በሊባኖስ ፓርላማ፣ መከላከያ፣ እና የጸጥታ መዋቅሩ ውስጥ በመሆን ሄዝቦላህ ወሳኝ የሆኑ የሊባኖስ ተቋማት ላይ ተጽዕኖውን እንዲያሳርፍ አድርገዋል በማለት ወንጅሏል።

    የግምጃ ቤቱ ኃላፊ ስኮት ቤሴንት “ሄዝቦላህ ሽብርተኛ ድርጅት ነው እናም ሙሉ በሙሉ ትጥቅ መፍታት አለበት” ብለዋል።

    ሄዝቦላህ ከኢራን የትጥቅ እና ስንቅ ድጋፍ የሚያገኝ ሲሆን እንቅስቃሴውን የጀመረው ከአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ መባቻ ጀምሮ ነው።

    አሜሪካ እና የባሕረ ሰላጤው አረብ አገራት ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ “ሽብርተኛ ቡድን” ሲሉ ፈርጀውታል።

    ሄዝቦላህ በ1983 (እአአ) በአሜሪካ ኤምባሲ እና በአሜሪካ ባሕር ኃይል ላይ ጥቃቶችን ፈጽሞ 258 አሜሪካውያን እና 58 ፈረንሳያውያን ሞተዋል።

    ከዚህም በተጨማሪ እአአ በ1983 በቤይሩት በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት በመፈጸምም ይወነጀላል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ባለፈው ሳምንት በመካከላቸው የተደረሰውን የተኩስ አቁም በ45 ቀን ለማራዘም ተስማምተዋል።

    ነገር ግን አሁንም እስረኤል በደቡብ ሊባኖስ በሄዝቦላህ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የምትፈጽማቸውን ድብደባዎች ሄዝቦላህም ወደ እስራኤል ዒላማዎች ሮኬቶች እና ድሮኖች መተኮሱን አላቆመም።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት የታጣቂ ቡድኑን የገንዘብ ምንጭ ለማድረግ የሚረዳ መረጃ ለሰጠ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ 10 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት መወሰኑን ተናግረዋል።

    ፒጎት በመግለጫቸው ላይ “ይህ የመጀመርያው ነው። ማንኛውም ከአሸባሪ ድርጅቱ ጋር የሚተባበር ወይንም ያስጠለለ ወይም የሊባኖስን ሉዓላዊነት የሚገዳደር ተጠያቂ አንደሚሆን ማወቅ አለበት” ብለዋል።

    አክለውም "የተረጋጋች፣ አስተማማኝ እና ነጻ የሆነች ሊባኖስ እንድትኖር ሄዝቦላህ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ መፍታት እና የሊባኖስ መንግሥት በመላ አገሪቱ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ብቸኛ ሥልጣን እንዲኖረው ማድረግን ይጠይቃል" ሲሉ ተናግረዋል።

  11. “በሆርሙዝ በኩል ለማሳለፍ ገንዘብ መጠየቅ ተቀባይነት የለውም” - የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ የክፍያ ሥርዓት ለመዘርጋት የምታደርገውን ጥረት "ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አጣጣሉት።

    በማያሚ አውሮፕላን ማረፊያ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር በሆርሙዝ ወሽመጥ ለማለፍ ክፍያ መጠየቅ ተቀባይነት እንደሌለው “እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም ይስማማበታል” ብለዋል።

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያላትን ይዞታ እና ቁጥጥር በማስፋት በሆርሙዝ ለሚያልፉ መርከቦች የክፍያ ሥርዓት እንደምትዘረጋ አስታውቃለች።

    ይሄንን የተቃወሙት ማርኮ ሩቢዮ በጉዳዩ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ማርቀቁን ገልጸዋል።

    በባህሬን የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ከ100 በላይ አገራት ደግፈዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም “በፀጥታው ምክር ቤት ታሪክ ብዙ ደጋፊ ያገኘ የውሳኔ ሐሳብ ነው” ብለዋል።

    ጉዳዩን ቻይና ሳሉ እንዳነሱት ጠቅሰው “የትኛውም አገር ክፍያን አልደገፈም” ብለዋል።

    ይህ አካሄድ ዲፕሎማሲያው ንግግርን እንደሚያሰናክልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “እንደዚህ ካደረጉ ለዓለም ስጋት ነው። ፍጹም ሕገ ወጥም ነው” ሲሉ አክለዋል።

  12. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያላትን ቁጥጥር የሚያሰፋ ካርታ ይፋ አደረገች

    ኢራን ወሳኝ በሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያላትን ቁጥጥር ለማጠናከር ባላት ዓላማ መሠረት የመተላላፊያ አካባቢውን ሰፊ ቦታ በይዞታዋ ስር የሚስገባ ካርታ በማውጣት የወታደራዊ ቁጥጥሯ ክልል መሆኑን አሳውቃለች።

    ኢራን ጦርነት ከተከፈተባት በኋላ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እና ጋዝ የሚተላለፍበትን ወሽመጥ ለመቆጣጠር ያስችለኛል ያላቸውን ሕግ በፓርላማዋ በኩል ማውጣቷ ይታወሳል።

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ አለኝ የምትለውን ሉዓላዊ ይዞታን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ውስጥ መተላላፊያውን እንዲቆጣጠር “የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወሽመጥ ባለሥልጣን” የተባለ አካል አቋቁማለች።

    ባለሥልጣኑ ይፋ ባደረገው ካርታ የኢራን ይዞታ አስከ ኦማን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውሃ ክልል ድረስ ዘልቆ የሚገባ ነው። ይህንንም አካባቢ የኢራን ጦር ኃይሎች የሚቆጣጠሩት መሆኑን አሳውቋል።

    ይህንንም ተከትሎ የተበባሩት አረብ ኤምሬቶች የውሃ ክልሏን ያካተተውን የኢራን ካርታ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን “ያልተጫበጠ ህልም” በማለት ውድቅ አድርጋዋለች።

    ነገር ግን ሆርሙዝን የሚቆጣጠረው የኢራን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት እንዳለው በወሽመጡ በኩል የሚደረጉ ማንኛውም የመርከቦች እንቅስቃሴ “ከባለሥልጣኑ ጋር በመነጋገር እና ፈቃድ በማግኘት” ሊሆን እንደሚገባ አስታውቋል።

    አሜሪካ እና በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ አጋሮቿ ግን ኢራን በሆርሙዝ ላይ ያላትን ቁጥጥር ለማረጋገጥ የምታደርገውን ሙከራ ውድቅ አድርገውታል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ኢራን ላወጣችው የቁጥጥር መመሪያ ተገዢ እንዳይሆኑ እየነገረች ነው።

    በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ሕግ ስምምነት መርከቦች በሌላ አገር የውሃ ክልል ላይ ያለምንም ችግር እንዲተላለፉ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ነገር ግን ኢራን ይህንን ስምምነት አልፈረመችም።

  13. አሜሪካ ኩባን ‘ማስፈራራት’ እንድታቆም ቻይና አሳሰበች

    አሜሪካ ኩባን “ማስፈራራት” እንዲሁም “ጫና ለማሳደር መሞከር” እንድታቆም ቻይና አሳሰበች።

    የአሜሪካ ፍርድ ቤት የ94 ዓመቱ የቀድሞ የኩባ ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ ላይ ክስ መመሥረቱን ተከትሎ ነው ቻይና ማሳሰቢያ የሰጠችው።

    ከ30 ዓመት በፊት በኩባ እና በፍሎሪዳ መካከል ተመትተው ከወደቁ ሁለት አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘ የቀድሞው የኩባ መሪ ላይ የተመሠረተው ክስ የአሜሪካ ዜጎችን ለመግደል ማሴር እና ሌሎችንም የያዘ ነው።

    አራት ሰዎች የሞቱበት ክስተት የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሻክሯል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኩባን ኮሚኒስት መንግሥት መገርሰስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጋዎ ጂያኩን “አሜሪካ በየአጋጣሚው ኩባን ማስፈራራት ማቆም አለባት” ብለዋል።

    ቻይና “በጽኑ ኩባን ትደግፋለች። በውጭ ኃይሎች በማንኛውም አውድ ኩባ ላይ የሚደርስ ጫናን ቤይጂንግ ትቃወማለች” ሲሉም ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ “አሜሪካ ማዕቀብ እና የሕግ መዋቅርን በመጠቀም ኩባን ማስፈራራት እና ጫና ማሳደር ማቆም አለባት” በማለትም አክለዋል።

    የኩባን ሉዓላዊነት እና ክብር ቻይና እንደምትደግፍ እንዲሁም የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወም ገልጸዋል።

  14. የኢራኑ ጠቅላይ መሪ በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየም ከአገራቸው እንዳይወጣ ወሰኑ

    ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የቀረበላትን በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየምን ወደ ውጭ ለመላክ የቀረበውን ሐሳብ ውድቅ ለማድረግ መወሰኗን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ሮይተርስ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየም ከአገር እንዳይወጣ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

    አሜሪካ ለሰላም ድርድር ካቀረበቻቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ይሄው ጉዳይ ነው።

    የጠቅላይ መሪው ውሳኔ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር ሊያስቆጣ እና የድርድር ሒደቱን ሊያወሳስብ ይችላል።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው የእስራኤል ባለሥልጣናት እንደሚሉት፤ ኢራን ያከማቸችው የተብላላ ዩራንየም ከአገሪቱ እንደሚወጣ ለእስራኤል ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

    የሰላም ስምምነት ላይ ኒውክሌር ጦር መሣሪያ የመሥራት ነጥብ ላይ የደረሰው የተብላላ ዩራንየም ከኢራን እንደሚወጣ መናገራቸው ተገልጿል።

    ስለ ጉዳዩ የኢራን መገናኛ ብዙኃን እስካሁን ድረስ ዘገባ አላወጡም።

    ኢራን ከአሜሪካ እና ከሌሎች ምዕራባውያን ጋር ለዘመናት ሲያወዛግብ የቆየው የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ሙሉ ለሙሉ እንድታቆም እና ከጥቅም ውጪ እንድታደርግ የቀረበላትን ጥያቄ ባለመቀበሏ ነው።

    በአሜሪካ እና በእስራኤል የተከፈተባትን ጦርነት ለማቆም ከቀረበላት ቅድመ ሁኔታ መካከልም እንዱ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ቢሆንም፤ ኢራን አልተቀበለችውም።

  15. ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኢቦላ ቫይረስ መቀስቀስ ምክንያት የዓለም ዋንጫ ልምምድን አቋረጠች

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰውን ኢቦላ ተከትሎ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ሊካሄድ የነበረን የዓለም ዋንጫ ቅድመ ልምምድ መሰረዟን አስታወቀች።

    ከ130 በላይ ሰዎችን ስለመግደሉ የተነገረለት በሽታ ማገርሸቱን ተከትሎ ዝግጅቶች ወደ ቤልጂየም መዘዋወራቸው ታውቋል።

    የዓለም የጤና ድርጅት ኢቦላን “የኅብረተሰብ ጤና ስጋት” ሲል መድቦታል።

    አገሪቱ እ.አ.አ ከ1974 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ እየተዘጋጀች ሲሆን፤ ቀድመው የተያዙ የሙከራ ጨዋታዎች በአውሮፓ እንደሚካሄዱ የብሔራዊ ቡድኑ ቃል አቀባይ ጄሪ ካሊሞ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከዴንማርክ፣ ቤልጂየም፣ ችሊ እና ስፔን ጋር ትጫወታለች።

    ቃል አቀባዩ እንዳሉት ልምምዱ የተሰረዘው ከሜክሲኮ እና ከካናዳ ጋር የዓለም ዋንጫን የምታዘጋጀው አሜሪካ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላይ የጉዞ እግድ በመጣሏ ነው።

    ዋሽንግተን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጨምሮ በሦስት አገራት ባለፉት 21 ቀናት ጉዞ ያደረጉ እና አሜሪካዊ ያልሆኑ መንገደኞች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ክልከላ ጥላለች።

    ሁሉም የአገሪቱ ተጨዋቾች እና ፈረንሳዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ሰባስቲያን ድሳብሬ መቀመጫቸው ከማዕከላዊ አፍሪካዊት አገር ውጭ በመሆኑ እና ልምምድ በመሰረዙ እግዱ ተፅዕኖ አያሳድርባቸውም።

  16. ኢራን ከታሰበው በበለጠ ፍጥነት የወታደራዊ ኢንዱስትሪዋን መልሳ እየገነባች መሆኑን ሲኤንኤን ዘገበ

    አሜሪካ እና እስራኤል በከፈቱት ጥቃት ወታደራዊ አቅሟ የተመታባት ኢራን፤ የተኩስ አቁም ከተደረገ ወዲህ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዋን በፍጥነት እየገነባች እንዲሁም የተወሰኑ ድሮኖችን እያመረተች መሆኑን ሲኤንኤን የአሜሪካ የስለላ መረጃን ጠቅሶ ዘገበ።

    የአሜሪካው ቴሌቪዥን ጣቢያ ያነጋገራቸው አራት ምንጮች እንደገለጹት የኢራን ጦር መጀመሪያ ላይ ሲጠበቅ ከነበረው ፍጥነት በበለጠ ሁኔታ አቅሙን እያጠናከረ መሆኑን የዋሽንግተን የስለላ መረጃ አመልክቷል።

    በአሁኑ ጦርነት ጥቃት የተፈጸመባቸው የሚሳዔል ስፍራዎች፣ ማስወንጨፊያዎች እና የመምረቻ አቅሞች እየተተተኩ መሆኑ፤ ኢራን በቀጣናው ለሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች አሁንም ትልቅ ስጋት መሆኗን ያሳያል ተብሏል።

    እንደ ሲኤንኤን ዘገባ፤ የስለላ መረጃው ስለ ኢራን ጦር እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረሱ አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት ጥቃት የሠራዊቱ አቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል ነው የሚለውን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል።

    የተለያዩ የጦር መሣሪያ ክፍሎችን ማምረት ለመጀመር የሚያስፈልገው ጊዜ የተለያየ ቢሆንም፤ ኢራን በድሮን ጥቃት የመፈጸም አቅሟን በስድስት ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት መመለስ እንደምትችል አንድ አሜሪካ ምንጭ መናገራቸውን ዘገባው ገልጿል።

    ሲኤንኤን ያነጋገራቸው ባለሥልጣን፤ “ኢራናውያን የስለላ ማኅበረሰቡ ለመልሶ ግንባታ ያስቀመጠውን የጊዜ ሰሌዳ በሙሉ አልፈዋል” ማለታቸው ተጠቅሷል።

    ዘገባው እንደሚያመለክተው፤ ኢራን ከታሰበው በበለጠ ፍጥነት መልሳ መገንባት የቻለችው በተለያዩ ምክንያቶች ነው።

    ከሩሲያ እና ቻይና ያገኘችው ድጋፍ እንዲሁም አሜሪካ እና እስራኤል ተስፋ ባደረጉት መጠን ከፍተኛ ጉዳት አለማድረሳቸው በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ አንድ ምንጭ ተናግረዋል ተብሏል።

    አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ካደረጉ ሳምንታት ቢቆጠሩም እስካሁን ድረስ ጦርነቱን በዘላቂነት የሚያስቆም ስምምነት ላይ አልደረሱም። አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን የሰላም ስምምነት የማትፈጽም ከሆነ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠንቅቀዋል።

  17. የፓኪስታን ሠራዊት አዛዥ ወደ ኢራን ሊጓዙ ነው

    የአሜሪካ እና ኢራን ዋና አሸማጋይ የሆነችው ፓኪስታን የሠራዊት አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ዛሬ ወደ ቴህራን እንደሚገቡ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ዘገባዎቹ እንደሚያመለክቱት የወታደራዊ አዛዡ የቴህራን ጉዞ ከዚህ ቀደም ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ሲደረግ ከነበረው ንግግር እና ምክክር የቀጠለ ነው።

    የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ ሞህሲንም በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ረቡዕ ዕለት ቴህራን መግባታቸውን ‘ኢስና’ የተባለው ኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል። ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን እና የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ እስካንዳር ሞሜኒ ጋር ተገናኝተዋል።

    የፓኪስታን እና የኢራን ባለሥልጣናት በንግግራቸው ቀጣናዊ ሁኔታዎችን እንደገመገሙ ዘገባው ጠቅሷል። በኢራን እና አሜሪካ መካከል የሚካሄደው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ስላለበት ሁኔታ መነጋገራቸውም ተገልጿል።

    የፓኪስታኒ ሚኒስትር አገራቸው ድርድሩን በተመለከተ ያላትን ምልከታ ለኢራን ባለሥልጣናት እንዳስረዱ ዘገባው አስነብቧል።

    ከፓኪስታኑ ሚኒስትር ጋር የተነጋገሩት የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ከዚያ በኋላ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ቴህራንን “በማስገደድ እጅ እንድትሰጥ” ለማድረግ የሚደረግ ጥረት “ቅዠት” ነው ብለዋል።

    “ኢራን ያለማቋረጥ ቃሏን ጠብቃለች፤ ጦርነትን ለመቀልበስም ሁሉንም ጎዳና አስሳለች” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “በእኛ በኩል ሁሉም መንገዶች ክፍት ናቸው” በማለት ጽፈዋል።

    “ኢራንን በማስገደድ እጅ እንድትሰጥ ማድረግ ቅዠት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። በዲፕሎማሲ ውስጥ የጋራ መከበባርን ማምጣት ከጦርነት እጅህ የላቀ ብልህ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው መንገድ ነው” ብለዋል።

  18. የአሜሪካ ጦር የሆርሙዝ እገዳን በመጣስ የተጠረጠረን በኢራን ባንዲራ የሚንቀሳቀስ መርከብ አቅጣጫ ማስቀየሩን አስታወቀ

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ዋሽንግተን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣለችውን እገዳ ለመጣስ ሞክሯል በሚል የተጠረጠረን በኢራን ባንዲራ የሚንቀሳቀስ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ በቁጥጥር ስር አውሎ አቅጣጫውን ማስቀየሩን አስታወቀ።

    ማዕከላዊ ዕዙ የአሜሪካ ኃይሎች ወደ መርከቡ ላይ ሲወጡ እና በቁጥጥር ስር ሲያውሉት የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አጋርቷል።

    “ኤም/ቲ ሴሌስቲያል ሲ የተባለው እና የኢራን ባንዲራን የሚያውለበልብ ነዳጅ ጫኝ የንግድ መርከብ” በባሕር ኃይሉ ወታደሮች የተያዘው “አሜሪካ የጣለችውን የባሕር ጉዞ እገዳ በመጣስ ወደ ኢራን ወደብ ለመጓዝ በመሞከር ተጠርጥሮ” እንደሆነ ገልጿል።

    “የአሜሪካ ኃይሎች መርከቡን ከፈተሹ እና የመርከቡ ሠራተኞች የጉዞ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ካደረጉ በኋላ መርከቡን ለቅቀውታል” ብሏል።

    የአሜሪካ ኃይሎች የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ ኢራን ወደብ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለውን እገድ “ሙሉ በሙሉ እያስፈጸሙ” መሆኑን የገለጸው ዕዙ፤ “91 የንግድ መርከቦች” ለእርምጃው እንዲገዙ መደረጉን ገልጿል።

  19. ትራምፕ እና ኔታንያሁ ስለ ኢራን ድርድር አካሄድ “በውጥረት የተሞላ” ንግግር ማድረጋቸው ተዘገበ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቤንጃሚን ኔታንያሁ የኢራን ጉዳይን በተመለከተ ማክሰኞ ዕለት “ከፍተኛ ውጥረት” የነበረበት እንዲሁም የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር “እጅግ ያበሳጨ” የስልክ ንግግር ማድረጋቸውን የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ዘገበ።

    እንደ አክሲዮስ ዘገባ፤ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተከናወኑ ስላሉ አዲስ ጥረቶች የተነሳበት የሁለቱ መሪዎች ንግግር ረጅም እና “አስቸጋሪ” ነበር።

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን በመደበኛነት ለማቆም እና በ30 ቀናት ውስጥ ድርድር እንዲካሄድ የሚያስችል “የፍላጎት መግለጫ” በአሸማጋዮች በኩል እየተዘጋጀ መሆኑን ትራምፕ ለእስራኤሉ መሪ ተናግረዋል ተብሏል።

    ዘገባው እንደሚያመለክተው በአንድ ወር ውስጥ የሚደረገው ድርድር እንደ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም እና የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት ያሉ ጉዳዮች ንግግር እንዲደረግባቸው የሚያስችል ነው።

    ዋሽንግተን እና ቴህራን እዚህ ሰነድ ላይ ፊርማቸው እንደሚያኖሩ የተነገራቸው ኔታንያሁ በአካሄዱ እንዳልተስማሙ ሁለት የእስራኤል ምንጮች ለአክሲዮን ተናግረዋል።

    ስለ ስልክ ንግግሩ ገለጻ የተደረገላቸው የአሜሪካ ምንጭ ደግሞ “ከስልክ ጥሪው በኋላ የቢቢ ጸጉር እሳት ለብሶ ነበር” ሲሉ የኔታንያሁን ስሜት መግለጻቸውን ዘገባው አስነብቧል።

    እንደ አክሲዮስ ዘገባ፤ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ያላቸው ኔታንያሁ፤ ጦርነቱ እንዲጀመር እና የኢራን ወታደራዊ አቅም ይበልጥ እንዲዳከም ፍላጎት አላቸው። ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን በመምታት አገዛዙ እንዲዳከምም ይፈልጋሉ ተብሏል።

    ትራምፕ በበኩላቸው ለሚደረገው ንግግር ጥቂት ተጨማሪ ቀናትን ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው። ይሁን እንጂ “ትክክለኛውም ምላሽ ካላገኘን” ጦርነት “በጣም በፍጥነት” ሊጀመር ይችላል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

  20. ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በልጃቸው የሚመራ የፀረ ሙስና ዘመቻ በባለሥልጣናት ላይ ጀመሩ

    ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የኡጋንዳ ጦር ሠራዊት አዛዥ በሆነው በልጃቸው የሚመራ በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የፀረ ሙስና ዘመቻ መጀመራቸው ተዘገበ።

    በዚህም የተነሳ ካምፓላ የሚገኘው የተሰናባቿ የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ መኖሪያ ቤት በኡጋንዳ የደኅንነት ኃይሎች ተፈትሾ ሮልስ ሮይስ እና ሬንጅ ሮቨርን ጨምሮ ቅንጡ መኪኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።

    የአገሪቱ ጦር አዛዥ እና የፕሬዝዳንቱ ልጅ የሆኑት ሙሁዚ ካይኔሩጋባ አባታቸው ኡጋንዳ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ሰው በቁጥጥር ስር የማዋል ሥልጣን እንደሰጧቸው ተናግረዋል።

    የፀረ ሙስና ዘመቻው ለአራት አስርት ዓመታት ኡጋንዳን እየመሩ ባሉት በፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ትዕዛዝ የሚካሄድ ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል።

    ቤታቸው የተፈተሸው አፈ ጉባዔዋ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰው ተደርገው ይታዩ የነበረ ሲሆን ለረዥም ጊዜ ስማቸው ከሙስና ጋር ሲነሳ ቆይቷል። በዚህም በብሪታኒያ እና በአሜሪካ ማዕቀቦች ተጥሎባቸዋል።

    አሁን ከባለሥልጣኗ ቤት የተያዙት ውድ ንብረቶች በጨረታ ተሽጠው ገንዘቡ ለሕዝብ እንደሚመለስ የጦሩ አዛዥ ተናግረዋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያጋሯቸው መልዕክቶች አነጋጋሪ የሆኑት የፕሬዝዳንቱ ልጅ ከሰሞኑ ባሠራጩት ጽሁፍ በዋና ከተማዋ ባሉ መንገዶች ላይ ጉድለት ከተገኘ የግንባታውን ኮንትራት የወሰዱትን ሰዎች አንገታቸውን እንደሚቀሉ አስጠንቅቀዋል።