ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኢቦላ ቫይረስ መቀስቀስ ምክንያት የዓለም ዋንጫ ልምምድን አቋረጠች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰውን ኢቦላ ተከትሎ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ሊካሄድ የነበረን የዓለም ዋንጫ ቅድመ ልምምድ መሰረዟን አስታወቀች።
ከ130 በላይ ሰዎችን ስለመግደሉ የተነገረለት በሽታ ማገርሸቱን ተከትሎ ዝግጅቶች ወደ ቤልጂየም መዘዋወራቸው ታውቋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ኢቦላን “የኅብረተሰብ ጤና ስጋት” ሲል መድቦታል።
አገሪቱ እ.አ.አ ከ1974 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ እየተዘጋጀች ሲሆን፤ ቀድመው የተያዙ የሙከራ ጨዋታዎች በአውሮፓ እንደሚካሄዱ የብሔራዊ ቡድኑ ቃል አቀባይ ጄሪ ካሊሞ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከዴንማርክ፣ ቤልጂየም፣ ችሊ እና ስፔን ጋር ትጫወታለች።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ልምምዱ የተሰረዘው ከሜክሲኮ እና ከካናዳ ጋር የዓለም ዋንጫን የምታዘጋጀው አሜሪካ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላይ የጉዞ እግድ በመጣሏ ነው።
ዋሽንግተን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጨምሮ በሦስት አገራት ባለፉት 21 ቀናት ጉዞ ያደረጉ እና አሜሪካዊ ያልሆኑ መንገደኞች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ክልከላ ጥላለች።
ሁሉም የአገሪቱ ተጨዋቾች እና ፈረንሳዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ሰባስቲያን ድሳብሬ መቀመጫቸው ከማዕከላዊ አፍሪካዊት አገር ውጭ በመሆኑ እና ልምምድ በመሰረዙ እግዱ ተፅዕኖ አያሳድርባቸውም።




















