የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢራን ሆርሙዝን የማትከፍት ከሆነ “አንድ ሰው የሆነ ነገር ማድረግ አለበት” አሉ
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ ከኢራን ጋር ስምምነት ተደርሶ የሆርሙዝ ወሽመጥ የማይከፈት ከሆነ “አንድ ሰው የሆነ ነገር ማድረግ ይኖርበታል” ሲሉ ተናገሩ።
ሩቢዮ እና የኔቶ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወሳኙ የባሕር መተላለፊያን መልሶ ስለመክፈት እየተወያዩ መሆናቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል ስምምነት የማይደረስ ከሆነ ወሽመጡን በተመለከተ “ሁለተኛ እቅድ” እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት እንዳነሱ ዘገባው ያመለክታል።
“በዚያ ሁኔታ ውስጥ፤ በራሳቸው ፈቃድ ወሽመጡን አይከፍቱትም” ያሉት ሩቢዮ ስምምነት ካልተደረሰ አንዳች እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንደ ኤፒ ዘገባ፤ ሩቢዮ ይህንን ጉዳይ ለበርካታ አውሮፓውያን አጋሮቻቸው አቅርበው “ይሁንታ” ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
“ኢራን [ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ] የክፍያ ሥርዓት ለመዘረጋት እየሞከረች ነው። ይሄ ተቀባይነት የለውም። ሊሆን አይችልም” ብለዋል።
“ይህ የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚፈጠር ከሆነ በዓለም ዙሪያ ሌሎች አምስት ቦታዎችም ላይም ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አክለውም ግን ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ መሻሻል እየታየ መሆኑን በመጥቀስ የኢራን ባለሥልጣናት የተናገሩትን ደግመዋል።
እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ የታየውን ውጤት “አላጋንነውም፤ ደግሞም አላድበሰብሰውም” ያሉት ሩቢዮ፤ “መከናወን ያለበት ተጨማሪ ሥራ አለ” በማለት ተናግረዋል።