ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አማጺያን የተቀናጀ ጥቃት በከፈቱባት ማሊ የመከላከያ ሚኒስትሩ ተገደሉ
የማሊ የመከላከያ ሚኒስትር በዋና ከተማዋ ባማኮ አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ተዘገበ።
ሳዲዮ ካማራ የተገደሉት ጂሃዲስት ታጣቂዎች እና ተገንጣዮች በመላ አገሪቱ በከፈቱት የተቀናጁ የጥቃት ማዕበሎች አካል በሆነ እርምጃ መሆኑን የበርካታ የዜና አውታሮች ዘገባ አመልክቷል።
የአገሪቱ መንግስት ቴሌቪዥን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሚኒስትሩ በደረሰባቸው ቁስል መገደላቸውን ዘግቧል። የወታደራዊው ጁንታ መሪ ጄኔራል አሲሚ ጎይታ ቤታቸው ዒላማ መደረጉን ተከትሎ ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ ተዛውረዋል ተብሏል።
በማሊ ጦር የተቀጠሩት የሩሲያ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ከሁለት ቀናት ግጭት በኋላ ከኪዳል ለመውጣት ተስማምተዋል ሲል የተገንጣዩ የአዛዋድ ነፃ አውጪ ግንባር (ኤፍኤልኤ) ተናግሯል።
ማሊ ለዓመታት በአል ቃይዳ እንዲሁም ከእስላማዊ መንግስት (አይኤስ) እና ከኤፍኤልኤ ጋር በተያያዙ ቡድኖች ጥቃት ሲፈጸምባት ቆይታለች።
የካማራን ቤተሰብ እና የፈረንሳይ ሚዲያዎችን በመጥቀስ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ባላቸው ታጣቂዎች ቅዳሜ ዕለት ካቲ ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ሦስት የካማራ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።
የመንግስት ቃል አቀባይ ኢሳ ኦስማን ኩሊባሊ እሑድ ምሽት ባነበቡት መግለጫ ካማራ "ፈንጂ የተሞላበት እና በአጥፍቶ ጠፊ በሚነዳ ተሽከርካሪ የሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት ጥቃት በተሰነዘረበት ወቅት ተገድለዋል" ብለዋል።
ከአጥቂዎቹ ጋር የተኩስ ልውውጥ እንዳደረጉ እና "አንዳንዶቹን በማስወገድ ረገድ እንደተሳካላቸው" ተናግረዋል። ሆኖም ግን ቆስለው በሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ህይወታቸው አልፏል።
ጥቃቱ የካማራን መኖሪያ ቤት እንዲፈርስ ከማድረጉም በላይ በአቅራቢያው ያለ መስጊድ እንዲወድም ምክንያት በመሆኑ በስፍራው የነበሩ በርካታ ምዕመናንም ተገድለዋል።
ቅዳሜ ዕለት ከዋና ከተማዋ ውጭ ዋና ወታደራዊ ካምፕ በሚገንባት ከተማ፣ በሰሜን ጋኦ እና ኪዳል እንዲሁም በማዕከላዊ ሴቫሬ እና ሞፕቲ ከተሞች ውስጥ ውጊያ እንደነበር ተዘግቧል።
ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በሰሜን በኩል የቱዋሬግ ጎሳን መንግሥትነት የሚሹ ተገንጣዮች በዋናነት ጥቃታቸው ያተኮረው በሰሜናዊ ከተሞች ላይ ነው።
የጂሃዲስት ቡድኑ ጃማአት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል-ሙስሊሚን (ጄኤንአይኤም) ደግሞ በመላ አገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተመሳሳይ ጊዜ ጥቃቶችን ሰንዝሯል።
በማሊ የሚገኘው የኮንራድ አደናወር ፋውንዴሽን የሳሄል ፕሮግራም ኃላፊ ኡልፍ ላሲንግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ክስተቱ "ለዓመታት በማሊ ላይ የተፈጸመው ትልቁ የተቀናጀ የጂሃዲስት ጥቃት" ይመስላል።
የኤፍኤልኤ ቃል አቀባይ መሐመድ ኤልማውሉድ ራማኔ በበኩላቸው ኪዳል "ሙሉ በሙሉ [በታጣቂዎቹ ስር ] አልወደቀም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "የማሊያ ጦር እና የሩሲያ ቅጥረኞች" በመኖራቸው በከተማው ውስጥ እንደቆዩ ተናግረዋል።
እሑድ ዕለትም በኤፍኤልኤ እና በማሊ መንግስት መካከል ግጭቶቹ በኪዳል ቀጥለዋል።
እነዚህ ሪፖርቶች ከተዘገቡ በኋላ "በአዛዋድ ኃይሎች እና በአፍሪካ ጦር የሩሲያ ክፍሎች መካከል ከግጭት ቀጣናው በሠላም ለመውጣት ስምምነት ላይ ተደርሷል" ሲሉ ራማኔ ተናግረዋል።
በኋላ ላይም "ከኪዳል በቋሚነት እየወጡ ነው" እናም "ኪዳል አሁን ነፃ ናት" ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ከማሊ ጦር ምንም ማረጋገጫ አልተሰጠም።
ቡድኑ ከተማዋን እንደተቆጣጠረም ገልጿል። በ2023 መጨረሻ ላይ የማሊ ጦር በሩሲያ ቅጥረኛዎች እገዛ ከመያዟ በፊት ከተማዋ ከአስር ዓመታት በላይ የተገንጣይ ቡድኑ ኦፊሴላዊ ያልሆነ ዋና መቀመጫ ሆና አገልግላለች።
በኪዳል ላይ በተደረገው ጥቃት የተሳተፉ የኤፍኤልኤ የጦር አዛዥ ቅዳሜ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቡድኑ ለወራት ለጥቃቱ ሲዘጋጅ ቆይቷል፤ "አሁን ዋናው ግባችን ጋኦን መቆጣጠር ሲሆን ቲምቡክቱ በቀላሉ በእጃችንት ትገባለች" ብለዋል።
የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ኦአርቲኤም በጥቃቶቹ ሲቪሎችን እና ወታደሮችን ጨምሮ 16 ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግቧል።
በተጨማሪም በርካታ "አሸባሪዎች" መገደላቸውን ገልጾ በሁሉም አካባቢዎች ሁኔታው "ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር" መሆኑን አክሏል።
ወታደራዊ ኃይሉ ግን በኪዳል እንዲሁም በካቲ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ውጊያው መቀጠሉን አረጋግጧል።
እሑድ ዕለት ባወጣው መግለጫም ጥቃቱ "መልስ ሳይሰጥበት የማያልፍ" መሆኑን ገልጿል።
በመላ አገሪቱ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አክሎ የደህንነት እርምጃዎች እና የፍተሻ ኬላዎች ተጠናክረው የጸጥታ ጥበቃው መጨመሩን ጠቅሷል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል። በባማኮ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለ ሲሆን ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ቅዳሜውን ጥቃቶችን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "ከማሊ ህዝብ ጋር ያላቸውን አንድነት" በመግለጽ "የዓመፅ ድርጊቶችን" አውግዘዋል። የምዕራብ አፍሪካ ክልላዊ ቡድን ኢኮዋስም በተመሳሳይ መልኩ ጥቃቶቹን አውግዘዋል።
ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሰራዊቱ ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ አገራቱ ከኢኮዋስን ወጥተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው ሁኔታውን "በጥልቅ ስጋት" እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት የቡርኪናፋሶው ወታደራዊ መሪ ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ በማሊ የተፈጸሙትን ጥቃቶች አውግዘዋል።
ትራኦሬ ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶን ጨምሮ የሳህል ግዛቶች ጥምረት (ኤኢኤስ) ፕሬዝዳንት ሲሆኑ አገራቱ በቅርብ ዓመታት ውስጥ መፈንቅለ መንግስት ከተፈጸመ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት በወታደራዊ መንግስታት የሚመሩ ናቸው።
ትራኦሬ እሁድ ምሽት ባወጡት መግለጫ ጥቃቶቹን "አረመኔያዊ እና ኢሰብአዊ" ሲሉ ገልጸው "በሳህል የነጻነት ትግል ጠላቶች የተደገፉ" መሆናቸውን ተናግረዋል።
ትራኦሬ ጥቃቶቹን "አረመኔያዊ እና ኢሰብአዊ" ሲሉ ገልጸውታል፣ እናም "በሳህል የነጻነት ትግል ጠላቶች የተደገፉ" መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጥቃቶቹ "የሳህልን ጀግኖች በነጻነት፣ በሠላም እና በክብር የመኖር ፍላጎትን ሊያናውጡት አይችሉም" ሲሉ አክለዋል።
የኤፍኤልኤ በሰሜን ማሊ የራሱን የቱዋሬግ አገር ለመፍጠር ለዓመታት ሲታገል የቆ ሲሆን ሰፊውን አካባቢም ውጤታማ በሆነ መንገድ ይቆጣጠራል።
ማሊ በአሁኑ ጊዜ በጄኔራል አሲሚ ጎይታ በሚመራ ወታደራዊ ጁንታ ትተዳደራለች። ጄነራሉ በ2020 በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዙ ሲሆን ደህንነትን ለመመለስ እና የታጠቁ ቡድኖችን ለመዋጋት ቃል ገብተዋል።
ጁንታው ስልጣን ሲይዝ የህዝብ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን በኋላ ላይ በእስላማዊ ታጣቂዎች የተጠለፈውን እና በሰሜን ቱዋሬግ ዓመጽ ምክንያት የተፈጠረውን የረጅም ጊዜ የጸጥታ ቀውስ ለመፍታት ቃል ገብቷል።
የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ እና የፈረንሳይ ኃይሎች ጁንታውን ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ከአገሪቱ የለቀቁ ሲሆን እየጨመረ የመጣውን ዓመፅ ለመቋቋም የሩሲያ ቅጥረኞችን ቀጥሯል።
ሆኖም የጂሃዲስቶቹ ዓመፅ በመቀጠል የአገሪቱ ሰሜን እና ምስራቅ ክፍሎች ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ሆነዋል።