ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በተገኙበት የእራት ግብዣ ጥቃት ስለፈጸመው ግለሰብ እስካሁን ምን እናውቃለን?
ቅዳሜ ምሽት የዋይት ሃውስ ዘጋቢዎች የእራት ግብዣ በተከናወነበት ሆቴል ውስጥ ተኩስ ከከፈተ በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለው ግለሰብ ኮል ቶማስ አለን እንደሚባል የሕግ አስከባሪ አካላት ገልጸዋል።
የ31 ዓመቱ ተጠርጣሪ በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ የቶረንስ ነዋሪ ነው።
ዋሽንግተን በሚገኘው ሂልተን ሆቴል ውስጥ በደኅንነት አባላት በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ፤ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ባለስልጣናትን ለማጥቃት እንደሚፈልግ ለሕግ አስከባሪ አካላት መናገሩን የቢቢሲ የአሜሪካ የዜና አጋር ሲቢኤስ ሁለት ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።
እሑድ ዕለት ከኤንቢሲ 'ሚት ዘ ፕሬስ' ጋር ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካው ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቶድ ብላንች የተጠርጣሪውን ዓላማ በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። "የመጀመሪያ" የምርመራ ውጤቶች ግን ጥቃቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የአስተዳደሩን ባለስልጣናትን ዒላማ እንዳደረገ ያመለክታሉ ብለዋል።
ብላንች አክለውም መርማሪዎች ተጠርጣሪው መሣሪያውን በሆቴሉ ውስጥ እንደገጣጠመ የሚገልጹ ሪፖርቶችን እየተመለከቱ መሆኑን ተናግረው፤ "ያንን ያህል ርቀት መጓዝ አልቻለም" ብለዋል።
"ጥበቃውን እምብዛም አላለፈም" ያሉት ብላንች፤ ተጠርጣሪው ከሎስ አንጀለስ ወደ ቺካጎ ከዚያም ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በባቡር መጓዙን ገልጸዋል።
ሲቢኤስ ምንጮቹን በመጥቀስ እንደዘገበው ቢያንስ ከአምስት እስከ ስምንት የተኩስ ድምጽ ተሰምቷል። ትራምፕ የለጠፉት የደኅንነት ካሜራ ቪዲዮ አንድ ግለሰብ የደኅንነት ጥበቃውን ጥሶ ሲሮጥ እና ጠባቂዎቹ ዞረው ሲከተሉት ያሳያል።
ቀደም ሲል በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፖሊስ አባላት ደኅንነት ሠራተኞች እና ተጠርጣሪው ተኩስ መለዋወጣቸውን ተገልጾ ነበር። ምን ያህል ጥይቶች እንደተኮሱ ግን አልተጠቀሰም።
የዋሽንግተን ጊዜያዊ የፖሊስ አዛዥ ጄፍሪ ካሮል በበኩላቸው ተጠርጣሪው በጥይት ባይመታም ለምርመራ ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪው የጋዜጠኞች እራት ግብዣ በተካሄደበት የዋሽንግተን ሂልተን ሆቴል እንግዳ እንደነበር ገልጸው፤ "ጠብመንጃ፣ የእጅ ሽጉጥ እና በርካታ ቢላዋዎችን እንደታጠቀ" አክለዋል።
አሁን ባለው መረጃ "ብቸኛ ተዋናይ፣ ብቸኛ ታጣቂ" ሆኖ የተንቀሳቀ እንደሚመስል የፖሊስ አዛዡ ተናግረዋል።
ትራምፕ በኋላ ላይ ከወገብ በላይ ራቁቱን የሆነ ግለሰብ መሬት ላይ ተኝቶ እጆቹ ከጀርባው በካቴና ታስረው የሴክሬት ሰርቪስ አባላት በዙሪያው ቆመው የሚያሳይ ፎቶ ለጥፈዋል።
እሑድ ዕለት ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተጠርጣሪው "ልቡ ውስጥ ብዙ ጥላቻ ነበረው"፤ ቤተሰቡም "ችግር እንዳለበት" ያውቁ ነበር ብለዋል። ተጠርጣሪው "ማኒፌስቶ" እንዳለው እና "አክራሪ ፀረ-ክርስቲያን" እንደሆነም ጠቁመዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የ31 ዓመቱ አለን አሌን ፀረ-ትራምፕ ፖለቲካዊ ሃሳቦችን በማኅበራዊ ሚዲያ መለጠፉን የሕግ አስከባሪ ምንጮችን ጠቅሰው እየዘገቡ ነው።
የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ከተጠርጣሪው ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚታመን የጽሑፍ ሰነድ አይቷል። ሌሎች የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃንም በተመሳሳይ ሰነድ ላይ ተመስርተው ዘገባ ሠርተዋል።
ታጣቂው የትራምፕ አስተዳደር አባላትን "ከከፍተኛ ደረጃ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ" ዒላማ ለማድረግ ማቀዱን እንዲሁም እንግዶች እና የሆቴሉ ሠራተኞች ዒላማዎች ባይሆኑም አስፈላጊ ከሆነ ወደ ባለስልጣናቱ ለመድረስ ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል ይገልጻል።
ቢቢሲ ኒውስ የተባሉትን ጽሑፎች በተናጥል ባያረጋግጥም እነዚህ ጽሑፎች እንደ ማኒፌስቶ ከመገለለጻቸውም በላይ ከጥቃት ሙከራው በፊት ለተጠርጣሪው ቤተሰብ አባላት ተልከዋል።
በኋላ ላይ የኤፍቢአይ አባላት እና ፖሊሶች ከተጠርጣሪው ጋር ግንኙነት እንዳለው በሚታመንበት የካሊፎርኒያ አድራሻ አካባቢ ሲፈትሹ የሚያሳዩ ፎቶዎች ወጥተዋል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ የተጠርጣሪውን የበይነ መረብ እንቅስቃሴ ሲፈትሽ ቆይቷል።
የሎስ አንጀለስ የመራጮች ምዝገባ መዝገቦች ምንም አይነት የሚደግፈው ፓርቲ እንዳልነበረው ያሳያሉ።
ቢቢሲ ቬሪፋይ የተመለከተው የፌዴራል የምርጫ ኮሚሽን መዝገብ እንደሚያሳየው እ.አ.አ ጥቅምት 2024 አለን ለካማላ ሃሪስ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ 25 ዶላር ለግሷል።
አለን ራሱን ሜካኒካል ሐንዲስ፣ የጌም ዲቭሎፐር እና መምህር ሲል ሊንክድኢን ላይ ገልጿል።
በመረጃው መሠረት ትልቅ ስም ካለው ከካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ተቋም (ካልቴክ) ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የተማረ ሲሆን በክርስቲያናዊ ህብረት ውስጥ ተሳትፏል።
በ2025 ከካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪ አግኝቷል። የምረቃ ካባውን ለብሶ የተነሳውን ፎቶ ለሊንክድኢን ላይ በማጋራት ስኬቱን ገልጿል። "ቦህርዶም" የሚባል ጌም አዘጋጅቶ ለቅቋል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ በዋሽንግተን ሂልተን ሆቴል በቁጥጥር ስር ከዋለበት ምስል ጋር የሚመሳሰሉ የፎቶዎችን አለን ፌስቡክ ላይ ለጥፏል። ፎቶዎቹ ገና በዓል እና ለምረቃት ከቤተሰቡ ጋር ፈገግ ብሎ የተነሳቸው ናቸው።
እአአ ታህሳስ 2024 በሲ2 ኤጁኬሽን ለተባለ እና ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እና የኮሌጅ ፈተና ዝግጅት በሚሰጥ ተቋም የወሩ ምርጥ መምህር ተብሎ መሰየሙን የተቋሙ የፌስቡክ ልጥፍ ገልጿል።
ከ2020 ጀምሮ የትርፍ ሰዓት መምህር ሆኖ በተቋሙ እያገለገለ እንደሚገኝ በሊንክድኢኑ ላይ ተገልጿል።
የዋሽንግተን ጠበቃ የሆኑት ዣኒን ፒሮ ተጠርጣሪው እንዳሉት በአመጻ ወንጀል ወቅት የጦር መሳሪያ በመጠቀም እና አደገኛ መሳሪያ በመጠቀም የፌዴራል ፖሊስ ላይ ጥቃት በማድረስ ሁለት ክሶች ይመሰረቱበታል።
ሰኞ ዕለት በፌዴራል ፍርድ ቤት በይፋ ክስ እንደሚመሰረትበትም ተናግረዋል።