ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'በጎዳና ላይ ራቁቴን የመሄድ ያህል ነው የተሰማኝ'- በምሥሏ በዲፕፌክ የወሲብ ፊልም የተሠራባት ተማሪ
ሲዩ ክዎንግ (ስሟ ተቀይሯል) የእርሷን ምሥል የያዘ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተፈጠረ ወሲብ ቀስቃሽ ምሥል መሠራጨቱን ያወቀችው በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሆንግ ኮንግ የመጨረሻ ዓመት የሕግ ተማሪ ሳለች ነው።
የመጀመሪያ ስሜቷ ሁኔታው እንዳልተፈጠረ ማመን ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን ፍርሃት እና መረበሽ ወርሰዋታል።
በዲፕፌክ የተሠሩት ምሥሎቿ በፒኪኒ እንዲሁም ያለምንም ልብስ እርቃኗን ሆና ወሲብ ስትፈጽም የሚያሳዩ ናቸው።
ምንም እንኳ እውነት አለመሆናቸውን የምታውቅ ቢሆንም የፈጠረባት ስሜት ግን ከዚያ ያልተናነሰ ነው።
"ሰዎች ገላዬን የሚያዩብኝ ይመስለኛል፤ ልክ ራቁቴን በአውራ ጉዳናው ላይ እንደመሄድ።"
ሲዩ ክዎንግ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ ያጋራችው ምሥሏ በወንድ የክፍል ጓደኛዋ፣ ኤክስ ተወስዶ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ከተቀየረባቸው 17 ሴቶች መካከል አንዷ ናት።
ሴቶቹ ይህንን የክብራቸውን ጥሰት፣ ነጻነታቸው እና ደኅንነታቸው ያለማወላወል የተጋፋ መሆኑን በመግለጽ በሆንግ ኮንግ ሕጎች ላይ ያለውንም ክፍተት አጉልቶ አሳይቷል ብለዋል።
የዩኒቨርስቲ ተማሪው ኤክስ ድርጊቱን መፈጸሙን ቢያምንም የተወሰደበት እርምጃ ውስን ሲሆን፣ ክስም አልተመሠረተበትም። ከዚያ ይልቅ ተበዳዮቹ በሕግ እና በተቋም አሠራር መካከል ራሳቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው አግኝተውታል።
ተደጋጋሚ በደል
እነዚህ ሴቶች መጀመሪያ ላይ የተነገራቸው ኤክስ እያሉ የሚጠሩት የክፍል ጓደኛቸው ሴት ጓደኛ ምሥላቸውን መጠቀሟን ነበር።
ቢቢሲ የቻይና አገልግሎት የተባለውን ግለሰብ ቀርቦ ሲያነጋግራት ግን ምሥሎቹን በኤክስ ላፕቶፕ በሴቶቹ ስም ተመዝግበው ማግኘቷን ተናግራለች።
የተወሰኑት ሲዩ ክዎንግ እና ስዜ ዋኢን ጨምሮ በሆንግ ኮንግ ዩኒቨርስቲ የሕግ ተማሪዎች መሆናቸውን ታውቃለች።
ሌሎቹ ግን ከዚህ ቀደም የኤክስ ጓደኛ የነበሩ ለምሳሌ መምህሩ፣ የክፍል ጓደኛው ፍቅረኛ እና በልጅነት አብረውት የተማሩት መሆናቸውን ተናግራለች።
ከቀውሱ ጋር አብሮ መኖር
ኤሚሊ ከኤከስ ጋር ይህ ከመፈጠሩ በፊት ጓደኛ ነበረች። የቡድን ሥራ ሲሰጣቸው አብረው ይሠሩ እንዲሁም ወደ መዝናኛ ስፍራ በጋራ ይሄዱ ነበር።
ምሥሏን ተጠቅሞ የሠራውን ካወቀች በኋላ ግን እንደተከዳች ተሰማት። ያለ ስምምነት "ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ አካልን ማራቆት" ስትል ትገልጸዋለች።
ሦስቱ ሴቶች የደረሰባቸውን ለትምህርት ቤቱ አስታውቀው ከኤክስ ክፍል እንዲቀየሩ ጠይቀዋል። ነገር ግን ዩኒቨርስቲው እርምጃ ባለመውሰዱ ኤሚሊ በየዕለቱ እርሱን ለማግኘት ተገድዳለች። "በአጠገቤ ባለፈ ቁጥር፣ ብሟሟ ደስ ይለኛል" ትላለች።
በአንድ አጋጣሚ በቀጥታ አጠገቧ ተቀመጠ። ከሳምንታት በኋላ ነው ተጎጂዎቹ ሴቶች ክፍል መቀየር ይችሉ እንደሆን መምህራኖቻቸው የጠየቋቸው።
ለስዜ ዋኢ ዋናው ነገር አንድ ተራ ምሥል እንዴት ወዳልተፈለገ ተግባር ሊለወጥ እንደቻለ ነው።
ከጓደኞቿ ጋር ምግብ እየተመገበች የተነሳችው አንድ ምሥል ተወስዶ ፊቷን የእርሷ በማድረግ ቀሪው አካሏ ግን ከምግባር የወጣ ተግባር ስትፈጽም በሚያሳይ ተቀይሯል።
"እነዚህ ምሥሎች ወደ ሰፊው ማኅበረሰብ ከተሠራጩ እውነተኛ ወይንም ሐሰተኛ ስለመሆናቸው ግድ አይሰጣቸውም" ትላለች።
ለጊዜው ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ብታቆምም፤ ነገር ግን በጣም ባሰብኩት ቁጥር ልሸሸው የማልችለው መሆኑ እየተገለጠልኝ መጣ። እንዴት መከላከል አንደሚቻል እንኳን አላውቅም" ትላለች።
የዩኒቨርስቲው ምላሽ
ተበዳዮቹ በጋራ በመሆን ዩኒቨርስቲው የኤክስን ጉዳይ በሥነ ምግባር ኮሚቴ በኩል አንዲሚለከተው ጠይቀዋል።
ዩኒቨርስቲው ምንም እንኳን የጉዳዩን አሳሳቢነት ቢያምንም የሕግ ባለሙያዎችን ካማከረ በኋላ አሁን ያለው መመሪያ ለእንደዚህ ዓይነት ባሕሪ የሥነ ምግባር እርምጃ አያስወስድም ብሏል።
ከዚያ ይልቅ የሆንግ ኮንግ ዩኒቨርስቲ ኤክስ ድርጊቱን መፈጸሙን እንዳመነ እና የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደተሰጠው፣ ተበዳዮቹንም ይቅርታ እንዲጠይቅ እንደተነገረው የሚገልጹ ሁለት መግለጫዎች አውጥቷል።
በጉዳዩ ላይ አዲስ የተወሰደ እርምጃ እንዳለ ሲጠየቅ ዩኒቨርስቲው ግላዊነትን እና ምሥጢራዊነትን በመጥቀስ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
ውሳኔው ሴቶቹን አስደንግጧቸዋል። በዩኒቨርስቲው ትንሽ የሚባሉ እንደ የቀሪ ተማሪዎችን መቆጣጣሪያ ላይ ማጭበርበር የመሰሉ ጥፋቶች ላይ መደበኛ እርምጃ የሚወስድ ተቋም በኤክስ ዶሴ ውስጥ ጥፋቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ለማካተት እንዲሁም ሌሎች ተጨባጭ እርምጃዎች ለመውሰድ ዳተኛ መሆኑ አስደንቋቸዋል።
በሆንግ ኮንግ የግላዊ መረጃ ጥሰትን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚሽን ግን የወንጀል ምርመራ ጀምሮ ነበር። በኋላ ላይ ግን ለቢቢሲ ቻይና እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ተጨማሪ ማስረጃ አልተገኘም በሚል ምርመራውን ማቋረጡን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ቻይና ኤክስን በስልኩ ላይ በመደወል፣ የጽሑፍ መልዕክት በመላክ፣ በኢሜይል፣ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ አማካኝነት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የሕግ ክፍተት
በሆንግ ኮንግ ሕግ መሠረት በምሥጢር መቅረጽ፣ የቅርብ ወዳጅን ምሥሎች ያለፈቃድ ማጋራት ወንጀሎች ናቸው። ነገር ግን በዲፕፌክ የወሲብ ቀስቃሽ ምሥሎችን መሥራት፣ ማተም ወይም ለማተም ማስፈራራት በግልጽ የተከለከለ አይደለም።
በአንጻሩ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን እና ዩናይትድ ኪንግደም ሁሉም ያለ ስምምነት በዲፕፌክ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ምሥሎች ማዘጋጀትን በተለያዩ ደረጃዎች ወንጀል አድርገውታል።
ቻይና፣ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ዲፕፌኮች ብላ ባትለያቸውም የሌሎችን መብት የሚጥስ ይዘት ለመፍጠር የኤአይ ቴክኖሎጂን መጠቀምን ከልክላለች።
በዩናይትድ ስቴትስ አሁን የኦንላይን መድረኮች ሪፖርት የተደረጉ ያልተፈቀዱ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ምሥሎችን በ48 ሰዓታት ውስጥ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል።
በሆንግ ኮንግ የሴቶችን ፆታዊ ጥቃት በተመለከተ የሚሟገት ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ቼሪል ይፕ ይህ ሁሉ የትኩረት ለውጥን የሚያንፀባርቅ ነው ብለው ያምናሉ።
ከዓላማው ይልቅ "ዋናው ጉዳይ ስምምነት ነው" የሚሉት ኃላፊዋ ግልጽ የሆነ ተፈጻሚነት እኩል ወሳኝ ነው ብለዋል።
ትችትን መጋፈጥ
የሕግ ተጠያቂነትን ለማስፈን የተሯሯጡት ተማሪዎች ወደየትም መሄድ እንደማይችሉ ተገንዝበዋል። ይህም እየተማሩ ባሉት የሕግ ትምህርት እና ሥርዓት ላይ ያላቸውን እምነት ሸርሽሮታል።
በመጨረሻም አደባባይ ወጥተው የደረሰባቸውን ለሕዝብ በመናገር ጉዳያቸው ትኩረት እንዲያገኝ አድርገዋል።
ይህ በይፋ ወጥተው መናገራቸው ነቀፌታንም ድጋፍንም አስገኝቶላቸዋል። ጽንፈኛ ፌሚኒስት፣ የሞራል መብት ተሟጋች እንዲሁም "የአስተሳሰብ ፖሊስ" በሚል ተነቅፈዋል። ሌሎች ደግሞ ኤክስ የሠራው ስህትት ካልሆነ ሕገ ወጥ ነው ሲሉ ከጎናቸው ቆመዋል።
ነገር ግን ሲዩ ክዎንግ ጉዳያቸውን ከቤት ውስጥ ጥቃት ጋር እንደሚመሳሰል ጠቅሳ ቀደም ሲል ሕገወጥ ስላልነበረ ብቻ "ትክክል ነበር ማለት አይደለም" ስትል ትሟገታለች።
ኤሚሊ "የትክክል እና የስህተት የሞራል ጥያቄ በወንድ እና በሴት መካከል እንደ ጦርነት ሜዳ ተደርጎ በተሳሳተ መንገድ መተረጎሙ" ያሳዝናል ብላለች።
በማሌዥያ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ያካተተ ሰፊ የዲፕፌክ ወሲብ ቀስቃሽ ምሥልን በሚመለከት ካነበበች በኋላ ለመናገር መወሰኗን እንደሆነ ገልጻለች። ወጣት ተጎጂዎች ዝም ለማለት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ማየቷ ብቻዋን እንዳልሆነች እንድትገነዘብ አድርጓታል።
ጉዳዩ ሰፊ የሆነ ዓለም አቀፍ ክስተትን ያሳያል። የአሜሪካ የሳይበር ደኅንነት ኩባንያ የሆነው 'ሴኪዩሪቲ ሂሮ' ባደረገው ጥናት እንደ አውሮፓውያኑ ከ2019 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በዲፕፌክ የተሠሩ ቪዲዮዎች ቁጥር ከአምስት እጥፍ በላይ ጨምሯል። ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ወሲብ ቀስቃሽ ምሥሎች ነበሩ፣ እና ሁሉም ሴቶችን በዋናነት ተጠቅመዋል።
የቴክኖሎጂ ዕድገት ማለት በአንድ ግልጽ የፊት ምሥል አማካኝነት ተዓማኒነትን የተላበሱ የዲፕፌክ ቪዲዮዎች በደቂቃዎች ውስጥ ሊፈጠሩ ይችላሉ ማለት ነው።
የሆንግ ኮንግ መንግሥት እና ፖሊስ ከቢቢሲ ቻይና አገልግሎት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፣ አሁን ያለው ሕግ በመርኅ ደረጃ በኦንላይን ላይ ተፈጻሚ መሆኑን እና ቴክኖሎጂው እየተሻሻለ ሲሄድ ውጤታማነቱን መገምገም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ለሲዩ ክዎንግ እና ለሌሎች ተማሪዎች ይህ ምላሽ በቂ አይደለም። ትኩረታቸው አሁን ባለው ሕግ ላይ ሳይሆን መሆን በሚገባው ላይ ነው ትላለች።
ለመቀጠል ያሰቡበት ትግል ነው። "በእውነቱ ተግባራዊ የሕግ ትምህርት እንዳጠናሁ ያህል ተጨማሪ ኮርስ እንደወሰድኩ ይሰማኛል" ትላለች ኤሚሊ። "ሰዎች ደፋር ብለው እንዲጠሩኝ አልፈልግም። በዚህ ሁኔታ እኔ ተጎጂ ነኝ፣ ግን ደካማ አይደለሁም።"