ናይጄሪያዊቷ ደራሲ ቺማማንዳ በልጇ ሞት ላይ የሚደረገውን ምርመራ በማደናቀፍ ሌጎስ የሚገኝ ሆስፒታልን ከሰሰች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ታዋቂዋ ናይጄሪያዊት ደራሲ ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቼ በሕንፃን ልጇ አሟሟት ላይ የሚደረገውን ምርመራ በማደናቀፍ በሌጎስ የሚገኝ ሆስፒታልን ከሰሰች።

ቺማማንዳ እንዳለችው ጥር ወር ላይ በኤውራኬር ሆስፒታል ውስጥ በድንገት ሕይወቱ ያለፈው የ21 ወር ልጇ አሟሟት ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ ሚያዚያ ወር ላይ መጀመር ነበረበት።

በዚህም "ምርመራውን በማዘግየት፣ በመሸፋፈን እና በማደናቀፍ" እንዲሁም የናይጄሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርመራውን እንዲያግድ በመጠየቅ ሆስፒታሉን ከስሳለች።

ቢቢሲ ኤውራኬር ሆስፒታል በቀረበበት ክስ ላይ ምላሹን ጠይቋል።

ቀደም ብሎ በናይጄሪያ በሜዲካል እና በጥርስ ሕክምና ምክር ቤት የተቋቋመው የምርመራ ኮሚቴ በሆስፒታሉ የሕክምና አሰጣጥ ላይ "ግድየለሽነትን" የሚያሳይ ኬዝ ማግኘቱን ገልጿል።

ቺማማንዳ በቅርቡ ሚያዚያ ወር ላይ ለሆስፒታሉ የላከችውን ደብዳቤ በማኅበራዊ ሚዲያዋ ላይ አጋርታለች።

ይህ በማሕፀን ኪራይ ከተወለዱት መንትያ ልጆቿ አንዱን ካጣች በኋላ በይፋ ለሕዝብ የሰጠችው አስተያየት ነበር።

"ኤውራኬር ስለ እውነት የሚጨነቅ ከሆነ ምርመራው ለምን እንዲዘገይ እና እንዲደናቀፍ ያደርጋል? እንዲቆምስ ለምን ይጠይቃል? ብላለች ባጋራችው ልጥፍ።

"ሃዘንን እና ብቸኝነትን የተስፋ መቁረጥን ጥልቅ ስሜት ማወቅ የሚችለው የደረሰበት ብቻ ነው" ብላለች እያለፈችበት ያለውን ጥልቅ ሃዘን ስትገልጽ።

"ቢያንስ በሰላም ሃዘኔን መወጣትን ናፍቄያለሁ፤ ነገር ግን ኤውራኬር ሆስፒታል ያንን እንኳን ነጥቆኛል።"

በደብዳቤዋ ላይ እንደገለፀችው ሆስፒታሉ ልጇ የሞተው በባክቴሪያ በሚመጣ ማጅራት ገትር እንደሆነ ገልጾላታል። ሆኖም ይህንን የሚያስረዳ ምንም ዓይነት የሕክምና ማስረጃ እንደሌለ ገልጻለች።

ቺማማንዳ እና ቤተሰቦቿ የሕክምና ባለሙያዎች ኦክስጅን ስለከለከሉት እና የልብ ችግር ያስከተለበትን ከልክ ያለፈ ማደንዘዣ በመስጠት ሆስፒታሉን በግድየለሽነት ከስሰዋል።

ሆስፒታሉ በሕጻኑ ሞት የተሰማውን ሃዘን የገለጸ ቢሆንም "ምንም ዓይነት ስህተት አልፈፀምኩም" ብሏል።

የሰሚጠው የሕክምና አገልግሎትም ዓለም አቀፍ የሕክምና ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ እንደሆነ አክሏል።

ሆኖም ቺማማንዳ ሆስፒታሉ ያልተሟላ የሕክምና ማስረጃዎች በመስጠት የከሰሰች ሲሆን "በሚያስደነግጥ ሁኔታ ከሙያ ያፈነገጠ ነው፤ አንደኛው ጭራሽ ትክክል አልነበረም" ብላለች ።

በቺማማንዳ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ለፍርድ ቤት የቀረበው ሰነድ እንደሚያስረዳው ከሆነ ንካኑ ቀላል ሕመም አጋጥሞት መጀመሪያ ላይ በሌጎሰ በሚገኘው አትላንቲስ ሆስፒታል ገብቶ ነበር።

ከዚያም ለተሻለ ሕክምና አሜሪካ ወደሚገኘው ባልቲሞር ጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል ለማዛወር ታቅዶ ነበር።

ሆኖም ለቅድመ በረራ ምርመራ ወደ ኤውራኬር ሆስፒታል ተወስዷል።

ንካኑ በሆስፒታሉ የተለያየ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ በአውሮፓውያኑ ጥር 7 ሕይወቱ አልፏል።

ቺማማንዳ 'ሃፍ ኦፍ ኤ የሎው ሰን' እና 'አሜሪካናህ' የተሰኙ መጽሐፍትን ጨምሮ በርካታ ሽልማት ያገኘችባቸውን ልብ ወለድ መጽሐፍት ለንባብ አብቅታለች።

በቅርቡም የቀድሞ አሜሪካ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሃሪስን ጨምሮ የዓለም መሪዎች የተገኙበት ውይይት አዘጋጅታለች።

ቺማማንዳ ነዋሪነቷ በአሜሪካ ሲሆን ለገና በዓል ናይጄሪያ ነበረች።