በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የትራምፕ ስም ከኬኔዲ ማዕከል ተነሳ

ኬኔዲ ማዕከል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኬኔዲ ማዕከል ተነሳ።

የክውን ጥበባት ማዕከሉ እንዳስታወቀው፤ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ተከትሎ የትራምፕን ስም ከማዕከሉ ሕንጻ እንዲሁም ከድረ ገጹ አስወግዷል።

ባለፈው ወር የፌደራል ዳኛ እንዳሉት የትራምፕ ስም በሕንጻው የተጻፈው ከሕግ ውጭ ነው።

ከሕንጻው ላይ የትራምፕ ስም ሲነሳ ብዙዎች ተሰብስበው ሲመለከቱ ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር በመጨረሻው ሰዓት የፍርድ ቤቱን ብይን ለመቀልበስ ቢሞክርም በዳኞች ትዕዛዝ ውሳኔው ጸንቷል።

በአገሪቱ ሕግ መሠረት ማዕከሉ የጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ነው። ስያሜውን ለመለወጥ የተደረገውን ጥረትም ፍርድ ቤት አልተቀበለውም።

'ሀንድስ ኦፍ ዘ አርትስ' የተባለ የንቅናቄ ቡድን ጥበብን ከመንግሥት ጫና ነጻ የማውጣት ዓላማ እንዳለው በመግለጽ ያለፈው አርብ አባላቱን በኬኔዲ ማዕከል አሰማርቷል።

ከአርብ አንስቶ እስከ ትናንት ቅዳሜ ድረስ የትራምፕ ስም ከማዕከሉ ሲነሳ የሚመለከቱ ሰዎች አካባቢውን ሞልተው ታይተዋል።

የትራምፕ ስም ሲነሳ 'አውርዱት!' እያሉ በድምጽ ማጉያ መፈክር ሲያሰሙም ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር በድጋሚ ለፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ መደረጉ ሲነገር ደግሞ በአካባቢው የተሰበሰቡ ሰዎች ደስታቸውን ገልጸዋል።

የትራምፕ ስም ከሕንጻው ላይ ሲነሳ እንዳይታይ ማዕከሉ በፕላስቲክ ተሸፍኖ ነበር።

ዳኛ ክሪስቶፈር ኩፐር ያለፈው ግንቦት ላይ ባስተላለፉት ውሳኔ ያለ ምክር ቤት ፈቃድ የማዕከሉን ስም መለወጥ እንደማይቻል አስታውቀዋል።

ማዕከሉ ዕድሳት እስከሚደረግለት ድረስ እንዲዘጋ የተላለፈውን ውሳኔም ውድቅ አድርገዋል።

የትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ውድቅ ከተደረገ የማዕከሉን መጠሪያ መለወጥ አወዛጋቢ ሊሆን ይችላል ሲል ተከራክሯል።

ትራምፕ የኬኔዲ ማዕከልን ስያሜ መለወጥን ጨምሮ ሌሎችም ማሻሻያዎችን አምና በዋሽንግተን ዲሲ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በአውሮፓውያኑ ጥር 2025 የበርካታ ኬኔዲ ማዕከል ባለ አደራዎችን አባርረው ራሳቸውን ባለ አደራ አድርገው ሾመዋል። ከዚያም የማዕከሉ ኃላፊ ሆነዋል።