የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ከኬነዲ ማዕከል እንዲነሳ ፍርድ ቤት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፍርድ ቤት ከኬነዲ የክዋኔ ጥበባት ማዕከል ላይ የዶናልድ ትራምፕ ስም እንዲነሳ ወሰነ።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ከኬነዲ ተቋም ይፋዊ መጠሪያነት፣ አካላዊ እና የዲጂታል መለያዎች እንዲሁም ይፋዊ ቁሳቁሶች ላይ በ14 ቀናት ውስጥ እንዲነሳ ክሱን የተመለከቱት ዳኛ ወስነዋል።
ዳኛው የማዕከሉ ስም ያለ ኮንግረሱ ፈቃድ አይለወጥም ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ዓመት ነበር በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬነዲ ማዕከል ስማቸው አባሪ እንዲሆን እና በዋሽንግተን ዲሲ ሌሎች ማሻሻያዎችን ይፋ ያደረጉት።
በርካታ የማዕከሉን ባለአደራዎች በመቀየር ራሳቸውን ባለአደራ አድርገው የሾሙት ትራምፕ፤ በኋላ ላይ ደግሞ የጥበብ ማዕከሉ ሊቀ መንበር ሆነዋል።
ባለፈው ታኅሳስ ወር ቦርዱ የተቋሙን ስም ለመቀየር ውሳኔ አሳልፏል። በውሳኔው ማግስት የትራምፕን ሙሉ ስም የያዘ አዲሱ የማዕከሉ መጠሪያ የተቋሙ የፊት መግቢያ በር ላይ ተለጥፏል።
የኬነዲ ማዕከል ቃል አቀባይ የዳኛውን ትዕዛዝ ይግባኝ እንደሚሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቱሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው "እየወደቀ ያለውን ተቋም ወደ እኛ ለመመለስ ከኮንግረሱ ጋር እሰራለሁ" ብለዋል።
ትራምፕ የአሜሪካን 250ኛ ዓመት ልደት ለማክበር ሲባል ማዕከሉን ለማደስ ለሁለት ዓመታት እንዲዘጋ የሰጡትን ትዕዛዝም ዳኛው አግደውታል።
የማዕከሉ የቦርድ እና የኮንግረስ አባል የሆኑት ጆይስ ቢቲ እና ሌሎች የማዕከሉ የቀድሞ ባለአደራዎች ናቸው ትራምፕ ላይ ክስ የመሰረቱት።
"የዛሬው ውሳኔ አስተዳደሩ የማዕከሉን ሥም ለመቀየር እና ማዕከሉን ለመዝጋት ያደረገው ጥረት ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው በትክክል አሳይቷል" ሲሉ ጆይስ ቢቲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኬነዲ ማዕከል የአሜሪካ ሕዝብ እንጂ የዶናልድ ትራምፕ አይደለም ያሉት የኮንግረስ አባሏ፤ ፕሬዝዳንቱ የተከበረውን ማስታወሻ ለራሳቸው ከንቱ ፍላጎት ሲሉ አራክሰውታል ብለዋል።
የማዕከሉ ቃል አቀባይ ሮማ ዳራቪ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ በላኩት መግለጫ፤ ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ ባህል ማዕከል ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠት ሲል ቦርዱ የወሰነውን ውሳኔ ለመመለስ ይግባኝ እንደሚሉ ተናግረዋል።
የማዕከሉ ሙሉ ስም የተቀየረው 'የዶናልድ ጄ ትራምፕ እና ጆን ኤፍ ኬነዲ መታሰቢያ የክዋኔ ጥበባት ማዕከል' ተብሎ ነው።
ዳኛ ክርስቶፈር ኩፐር የሰጡት ትዕዛዝ የማዕከሉ ሥም እ.አ.አ በ1971 ሲመሰረት ጀምሮ በነበረው መጠሪያ 'ጆን ኤፍ ኬነዲ መታሰቢያ የክዋኔ ጥበባት ማዕከል' እንዲባል ነው።
"ኮንግረስ ለኬነዲ ማዕከል ስም የሰጠ ነው፤ እናም ስሙን የሚቀይረው እርሱ ብቻ ነው" ብለዋል።
ኬነዲ ማዕከል እ.አ.አ በ1963 ለተገደሉት ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬነዲ መታሰቢያ እንዲሆን ነበር የተሰራው።














